ሴቶች በእጅጉ ሊጠነቀቁባቸው የሚገቡት በመነጽሮች በድብቅ የሚቀረጹ ቪዲዮዎች

ጆይ ካሌኪ
የምስሉ መግለጫ, ጆይ ካሌኪ
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ጆይ ካሌኪ በፍቅረኞች (በቫለንታይን) ቀን በጣም የተጨነቀች ከምትመስል ጓደኛዋ የስልክ ጥሪ ደረሳት። ቪዲዮ በበይነ መረብ ላይ በመለጠፉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንድትመለከት ነገረቻት።

ቪዲዮውን አየችው። በወቅቱ የ19 ዓመት ተማሪ የነበረችው ካሌኪ በኬንያ መዲና ናይሮቢ በትራፊክ በተጨናነቀ መንገድ ዳር ብቻዋን ቆማ ስልኳን ስትመለከት የሚያሳይ ነው። የሚቀርጻት ሰው ወደ እሷ እየተጠጋ "ሰላም፣ መልክሽን ወድጄዋለሁ" ይላታል።

ካሌኪ አጋጣሚውን ረስታው ነበር።

"ባለፈው ዓመት ያገኘሁት ሩሲያዊ ሰው መሆኑን ተገነዘብኩ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። ቪዲዮውን ካየችው በኋላ እየቀረጻት እንደነበር ተረዳች።

ግለሰቡ በኬንያ እና በጋና ቀርጾ በበይነ መረብ ላይ ከተለጠፋቸው በርካታ ቪዲዮዎች በአንዱ ላይ ነው ካሌኪ የምትታው።

ፀጉራቸውን ይነካል፣ እጃቸውን ይይዛል፣ ስልክ ቁጥራቸውን ይጠይቅ እና በድጋሚ ለመገናኘት ይጠይቃቸዋል።

ሴቶቹ በወንዶች በሚጠቀሟቸው ድብቅ ካሜራዎች ያለፈቃዳቸው የሚቀረጹበት እና ቪዲዮዎቹ በበይነ መረብ ላይ የሚያሠራጩበት አጋጣሚ ዓለም ሰለባዎች ናቸው። በዚህ መልኩ የተጫኑ አንዳንድ ቪዲዮዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕይታዎችን ያገኛሉ።

አንዳንድ የቪዲዮዎቹ ባለቤቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በመለጠፋቸው ወይም ወንዶች ሴቶችን እንዴት ማነጋገር እንደሚችሉ በቪዲዮዎቹ በማስተማር ገንዘብ እንደሚያገኙበት ይገመታል።

ጉዳዩ በኬንያ እና በጋና የሚገኙ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። ሩሲያዊ ነኝ የሚለው ግለሰብ እንዲታሰር ጥሪ አቅርበዋል።

ሴቶቹም በበይነ መረብ ላይ ወቀሳ፣ ስላቅ እና ስድብ አስተናግደዋል።

ክስተቱ እና የተፈጠረው ሁኔታ "ታዋቂ ሰው እንደመሆን ቢሆንም ግን በጥሩ መልኩ አይደለም" ትላለች ካሌኪ።

በኬንያ የሴት ጠበቆች ፌዴሬሽን (ፊዳ-ኬንያ) የሕግ አማካሪ የሆኑት ብሬንዳ ያምቦ የሕዝቡ ምላሽ ጎጂ የሆኑ የፆታ አመለካከቶችን ከማሳየቱም በላይ ጥፋቱን ወደ ተጎጂዎች የማዞር አሰተሳሰብን ያሳያል ብለዋል።

ያለፍላጎት በመቀረጹ እና በበይነ መረብ ላይ በመጫኑ ላይ ከማተኮር ይልቅ ማኅበረሰቡ የሴቶቹን ባህሪይ ይወቅሳል ይላሉ።

"ስለ ምርጫዎቿ፣ ስለ ሥነ ምግባሯ፣ ስለ አለባበሷ ይነጋገራሉ" ይላሉ። ይህም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንደሚጨምር እና ተጎጂዎች በይፋ ወጥተው መብታቸውን እንዳይጠይቁ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ሰውየው ካናገራት በኋላ ካሌኪ ለመገናኘት የቀረበላትን ግብዣ ውድቅ አድርጋው ነበረ።

የእሷ እና የሌሎች ቪዲዮዎች ግን በቅርቡ ነው መሠራጨት የጀመሩት። የኬንያ እና የጋና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቪዲዮዎቹን ተቀባብለዋቸዋል። አንዳንዶቹ በአገርኛ ቋንቋዎች መጥፎ ጽሑፎችን ጨምረውባትል። ይህም ቪዲዮዎቹ ብዙ ተመልካች እንዲኖራቸው ለማድረግ የተደረገ ግልፅ ጥረት ነው።

