በወር አበባ ወቅት የሚሰቃዩ ሴቶችን ሕመም ለመቀነስ የሚደረገው ምርምር ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

የወር አበባ ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኤማ ባክሉድ ብዙም ስለ ወር አበባዋ አታስብም ነበር፤ በአውሮፓውያኑ 2023 ኔክስት ጄን የተባለ የባዩቴክ ተቋም የወር አበባ ናሙናዋን እንድታቀርብ እስከሚጠይቃት ድረስ።

ካሊፎርኒያ፣ ኦክላንድ የሚገኘው ተቋም የወር አበባ ናሙና ሲጠይቃት አንግዳ ሆኖባት ነበር። ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚሰማቸውን ሕመም ማስወገድ የሚችል ጥናት ተሳታፊ እንደምትሆን ስታስብ ተስማማች።

ሚኒሶታ የምትኖረው ኤማ "11 ዓመት ሲሞላኝ የወር አበባዬ መጣ። የምሞት ነበር የመሰለኝ" ትላለች።

"ለእናቴ ሆስፒታል መሄድ እንዳለብኝ ነገርኳት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየወሩ ሆስፒታል መሄድ እንዳለብኝ ይሰማኛል። በየወሩ ያስመልሰኛል። ትምህርት ቤት መሄድ ወይም አንዳች ማኅበራዊ ጉዳይ መሳተፍ የማልችልበት ጊዜ አለ። ማቃጠል፣ መውጋት፣ መቁረጥ እና ሌሎችም የሕመም ስሜቶች ቀጥለዋል።"

የማሕጸን ሕዋስ ከማሕጸን ውጭ ሲያድግ የሚፈጠረው ሕመም (endometriosis) እንዳለባት ለማወቅ 13 ዓመታት ወስዶባታል።

በመላው ዓለም 190 ሚሊዮን ሴቶች በዚህ ሕመም ይሰቃያሉ። መውለድ በሚቻልበት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች አንድ አሥረኛው ናቸው።

እነዚህ ሴቶች ከመጠን ያለፈ የወር አበባ የሚያዩ ሲሆን፣ ከፍተኛ ሕመም ይሰማቸዋል። ከሽንት እና ሰገራ ጋር የተያያዘ ችግር እንዲሁም ከወሊድ ጋር የተያያዘም እክል ይገጥማቸዋል።

አንድ ሴት ሕመሙ እንዳለባት ለማወቅ ከአምስት እስከ 12 ዓመት መጠበቅ አበላት፤ ኤማ የገጠማትም ይሄ ነው።

የኔክስት ጄን አጋር መሥራች ሪዳሂ ታሪያል እንደምትለው፤ ምርመራውን ለማድረግ ከሆድ እቃ በታች ባለው የዳሌ አካባቢ ትንሽ ካሜራ ማስገባት (laparoscopy) ያስፈልጋል።

ሪዳሂ የምርመራው ሒደት እንዲሻሻል ከሚሠሩ ባለሙያዎች አንዷ ናት። ምርመራው ፈጣን፣ ርካሽ፣ ውስን ቀዶ ሕክምና ብቻ የሚፈልግ እና ከኢንዶሜትሪዮሲስ ሕመም ውጪ ያሉ ሕመሞችን ለማወቅ የሚውልም እንዲሆን ትፈልጋለች።

ይሄንን ለማሳካት ቁልፍ የሆነው የወር አበባ ደም እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያምናሉ።

የወር አበባ ናሙና

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ BBC

የወር አበባ ናሙና

የሽንት ናሙና መመርመር ከ6,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። ከሽናት ናሙና ምርመራ በኋላ ሳይንስ የሰገራ እና ደም ምርመራን አካቷል።

የወር አበባ ደም ላይ ግን ምርመራዎች አልተካሄዱም። በወር አበባ ደም ውስጥ የፕሮቲን፣ የሆርሞን፣ የባክቴሪያ፣ የማሕጸን ሕዋስ፣ የብልት ግድግዳ፣ የማሕጸን ግድግዳ እና የእንቁላል ዕጢ ናሙና ማግኘት ይቻላል።

"የሚገኘው የሕዋስ ናሙና በደም፣ በምራቅ ወይም በሌሎች የሰውነት ናሙናዎች የማይገኝ ነው። በሥነ ተዋልዶ ሚና ያላቸው የሰውነት ክፍሎችን ገጽታ ለመረዳት ይጠቅማል" ስትል ባለሙያዋ ታስረዳለች።

