ኦቲዝም ከሴቶች ይልቅ በተለይ በወንዶች ላይ ይስተዋላል? እንዴት ቀድሞ መለየት ይቻላል?

ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ሴቶችም ወንዶችም ሕጻናት በእኩል ደረጃ ለአእምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ወንዶች የበለጠ ለአእምሮ ዕድገት መዛባት ተጋላጭ ናቸው የሚለውን አመለካከት ጥናቶች ውድቅ ያደርጋሉ።

ከአሥር ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት ዘንድ በአማካይ አራት ወንዶች የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባቸው ማወቅ ይቻላል። ከሴት ሕጻናት መካከል ግን ሲነጻጸር ኦቲዝም እንዳለባት የሚታወቀው አንዲት ታዳጊ ብቻ ናት።

ስዊድን የሚገኘው ኮሮሊንስካ ኢንስቲትዩት የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው፤ የአእምሮ ዕድገት መዛባትን በማወቅ ረገድ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለው ልዩነት በጊዜ ሒደት እየጠበበ መጥቷል።

ሴት ሕጻናት ከወንዶች ዘግይተው ኦቲዝም እንዳለባቸው ይታወቃል። ወደ 20 ዓመት ሲጠጉ ግን የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባቸው የሚታወቅበት መጠን እኩል ይሆናል።

ጥናቱ ከአውሮፓውያኑ 1985 እስከ 2020 የተወለዱ 2.7 ሚሊዮን ስዊድናውያንን ያካተተ ነው። ከተሳታፊዎቹ 2.8 በመቶ የሚሆኑት ከሁለት ዓመት እስከ 37 ባለው ዕድሜ ክልል የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባቸው ታውቋል።

ሴቶችም ወንዶችም ሕጻናት በእኩል ደረጃ ለአእምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴቶችም ወንዶችም ሕጻናት በእኩል ደረጃ ለአእምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ

በብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል የወጣው ጥናት መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ካሮላይን ፌፌ "ሴቶች ኦቲዝም እንዳለባቸው የሚታወቀው ዕድሜያቸው ሲጨምር መሆኑን ጥናታችን ያሳያል" ይላሉ።

ይህም በይበልጥ የተስተዋለው ከ15 እስከ 19 ዓመት በሆናቸው ሴቶች ላይ ነው። የአእምሮ ዕድገት መዛባትን በመለየት ረገድ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"20 ዓመት ላይ ወንዶችም ሴቶችም ኦቲዝም እንዳለባቸው የሚታወቀው በእኩል መጠን ነው። ስለዚህ ዕድሜያቸው ከፍ ሲል በፆታዎቹ መካከል ያለው ልዩነት ይጠባል" በማለት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ በ2021 ባወጣው አሃዝ መሠረት በመላው ዓለም ከ127 ሰዎች መካከል አንዳቸው ኦቲዝም እንዳለበት/እንዳለባት ያሳያል።

አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት በቂ መረጃ ባይገኝም፤ ለአእምሮ ዕድገት መዛባት ያለው ተጋላጭነት በየአገሩ የተለያየ መሆኑ ተስተውሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የኦቲዝም ማኅበር እንዳለው፤ የአእምሮ ዕድገት መዛባትን ለመለየት የታዳጊዎች የንግግር እና የማኅበራዊ ግንኙነት ሁኔታ እንዲሁም ዝንባሌያቸው እና ነገሮችን የመደጋገም ልምድ ይስተዋላል።

ዶ/ር ካሮላይን እንደሚሉት፤ ሴቶች ዕድሜያቸው ከፍ ሲል የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባቸው የሚታወቅበት ምክንያት ተጨማሪ ጥናቶች ይፈልጋል።

"ወንዶች አንድ ነገር ላይ ብቻ የማተኮር እና የመደጋገም ባህሪ ያሳያሉ። ሴቶችም አንድ ነገር ላይ ማተኮር ቢያሳዩም ከተለመደው የወጣ አይደለም። ሴቶች በማኅበራዊ ግንኙት መሰናክል ቢገጥማቸው ለመሸፈን ይችላሉ" ይላሉ።

ሴቶች ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ውስብስብ ማኅበራዊ መስተጋብርን መከወን ሲቸገሩ ምልክቶች መታየት እንደሚጀምሩ ያስረዳሉ።

"ጭንቀት እና ድባቴ የሚገጥማቸው በዚህ ዕድሜ ላይ ነው። ከዚያም ኦቲዝም እንዳለባቸው ይታወቃል" ይላሉ ባለሙያዋ።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የኦቲዝም ማኅበር ዋና የጥናት ባለሙያ ዶ/ር ጁዲት ብራውንም ይሄንን ሐሳብ ይጋራሉ።

"ኦቲዝም ያለባቸው ሴቶች በማኅበራዊ ግንኙት ላይ የሚያሳዩት ልዩነት ብዙም የጎላ አይደለም። የሚታይባቸውን ልዩነትም መደበቅ ስለሚችሉ ኦቲዝም እንዳለባቸው ለማወቅ ያስቸግራል" በማለት ይገልጻሉ።

ወላጆች እና መምህራን የአእምሮ ዕድገት መዛባት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ላይ እንደሚታይ ያምናሉ።

"ኦቲዝም ያለባቸው ወንዶች ናቸው የሚል የተዛባ አመለካከት እና መድልዎ እንዲፈጠር አድርጓል። ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ብቻቸውን መሆን የሚፈልጉ፣ አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ ወይም የንግግር እና የትምህርት ውስንነት ያላቸው ናቸው ተብሎ ይታሰባል" ሲሉ ዶ/ር ጁዲት ይናገራሉ።

እንዲህ ያሉ አመለካከቶች "ሴቶች ኦቲዝም ሊኖርባቸው አይችልም" ወደሚል የተዛባ ዕሳቤ እንደሚወስድ ይናገራሉ።

"ሴቶች ዐይን አፋር ናቸው ወይም በቀላሉ ከሰው አይግባቡም በሚል ሊወሰድ ይችላል" ይላሉ።

ሴት ሕጻናት ከወንዶች ዘግይተው ኦቲዝም እንዳለባቸው ይታወቃል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴት ሕጻናት ከወንዶች ዘግይተው ኦቲዝም እንዳለባቸው ይታወቃል

"ትንሽ የተለየሁ መሆኔ ችግር የለውም"

ቤትሲ የ18 ዓመት ተማሪ ናት። 'አምቢሺየስ አባውት ኦቲዝም' በተባለ ንቅናቄ ውስጥ ወጣቶችን ታማክራለች።

የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባት የታወቀው።

"ሁሌም ይደክመኝ ነበር። ትምህርት ቤት ለመሄድ እቸገር ነበር። ድምጽ በጣም ይረብሸኝ ነበር" ትላለች።

ከዚያ ቀደም ስለ አእምሮ ዕድገት መዛባት ብትሰማም ምልክቶቹ እስከሚባባሱባት ድረስ በሴቶች ላይ ስላለው ተጽዕኖ በትክክል አታውቅም ነበር።

ዶ/ር ጁዲት እንደሚሉት እንደ ቤትሲ ዓይነት ታሪክ ያላቸው ሴቶች ብዙ ናቸው። ከሌሎች የዕድሜ እኩዮቻቸው የተለዩ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

ባለሙያዋ አንዲት ኦቲዝም ያለባት ሴት "ሌላው ሰው ሁሉ እንዴት መኖር እንዳለበት መመሪያ ተሰጥቶት መመሪያውን እየተከተለ ይመስለኛል። እኔ ግን መመሪያው አልደረሰኝም" እንዳለቻቸው ያስታውሳሉ።

የአእምሮ ዕድገት መዛባትን በመለየት ረገድ በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መጥቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአእምሮ ዕድገት መዛባትን በመለየት ረገድ በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መጥቷል

የአእምሮ ዕድገት መዛባት ያለባቸው ሰዎች የሚያሳዩት ልዩ ትኩረት በሴቶች እና በወንዶች ላይ የተለያየ ገጽታ እንዳለው ያስረዳሉ።

የወንዶች ልዩ ትኩረት በጣም ጎልቶ ሲታይ የሴቶች ግን እንደ ሌሎች የዕድሜ እኩዮቻቸው ትኩረት የሚሰጡትን ነገር አጥብቆ መውደድ ሆኖ ይታያል።

ቤትሲ የአእምሮ ዕድገት መዛባት እንዳለባት ሲነገራት ሕይወቷን ለመምራት ቀላል ሆኖላታል።

"ምንም ችግር እንደሌለብኝ አውቄያለሁ። ትንሽ ልዩ ነኝ። ይሄም ችግር የለውም" ትላለች።

ዶ/ር ካሮላይን የአእምሮ ዕድገት መዛባት እና ሴቶች ላይ የሚታይበት መንገድ መጠናት አለበት ይላሉ።

የአእምሮ ዕድገት መዛባት ምልክቶች ሲተነተኑ ሴቶችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።

"ወንዶች የበለጠ ለኦቲዝም ተጋላጭ ናቸው በሚል ጥናቶች በአመዛኙ ወንዶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ምልክቶች የተለዩትም በወንዶች ነው። ሴቶች ላይ ያሉት የተለዩ ምልክቶች በለጋ ዕድሜያቸው መታወቅ አለባቸው" ይላሉ።