የ22 ዓመቱ ኬልቪን ካሩሜ ሥራ አጥ ሲሆን፣ መኖሪያውን በናይሮቢ አድርጓል። የይዘት ፈጣሪ ሆኖ ስሙን ለመገንባት እየሞከረ እንደሆነ የሚናገረው ኬልቪን ቪዲዮዎቹን ከሩሲያ የዩቲዩብ ቻናል ላይ እንዳገኛቸው ተናግሯል።

የ22 ዓመቱ ኬልቪን ካሩሜ

የፎቶው ባለመብት, Kelvin Karume

የምስሉ መግለጫ, ኬልቪን ካሩሜ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንድ እሑድ ዕለት ወደ ቤተክርስቲያን ከመሄዱ በፊት ከቪዲዮዎቹ አንዱን በቲክቶክ ገጹ ላይ እንደለጠፈ ያስታውሳል። ከዚያም ስልኩን ዘጋው።

"ለእኔ ቪዲዮዎቹን መለጠፍ ችግር የለውም ብዬ ይሰማኝ ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች እየፈለጉዋቸው ነበር። እኔ ደግሞ አውርጄዋለሁ" ሲል ካሩሜ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በሁለት ሰዓታት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዕይታን እና ወደ 3,000 የሚጠጉ አስተያየቶችን እንዳገኘ ገልጿል።

ካሩሜ እና ሌሎችም የካሌኪን ቪዲዮ ካጋሩ በኋላ ከቤቷ ስትወጣ አንድ ግለሰብ "ኢንዳ ኡሜዜ ዳዋ" አላት። በስዋሂሊ ቋንቋ ኤችአይቪን ለማከም የሚያውለውን ፀረ-ቫይረስ መድኃኒት እንድትወስድ እየነገራት ነበር።

"አክሎም 'ኡታ ኩፋ ዌዌ' [ትሞቺያለሽ] አለ። በጣም አሳዛኝ ነበር። እየጮኸ ስለነበር ሰዎች ይመለከቱኝ ጀመር" ትላለች።

ካሌኪ ከቪዲዋ ስር አስተያየት ስለተወች እና እንዲያጠፋው ከጠየቀችው በኋላ የእሷን እና የሌላ ሴትን ቪዲዮ ማጥፋቱን ተናግሯል። ቪዲዮው እየተሠራጨ በመሆኑ "በዚህ መልኩ ማጋለጥ" ተገቢ አለመሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህ ቢሆንም ግን ያለፈቃዳቸው የተቀረጹ የሁለት ሌሎች ሴቶች ቪዲዮዎች አሁንም በገጹ ላይ ይገኛሉ።

ማንም ቅሬታ ስላላቀረበ እና ቪዲዮዎቹ እንደሌሎቹ ትኩረት ባለማግኘታቸው የሌሎቹን ቪዲዮዎች መሰረዝ አስፈላጊ ሆኖ እንዳላገኘው ካሩሜ ተናግሯል።

ተጨማሪ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ቪዲዮዎቹን በድጋሚ መጫን ሲቀጥሉ የኬንያው የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (ዲሲአይ) መግለጫ አውጥቷል። ስምምነት ያልተደረገባቸውን ቪዲዮዎች እንደገና ማጋራት ሁለተኛ ጉዳት በመሆኑን ወደ ወንጀል ክስ ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የጋና ባለሥልጣናት ቪዲዮዎቹን የቀረጸው ግለሰብ የ36 ዓመቱ ቭላዲላቭ ሊዩልኮቭ መሆኑን ተናግረዋል። የፓስፖርት ፎቶውንም አሠራጭተዋል።

በበይነ መረብ ደኅንነት ሕጎቻቸው መሠረት ክስ ለመመሥረት እና ወደ ጋና እንዲመጣ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ግልሰቡ ግን የት እንዳለ አይታወቅም።

በቪዲዮዎቹ ውስጥ በአንዳቸውም ላይ የሰውየው ፊት ስለማይታይ ካሌኪን ያገኛት ግለሰብ ሊዩልኮቭ ስለመሆኑ ለመለየት አስቸጋሪ ነው።

ግለሰቡ ከቀረጻቸው ውስጥ ሦስቱን በናይሮቢ በሚገኙት ሳሪትሴንተር እና ቲአርኤም ሞል መሆኑን ታውቋል። ሌሎቹ ደግሞ በባሕር ዳርቻዋ ሞምባሳ ከተማ በሚገኘው ኛሊ ሞል መሆኑ ተረጋግጧል።

በጋና ውስጥ ደግሞ አንዳንዶቹ ሴቶች በዋና ከተማዋ በሚገኘው አክራ ሞል አቅራቢያ ነው የተቀረጹት።

ከቪዲዮዎች የሚሰማው ድምፅ በጣም ተመሳሳይ ሲሆን፣ ፊቱ ባይታይም ክንዱ ላይ ሰማያዊ የካሲዮ ሰዓት አስሯል።

በአንዳንድ ቪዲዮዎች ላይ ሁለቱም እጆች በግልጽ ስለሚታዩ ካሜራ እንዳልያዘ ያሳያል።

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች በጋና የምትኖር አንዲት ሴት ለቢቢሲ ፒድጂን እንደገለጸችው ግለሰቡ በጥር ወር እንዳያት እና ሊያገኛት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋዋለች።

በመስመር ላይ ስለተደረገው ማንኛውም ቀረጻ ምንም አይነት መረጃ አታውቅም፣ ነገር ግን በቪዲዮዎቹ ውስጥ ያለው ሰው ተመሳሳይ እንደሆነ ታምናለች።

"እነዚያን ቪዲዮች ሳያቸው ያሳዝነኛል። ያላፈውን ነገር ያስታውሰኛል ይሰጠኛል። እኔም ሊሆን እችል ነበር" ትላለች።

በሩሲያ የፍቅር ጓደኛ ማፈላለጊያ መተግበሪያ ላይ ሊዩልኮቭን የሚመስሉ ፎቶግራፎችን የያዙ ሰዎችን አግኝተናል። ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው ግለሰብ ቪዲዮዎቹን ከቀረጸው ሰው ጋር በጣም ተመሳሳይ የሆነ ሰማያዊ ሰዓት አስሮ ይታያል።

በሚያዝያ 2025 በተለጠፈ ፎቶው ደግሞ የሜታን ሬይ ባን የተባለውን ቪዲዮ የሚቀርጽ መነጽር እና በተለምዶ በምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ የሚገኝ ኮፍያ ለብሶ ይታያል። ከሞምባሳ ውጭ በምትገኘው በምትዋፓ ከተማ ከሚገኝ መስጊድ ውጪ ቆሞ የተነሳው ፎቶ ነው።

ሊዩልኮቭን ቪዲዮ መቅረጽ የሚችል መነጽር አድርጎ

የፎቶው ባለመብት, Photo via Fotostrana.ru

የምስሉ መግለጫ, ሊዩልኮቭን ቪዲዮ መቅረጽ የሚችል መነጽር አድርጎ

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ቪዲዮዎቹ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉት የወንድ ብልትን እና ክብር ከሚሉ የሩሲያ ቋንቋ የተጣመሩ ቃላትን በመጠቀም ነው።

በተመሳሳይ ስም ሚገኝ ድረ ገጽ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ጠፍቷል። በድረ ገጹ ላይ ሴቶችን ለመቅረብ የሚያግዙ መንገዶችን በ250 ሩብል (3 ዶላር ገደማ) እንደሚሸጥ ይገልጻል።

ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ተሰባሰቡ ቪዲዮዎችም ተመሳሳይ ስም ባለው ገጽ ላይ ተሠራጭቷል።

በአንደኛው ላይ ተመሳሳይ የአነጋገር ዜዬ እና ሰማያዊ ሰዓት ያለው ሰው ኩባ ውስጥ ከሁለት ሴቶች ጋር ሲነጋገር ይታያል።

ቢቢሲ ሊዩልኮቭን ስለጉዳዩ ቢጠይቀውም ምንም የማኅበራዊ ሚዲያ እና ድረ-ገጽ እንደሌለው አሳውቋል። በኬንያ፣ በጋና ወይም በኩባ ስማርት መነጽር ተጠቅሞ ሴቶችን በመቅረጽ አለመለጠፉን ተናግሯል።

ለሩሲያው የሚዲያ ተቋም ቮት ታክ በኬንያ እና በጋና ሴቶችን ማግኘቱን አምኖ ነገር ግን እንዳልቀረጻቸው አሳውቋል።

በኬንያ እና በጋና በአብዛኛው በበይነ መረብ ላይ የተሰጠው አስተያየት በሴቶቹ ባህሪ ላይ ያተኮረ ሲሆን የማሾፍ፣ የስድብ ቃላትን እና ተጎጂዎች አለመሆናቸውን የሚገልጹም ይገኙባቸዋል።

ካሌኪ ስለ እሷ የተነገረውን ለመቃወም ስለደረሰባት መከራ በይፋ እየተናገረች እንደሆነ ገልጻለች።

ለመደበቅ ብትሞክርም ነገር ግን "እኔ ጠንካራ ነኝ። አንድ ሰው በተናገረው ነገር ምክንያት እዚህ መቆየት የለብኝም" ብላ አሰበች።

"በግድየለሽነት መጻፍ የምትችለው ያ ትንሽ አሉታዊ አስተያየት የአንድን ሰው ሕይወት እንዴት ሊነካ እንደሚችል አያውቁም" ብላለች።