ከ50 ዓመታት በላይ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በባልደረቦቻቸው ሲታወሱ

አምባሳደር ቆንጂት

የፎቶው ባለመብት, au

የምስሉ መግለጫ, ከ50 ዓመታት በላይ በዲፕሎማትነት አገራቸውን ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መድረክ ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ መጋቢት 26/2018 ዓ.ም. አርፈዋል።

አምባሳደር ቆንጂት የዲፕሎማሲውን መስክ የተቀላቀሉት በ1950ዎቹ መሆኑን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በ1932 ዓ.ም. ሐረር ውስጥ የተወለዱት አምባሳደሯ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከእህታቸው ጋር ወደ ለንደን በማቅናት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከዚያ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ለማጥናት ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከእንግሊዝ አገር ተመርቀው መጥተው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ለመቀጠር የገጠማቸው ተግዳሮት ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወቅቱ የነበሩትን ሚኒስትር ለቀናት ተመላልሰው እንዲቀጥሯቸው ቢጠይቁም "በወቅቱ ሴት የምትገባበት የሥራ መስክ አልነበረም" ብለው ስለሚያስቡ በቶሎ ምላሽ አለማግኘታቸውን አምባሳደር ታደለች ያስታውሳሉ።

አምባሳደር ቆንጂት ያለመታከት እየተመላለሱ ሚኒስትሩን መልስ እንዲሰጧቸው በመጠየቃቸው ኋላ ላይ "ውይ ይህች ችኮ ትቀጠር" ብለው ሚኒስትሩ መወሰናቸውን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ቆንጂት አምባሳደር ለመሆን ረዥም ዓመታት መጠበቅ ግድ እንደሆነባቸው አምባሳደር ታደለች ይናገራሉ።

በወቅቱ የአምባሳደር ቆንጂት ያጠኑት ትምህርት ዓለም አቀፍ ግንኙነት የነበረ ቢሆንም ሴት በመሆናቸው ብቻ ከፍተኛ ተግዳሮትን መጋፈጣቸውን ይናገራሉ።

ከተቀጠሩም በኋላ ቢሆን ሴት በመሆናቸው ብቻ በሥራው ለማስቀጠልም ሆነ አምባሳደር አድርጎ ለመሾም "ወጣት ናት፤ ልጅ ናት፤ ሴት ናት ደግሞ አግብታ አርግዛ" በሚል ሰበቦች "ምናልባት ውጭ ጉዳይ ከተቀጠሩ ሰዎች ወደ አምባሳደር ደረጃ ለመድረስ እጅግ ብዙ ጊዜ የወሰደባቸው እርሳቸው ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ የአገሪቱ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር በመሆን አገራቸውን ያገለገሉ እንደነበሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኦቶዋ ካናዳ ኢትዮጵያ ኢምባሲ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋናው መሥሪያ ቤት በአፍሪካ እና በሌሎች ክፍሎች ውስጥ በጋራ መሥራታቸውን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና "የማስታውሳቸው ለአገራቸው ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ነው" ይላሉ።

በአገር ጉዳይ "ቆቅ" የሆኑት ዲፕሎማት

ለ52 ዓመታት ኢትዮጵያን በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት የሙያ አጋሮቻቸው "ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ" በማለት ይጠሯቸዋል።

በአፍሪካ ኅብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን አገራቸውን አግለግለዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም፣ ኢጋድ ውስጥ ደግሞ ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም. ድረስ የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ልዩ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በነበራቸው ልምድ፣ ባካበቱት ልምድ በጣም ትንንሽ ነገሮች አንጥረው ማየት ይችላሉ ያሉት ደግሞ አምባሳደር ታደለች ናቸው።

ከእርሳቸው ጋር የሚሠራ ዲፕሎማት በሚያዘጋጀው የጽሑፍ ረቀቂ ላይ የሚሠራው ስህተት ቢኖር "አበጥረው ስለሚመለከቱ" የሚያልፍ ነገር አለመኖሩንም ይጠቅሳሉ።

ከ50 ዓመት በላይ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሰነድን ሲመለከቱ የኖሩ ዲፕሎማት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ አምባሳደር ቆንጂት በተለያዩ ጊዜያት የተላለፉ ውሳኔዎቸን በማስታወስ ረገድ "ራሳቸው መጽሐፍ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ጀምሮ የነበረውን የዲፕሎማሲ ሂደት ያውቃሉ ያሉት አምባሳደር ታደለች "እንደ ወጣት ዲፕሎማት ምን ይደረግ እንደነበር። ውሳኔዎች ለምሳሌ ከአገሮች ዕይታ ውጪ እንዴት ገብተው ሊያልፉ እንደሚችሉ በጣም ማየት ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማት ሲበረከትላቸው
የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ቆንጂት ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማት ሲበረከትላቸው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአፍሪካ አንድነት ውስጥ ሲሠሩ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የድርጅቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ መውጣት አለበት በሚሉበት ወቅት "አገር በደከመበት ሰዓት እንዴት ነገሮች ሊያልፉ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ነቅተው የሚጠብቁ ቆቅ ነበሩ ማለት ይቻላል" ሲሉ የነበራቸውን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።