ኔክስት ጄን ከበጎ ፈቃደኞች ናሙና ለመሰብሰብ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ይልካል። ከአውሮፓውያኑ 2014 ወዲህ ከ330 በላይ ሴቶች የሰጡት ከ2,000 በላይ ናሙና ላይ ምርምር አድርጓል።

በፌንስቲን ኢንስቲትዩት ፎር ሜዲካል ሪሰርች ውስጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ክርስቲን ሜቴዝ "ማሕጸንን የሚጎዳ ማንኛውንም ሕመም በወር አበባ ናሙና መለየት ይቻላል። እነዚህ ሕመሞች ብዙ ዓይነት ናቸው" ይላሉ።

ኢንዶሜትሪዮሲስ ላይ ምርምር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከሰውነት በሚወሰድ ናሙና የኢንዶሜትሪክ ካንሰር ወይም የማሕጸን ግድግዳ እና በሽንት ትቦ ግድግዳ አካባቢ ሲወጣ የሚፈጠረውን ሕመም (endometritis) አልያም የኢንዶሜትሪያል ግድግዳ እብጠትን ለማወቅ ይውላል።

"የወር አበባ ደም ናሙና የማሕጸን ጤናን ለመረዳት ይጠቅማል። ስለ ማሕጸን ማወቅ የምንችልበት ሌላ ብዙም መንገድ የለም" ይላሉ ባለሙያዋ።

ምርመራውን ቤት ውስጥ ማካሄድ የሚቻልበት መሣሪያ ያዘጋጁ ሲሆን ከአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ፈቃድ እስከሚያገኙ እየጠበቁ ነው።

የፎቶው ባለመብት, NextGen Jane

የምስሉ መግለጫ, ምርመራውን ቤት ውስጥ ማካሄድ የሚቻልበት መሣሪያ ያዘጋጁ ሲሆን ከአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ፈቃድ እስከሚያገኙ እየጠበቁ ነው።

አንድ ጥናት በወር አበባ ደም ውስጥ የሚገኙ 385 የፕሮቲን ዓይነቶችን ለይቷል።

የወር አበባ ደም በየወሩ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ አጠቃላይ የማሕጸን ጤናን ለማወቅ ዋነኛው መንገድ ነው።

"ማሕጸን የወይን ፍሬ ያህል ነው። አነስተኛ ካሜራ በማሕጸን ውስጥ በማስገባት የሚደረግ ምርመራ ከሚያሳየው ይልቅ የወር አበባ ደም ናሙና አጠቃላይ ገጽታውን ያሳያል" ይላሉ።

የወር አበባ ደም ናሙና ላይ እምብዛም ምርምር ስላልተደረገ አሁንም ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ።

ሪዳሂ ምርምር የምታደርገው ከጄነቲሲስት ፒተር ግራግሰን ጋር ነው። እስካሁን በጥናታቸው የተሳተፉት 3,700 ሴቶች ናቸው። አበረታች ውጤት እንዳገኙ ይናገራሉ።

ኢንዶሚትሪዮሲስ ያለባቸው ሴቶች ማሕጸን ጽንስ እንዲሸከም፣ ጽንሱ እንዲያድግ እና ጽንስን ከኢንፌክሽን ለመከላከል የሚያስችለው ሕዋስ (uterine) በውስን መጠን ሰውነታቸው ውስጥ እንደሚገኝ ሪዳሂ ትናገራለች።

ለጽንስ ዕድገት ካላቸው ጥቅም አንጻር በውስን መጠን ሲገኙ ችግር ያስከትላሉ።

የወር አበባ ናሙና

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/ BBC

አዲስ የምርምር ስልት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የማሕጸን ግድግዳ ከእያንዳንዱ የወር አበባ በኋላ እንዲታደስ የሚረዳው ሕዋስ (stromal fibroblast cells) ከእርግዝና ጋር ያለውን ትስስርም በጥናታቸው ዳስሰዋል።

ይህም ጽንስ ከማስወረድ እና እንደ ፖሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድረም (polycystic ovarian syndrome ወይም PCOS) ጋር የሚተሳሰር ነው።

የወር አበባ ደም ናሙና ኢንዶሚትሪዮሲስ ሰውነትን በማይጎዳ ምርመራ የሚታወቅበት መንገድ ነው።

ምርመራውን ቤት ውስጥ ማካሄድ የሚቻልበት መሣሪያ ያዘጋጁ ሲሆን ከአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ፈቃድ እስከሚያገኙ እየጠበቁ ነው።

ከወር አበባ ደም ናሙና ውስጥ አርኤንኤ (RNA ወይም mRNA) ዘረ መል በማግኘት ሕመሙን ለመለየትም ምርምር አድርገዋል።

በአውሮፓውያኑ 2025 ኔክስት ጄን ሙከራ እንዲያካሂድ 1.62 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል።

ሌላው የጥናታቸው ትኩረት የማሕጸን እና የዕድሜ ትስስር ነው። በሰውነት ውስጥ የኦኤስትሮጅን ሆርሞን መጠን ሲጨምር የወር አበባ እየቀነሰ ወይም ዕድሜ እየጨመረ እንደሆነ ያመላክታል።

በተጨማሪም ሰውነት ምግብ የሚያብላላበትን ሆርሞን ከሚፈለገው አብዝቶ ወይም አሳንሶ የሚያመርት ከሆነ የሚፈጠረውን ሕመም (hypo ወይም hyperthyroidism) በወር አበባ ደም ናሙና ለመለየት ጥናታቸውን ቀጥለዋል።

ሰውነት ምግብን የሚያብላላበትን ሆርሞን የሚቆጣጠሩት (thyroxine እና triiodothyronine) ከኢንዶሚትሪዮሲስ ጋር ትስስር እንዳላቸው ሪዳሂ ትናገራለች።

የወር አበባ ዑደት ሰውነት ላይ የተለያዩ ለውጦች የሚያስከትል ስለሆነ እንደ አርትራይተስ፣ ሉፐስ እና መልቲፕል ስኬሎሮሲስ ያሉ ሕመሞችን ለማወቅም እንደሚረዳ ታክላለች።

በአውሮፓውያኑ ከ2021 እስከ 2024 የተሠሩ ጥናቶች የወር አበባ ደም ናሙና ለስኳር ምርመራ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ካሊፎርንያ የሚገኘው ኩቪን ደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመለካት የወር አበባ ደም ላይ ምርምር አድርጓል።

በ2024 የአሜሪካ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ የሰጠው ወር አበባን መሠረት ያደረገ የስኳር ምርመራ ይፋ አድርገዋል።

ኤችፒቪ በሰውነት ውስጥ መኖሩን ለማወቅ የወር አበባ ደም ናሙና እንደሚረዳ በአውሮፓውያኑ በ2022 በታይላንድ የተሠራ ጥናት ይጠቁማል። ኤችፒቪ የማሕጸን ካንሰር ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል።

እንደ ጨብጥ ያሉ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመለየት የወር አበባ ደም ናሙና የሚኖረውን ሚና ለማወቅ ምርምሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የኩቪን ኃላፊ ማድስ ሊላንድ ይናገራሉ።

በርሊን ውስጥ የሚካሄድ ምርምር ቅድመ ማረጥን እና ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ሕመሞችን ለመለየት ይሞክራል።

የወር አበባ ደም ምርምር አሁንም ብዙ ይቀረዋል። በውስጡ ስለያዛቸው ንጥረ ነገሮች አሁንም በግልጽ እንደማይታወቅ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

"የወር አበባ ሊነገር የማይገባ አሳፋሪ ነገር ተደርጎ ነው የሚወሰደው" ትላለች ሪዳሂ።

በሴቶች ጤና ምርምር ላይ ብዙም የገንዘብ ድጋፍ አለመገኘቱ ጥናቱን እንዳጓተተው ታስረዳለች።

በ2020 ዓለም አቀፍ የሴቶች ጤና ምርምር 5 በመቶ ብቻ ነበር የሸፈነው።

"አብዛኞቹ የመድኃኒት ምርምሮች የተደረጉት በወንዶች ላይ ነው። የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች ያማከለም አይደለም" ትላለች ባለሙያዋ።

እንደ ኤማ በየወሩ በወር አበባቸው ምክንያት በሕመም የሚሰቃዩ ሴቶች ጥናቶች ቀደም ብለው መጀመር ነበረባቸው ብለው ያምናሉ።

"በወር አበባ ምክንያት መታመም በጣም ብቸኛ የሚያደርግ ስቃይ ነው" ስትል ትናገራለች።

የሕመሙን መንስዔ በፍጥነት ማወቅ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫናን እንደሚቀንስ ትናገራለች።