መሪዎቹ እየተገደሉበት ባለበት ጸንቶ የቀጠለው የኢራን የጦርነት ወቅት አመራር የተዋቀረው እንዴት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢራን በኩል ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ድርድር እያደረጉ ያሉት የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህም ኢራን ጠቅላይ መሪዋ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከተገደሉ በኋላ ማን እያስተዳደራት ነው? የሚል ጥያቄ አጭሯል።
ትራምፕ አምባገነን መንግሥታትን ለመገርሰስ ሲያስቡ በቬንዙዌላ ላይ የወሰዱት ዓይነት እርምጃን መተግበር ይሻሉ።
ሆኖም የኢራን ጠቅላይ መሪ መገደል የታሰበውን የሥርዓት ለውጥ አላመጣም። አገሪቱም የተዳከመች አትመስልም።
የኢራን እስላማዊ ዘብ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን መቋቋም በሚያስቸለው መንገድ እንደተዋቀረ ተንታኞች ይናገራሉ።
የኢራን አስተዳደር ወታደራዊ መዋቅሩን እንደያዘ ቀጥሏል። የኢራን የሥልጣን ክፍፍል በሃይማኖታዊ መሪዎች፣ በፖለቲከኞች እና በዋነኛነት በእስላማዊ አብዮቱ ዘብ ከፍተኛ አዛዦ ተከፋፍሏል።
የጦርነቱን መነሳት ተከትሎ ውሳኔ ሰጪው አካል የደኅንነት መዋቅሩ ሆኗል። ወታደራዊ ልምድ ያላቸው አመራሮችም በዚህ ይሳተፋሉ። የኢራን መደበኛ የአመራር ተዋረድ አሁንም ባለበት ይገኛል።
እስራኤል እና አሜሪካ በከፈቱት ጥምር ጥቃት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቢገደሉም አስተዳደሩ በመንግሥት ሥራዎች እና በወታደራዊ ኃላፊነቶች ተከፍሎ ቀጥሏል።
አስተዳደሩ የተዋቀረው የከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደል እንዳይንደው በተቀመረ አካሄድ እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ከፍተኛ አመራሮች ሲገደሉ የሚተኳቸው ባለሥልጣናት መዘጋጀታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ሲያስተጋቡ ይደመጣል። የቴህራን ባለሥልጣናትም ይህንኑ ደጋግመው ተናግረዋል።
አዲሱ ጠቅላይ መሪ አገሪቱን እየመሩ ነው?
የተገደሉት የኢራን ጠቅላይ መሪ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን ሥልጣን በይፋ ተረክበዋል።
ይህ የጠቅላይ መሪው ሥልጣን በእስላማዊ አብዮታዊ አመራር ውስጥ ከፍተኛው ነው። በወታደራዊ መዋቅር፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በቁልፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ሥልጣን ይሰጣቸዋል።
በተግባር ግን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ያላቸው ሥልጣንን በተመለከተ የጠራ መረጃ የለም። ከሕዝብ ዕይታ መራቃቸው እና አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል የሚለው ጭምጭምታ ጥያቄዎች አስነስቷል።
አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ እምብዛም በሕዝብ አልታዩም። በአስተዳደር እና ዲፕሎማሲ ረገድ ያላቸው የልምድ ማነስ በዚህ ፈታኝ ወቅት ዋነኛ አመራር እንዳይሆኑ ሊያግዳቸው ይችላል።
በአገሪቱ አስተዳደራዊ መርኅ መሠረት ከፍተኛው ሥልጣን የጠቅላይ መሪው ቢሆንም እንኳ፤ በዚህ የጦርነት ወቅት የዕለት ከዕለት ውሳኔዎች ላይ የሚደረሰው በከፍተኛ አመራሮች እና በአብዮታዊ ዘቡ ከፍተኛ አዛዦች ምክክር ይሆናል።
ስለዚህም አሁን ያለው የኢራን አስተዳደር ቅይጥ መልክ አለው። ማዕከሉን ያደረገው ጠቅላይ መሪውን ነው። ጠቅላይ መሪው የአንድነት ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ።
ሆኖም ግን ውሳኔዎችን በመስጠት ረገድ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ልሂቃን ይሳተፋሉ።
የኢራን እስላዊ አብዮታዊ ዘብ እና መደበኛ ሠራዊቱን ጥምረት የሚቆጣጠረው የማዕከላዊ ዕዝ ዋና ጽህፈት ቤት (ካህቱም አል-አንቢያ) በጦርነቱ ማዕከላዊ ቦታ የያዘውም ለዚህ ይሆናል።

የአብዮታዊ ዘቡ ሚና ምንድን ነው?
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአገሪቱ ዋነኛ አስተዳደራዊ መዋቅር ነው።
አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ አብዮታዊ ዘቡ ያለው ሚና ሰፍቷል።
በአውሮፓውያኑ 1979 የአብዮቱን ዕሳቤ እና አመራር ለማስጠበቅ የተቋቋመው አብዮታዊ ዘቡ ወደ ኃያል ወታደራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ተሻግሯል።
የኢራንን የባለስቲክ ሚሳዔል እንዲሁም የውጭ ዘመቻዎችን እና የአገር ውስጥ የደኅንነት እንቅስቃሴዎችን ይመራል።
የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ግድያን ተከትሎ የሥልጣን ሽግግርን ጨምሮ የቴህራንን አስተዳደራዊ መዋቅር እያስቀጠለ ያለው እስላማዊ አብዮታዊ ዕዝ ነው።
በአዲሱ ጠቅላይ መሪ ሹመት ውስጥም ቁልፍ ሚና እንዳለው ተንታኞች ይገልጻሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት የኢራን ጠቅላይ መሪ ይፋዊ የመንግሥት ሥልጣን ባይኖራቸውም ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር የቅርብ ትስስር አላቸው።
በተለይም ከጦርነቱ እና ቀጣናዊ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች ላይ የሚደረሰው በአብዮታዊ ዘቡ አማካኝነት ነው።
የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ የቀድሞ እና የአሁንም አዛዦች በመላው አገሪቱ በምክር ቤት፣ በደኅንነት መዋቅሮች እና በቀጣናዊ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው።
ይህ የሚከወነው በአንድ ሰው ሳይሆን በከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ደጋፊዎቻቸው በሆኑ ፖለቲከኞች መዋቅር ውስጥ ነው። የኢራን አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ የዚህ መዋቅር አንድ አካል ናቸው።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እያደረገ ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከመዋቅሩ አሠራር ጋር የሚያያዝ ነው።
የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች እየተገደሉ እና የጥቃት ዒላማ እየሆኑም አስተዳደሩ መቀጠል በሚችልበት መንገድ ነው የተዋቀረው።
"መስዋዕት የሆኑ" አመራሮችን በሌሎች ባለሥልጣናት በመተካት ወደፊት እየቀጠለ ይገኛል።
በዚህ መዋቅር ውስጥ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማዕከላዊ ሚናውን ይዞ ከመጋረጃ ጀርባ ዋነኛ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል።
የኢራን አፈ ጉባዔ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው?
የኢራን አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ በቴህራን በሕይወት ከሚገኙ ዋነኛ የፖለቲካ መዋቅሩ አባላት መካከል አንዱ ናቸው።
ከአሁኑ ጦርነት በፊት በተካሄደው የ12 ቀናት የኢራን እና እስራኤል ግጭት የቴህራን ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸው ይታወሳል።
አፈ ጉባዔው በወታደራዊ እንዲሁም በሲቪል አመራር ውስጥም ቁልፍ ሚና ያላቸው ናቸው። ባለፉት 40 ዓመታት በፖለቲካ እና በደኅንነት ከፍተኛ መሪነት ሠርተዋል።
በአውሮፓውያኑ ከ1994 እስከ 2000 የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ ነበሩ። ከ2000 እስከ 2005 ደግሞ የፖሊስ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
በ2020 አፈ ጉባዔ ከመሆናቸው አስቀድሞ ከ2005 እስከ 2017 ድረስ የቴህራን ከንቲባ ነበሩ። ዋና ከተማዋን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩም መሪ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2005 ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው 13.8 በመቶ ድምጽ በማግኘት በአራተኛ ደረጃ አጠናቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው አልተሳካላቸውም። በ2013 ሲወዳደሩ በ16.6 በመቶ ድምጽ ሁለተኛ ሆነዋል።
በ2017 ደግሞ ኢብራሒም ራኢሲን በመደገፍ ከዕጩነት ራሳቸውን አግልለዋል። በምርጫው ያሸነፉት ሐሰን ሩሀኒ ነበሩ።
ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በ2024 በተካሄደ ምርጫ ማሱድ ፔዜሽኪያን ሲያሸንፉ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ በሦስተኛነት አጠናቀዋል።
ጋሊባፍ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በማፈን የሚታወቁ ሲሆን፤ ይህም የ1999 የተማሪዎች ንቅናቄን ይጨምራል።
በሌላ በኩል የኢራንን የምጣኔ ሃብት ችግር መቅረፍ እንደሚችሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ለረዥም ጊዜ የሙስና ክስ ሲቀርብባቸው ነበር። ሆኖም ግን ጉዳዩ ፍርድ ቤት አልተወሰደም። በ2022 ኢራናውያን በኑሮ ውድነት ሲፈተኑ፤ ቤተሰባቸው ወደ ኢስታንቡል "ቅንጡ ጉዞ አድርጓል" ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲወገዙ ነበር።
አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ መካለኛው መንገድ ላይ እንዳለ ባለሥልጣን ነው የሚቆጠሩት።
የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃንን፣ የሃይማኖት መሪዎችን እና የደኅንነት ባልደረቦችን መካከል ላይ ሆኖ በማቀራረብ ስማቸው ይነሳል።
በኢራን መሪዎች ላይ ጥቃቶች ሲሰነዘሩ እሳቸው ግን መሀል ላይ እንደሚገኝ ባለሥልጣን ተቆጥረዋል።
ሆኖም ግን ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ተጋንኖ መታየት የለበትም።
እንደ አሸማጋይ ሊወሰዱ ይችላሉ የሚሉ ሪፖርቶች ቢወጡም የወታደራዊ እና ሃይማኖታዊ መዋቅሮች ድጋፍ እንደሌላቸው ይታመናል።
ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሚዘወር የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚወሰን ይሆናል። አብዮታዊ ዘቡ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ድምጽ በማስተጋባት ይታወቃል።

የኢራን ፕሬዝዳንት እና ካቢኔ ሚና
ፕሬዝዳንት ማሱድ የአገሪቱን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እየመሩ ይገኛሉ። ሆኖም ግን ሥልጣናቸው የተገደበ ይመስላል።
ጠቅላይ መሪው መገደላቸውን ተከትሎ ከከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን በሽግግር አስተዳደር ሥር ካሉ ሦስት አመራሮች አንደኛው ነበሩ።
ሆኖም ግን ወቅቱ የጦርነት በመሆኑ እና የደኅንነት አመራሮች ሚና እየጎላ በመሄዱ ምክንያት የተመረጠው የመንግሥት አስተዳደር ሚናው እየተገደበ መጥቷል።
አዲስ ጠቅላይ መሪ ከተሾሙ በኋላ የአስተዳደራዊ መዋቅር ሚና ተለውጧል።
ፕሬዝዳንት ማሱድ ከጦርነቱ በፊት እና በጦርነቱ ወቅትም ስትራቴጂያዊ ውሳኔያቸው ላይ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ብዙዎች ያምናሉ።
ፕሬዝዳንቱ በተለይም ከወታደራዊ እና የውጭ ጉዳይ ውሳኔዎች መገለላቸው ይገለጻል።
ሆኖም ግን ካቢኔው የሕዝብ አገልግሎት እና ግብይትን በማሳለጥ ቁልፍ ሚና አለው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች አመራሮች ሚና
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ከአሜሪካ እና ከተቀሩት ምዕራባውያን ጋር በመደራደር ልምድ ያካበቱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ከኒውክሌር ጋር የተያያዙ ድርድሮችን መርተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ኃላፊነት በማጣጣም የተዋጣላቸው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ሆኖም ግን ስትራቴጂ እና ፖሊሲ የሚወሰነው በእሳቸው ደረጃ አይደለም። ዋነኛው አመራር የሚሰጠው በአገሪቱ ብሔራዊ ላዕላይ ምክር ቤት ነው።
በጦርነትም በሰላም ወቅትም ከፍተኛ ሚና ያለው ተቋም ነው። የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ይቀርጻል። በጠቅላይ መሪው ሥር መከላከያን በማዋቀር እና የደኅንነት መረጃ በማደራጀት ረገድም የጎላ ሚና ይጫወታል።
መሪው ፕሬዝዳንቱ ሲሆኑ ከፍተኛ ሚኒስትሮች፣ ዳኞች፣ የምክር ቤት አባላት እና የጠቅላይ መሪው ተወካዮችን ያካትታል። ውሳኔዎቹ በጠቅላይ መሪው ይሁንታ ሲያገኙ ይተገበራሉ።
የጠቅላይ መሪው መገደል በምን መንገድ እና መቼ ይገለጽ የሚለው የተወሰነው በዚህ ምክር ቤት ነው። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ይፋዊ መረጃ እና ማረጋገጫ የመስጠት ሥልጣንም አለው።
ኢራን እና እስራኤል የ12 ቀናት ጦርነት ባደረጉበት ወቅት የተመሠረተው የመከላከያ ምክር ቤት ወታደራዊ ውሳኔ በማዕካለዊ ዕዝ እንዲተላለፍ የማድረግ ሚና አለው።
ይህም ከፍተኛ ወታደራዊ እና የሲቪል አመራሮች የያዘ ሲሆን፤ ሦስት እርከን ያለው አመራር፣ ሁለት የጠቅላይ መሪው ተወካዮች እንዲሁም ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና ሌሎችም አባላትን ይዟል።
ሌሎች በጦርነቱ ወቅት ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መካከል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪው ብርጋዴር ጄነራል አሕመድ ቫህዲ ይጠቀሳሉ።
የኢራን እስላዊ አብዮታዊ ዘብ እና የመደበኛ ሠራዊቱን ጥምረት የሚቆጣጠረው ማዕከላዊ ዕዝ ዋና ጽህፈት ቤት (ካህቱም አል-አንቢያ) መሪ ጄነራል አሊ አብዱላሂ ሌላው መሪ ናቸው።
በተጨማሪም የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአየር ኃይል ኃላፊ አድሚራል አሊሬዛ ታግሲሪ፣ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል ኃላፊ ሜጀር ጄነራል አሚር ሐታሚ ይገኙበታል።
እንዲሁም የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የቁድስ ኃይል ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል መሐመድ ባጊር ዞላግዳር፣ የፖሊስ ኃላፊ አሕመድ ሬዛ ረዳን እና የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ማጂድ ካምዳሚ ይገኙበታል።