አምባሳደር ቆንጂት "በጣም ጥንቁቅ ናቸው። ከመጠን በላይ ጥንቁቅ ናቸው" ያሉት አምባሳደር ታደለች ይህ ከእርሳቸው የሚያስታውሱላቸው ነገር መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና ክብርት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ "የኢትዮጵያን ጥቅም በዲፕሎማሲ መስክ ለማስከበር ቁርጠኛ ናቸው። ይህንን እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የኤምባሲው አባላት በሙሉ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብሩ ያላቸው ግፊት በጣም ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

አምባሳደር ዲና አክለውም "ከሁሉ በላይ ሠርተው የማይጠግቡ ናቸው" በማለት ጠንካራ ሠራተኝነታቸውን መስክረዋል።

አምባሳደር ቆንጂት "ለአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም፣ ለዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮል እና ለሕግ የበላይነት የማይናወጥ አቋም" እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አምባሳደር ቆንጂት "ለበርካታ ዲፕሎማቶች አርዓያ" እንደነበሩ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ላይ "አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በታማኝነት፣ በልዩ ብቃት እና ለጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ባላቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት የታወቁ፣ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ዕሴቶች መገለጫ ነበሩ" ብለዋቸዋል።

አክለውም "የእሳቸው አርዓያነት ለቀጣዩ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች፣ በተለይም ለሴቶች፣ በድፍረት፣ በልዩነት እና በዓላማ እንዲያገለግሉ መነሳሳትን መፍጠሩን ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

ሌሎችን ለማስተማር የማይታክቱት ዲፕሎማት

አምባሳደር ታደለች ወጣት ዲፕሎማቶች ከአምባሳደር ቆንጂት በቅድሚያ መማር ያለባቸው "መንግሥትን እና አገርን መለየት መቻል እንዳለባቸው ነው" ይላሉ።

"የአገርን ጥቅም ማዕከል አድርጎ መሥራት" ከእርሳቸው መማር የሚገባ መሆኑን የሚናገሩት አምባሳደር ታደለች፤ ምንጊዜም ከመንግሥት ጥቅም ይልቅ "የአገር ጥቅም" መቅደም እንዳለበት ከእርሳቸው መማር ያለባቸው ትምህርት መሆኑን ይናገራሉ።

አምባሳደር ዲናም በበኩላቸው አምባሳደር ቆንጂት የሚያውቁትን ለሌሎች በማስተማር ረገድ የማይታክቱ ዲፕሎማት ነበሩ ብለዋል።

"ሁልጊዜም ሰው በዲፕሎማሲ መስክ አተኩሮ መሥራት አንዳለበት ነው የሚሞግቱት። ስለ ዲፕሎማሲ ሥነምግባር፣ ስለ ፕሮቶኮል . . . ከአለባበስ፣ ከአነጋገር፣ ከአካሄድ ጀምሮ ምን ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቀው የሚያውቁትን ለእያንዳንዱ ዲፕሎማት የማስገንዘብ የማስጨበጥ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ነበሩ" ብለዋል።

አምባሳደር ዲና አክለውም አምባሳደር ቆንጂትን "ትልቅ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት. . . ትልቅ የክፍለ ዘመኑ ዲፕሎማት" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ሆነው በርካታ ዓመታት የሠሩት አምባሳደር ቆንጂት ከዚያ በኋላ ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆነው ሠርተዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኅብረት በወከሉበት ወቅት "የአፍሪካውያን ሪፎርም በማጠናከር ረገድ አፍሪካ ጠንካራ ክፍለ አህጉር ሆና ለአፍሪካውያን ተሟጋች እንድትሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካ ሚናዋ ከፍ እንዲል ከሌሎች የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጋር ሆነው ከፍተኛ አመራር" መስጠታቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በዲፕሎማትነታቸው ዘመን ሁሉ "ለለውጥ፣ ለሥራ፣ ለውጤት ሁሉም እንዲተጋ. . . ሙያዊ ግፊት" ያደርጉ አንደነበር አምባሳደር ዲና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና አምባሳደር ቆንጂት ለዘመናት ማኅበረሰቡ ውስጥ የኖረውን ለሴቶች ዕድል መንፈግ በመስበር ወደፊት በመውጣት ለሴቶች አርዓያ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

ከአምባሳደር ዮዲቱ እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የሴት አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ቆንጂት "አሁን እየተተገበረ ላለው የፆታ እኩልነት የእርሳቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ሌሎች ሴቶችን ወደፊት በማምጣት ረገድ የሚጫወተው ሚናም ቁልፍ ነው" ብለዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በዲፕሎማሲው መስክ ለአገራቸው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ለአገራቸው በሰጡት አገለግሎት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እጅ የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋ።