የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት ተራዘመ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት የሥልጣን ዘመናቸው የሚጠናቀቀውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ ሹመትን ለአንድ ተጨማሪ ዓመት አራዘሙ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ሥልጣን መራዘሙን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 30/2018 ዓ.ም. ባወጣው አጭር መግለጫ ነው።

መግለጫው እንደሚያስረዳው የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን ከነገ ሐሙስ ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የተወሰነው ማክሰኞ ዕለት ከተደረገው የክልሉ ዓመታዊ አፈጻጸም ግምገማ እና ውሳኔ በኋላ ነው።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ማክሰኞ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተገኝተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ዓመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት" እንዳቀረቡ እና "በውጤቶቹ ላይ ግምገማ እና ውይይት" እንደተደረገ ተገልጾ ነበር።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።

በዚህ ውይይት ወቅት ምን ጉዳዮች እንደተነሱ በዝርዝር አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቲቪ እና ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያለው ፋና ቴሌቪዥን ትናንት ያወጡት ዘገባ ያተኮረው በትግራይ ክልል የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ ነው።

ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ባስተላለፉት ተመሳሳይ ዘገባ በክልሉ የሚሰማው "የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ መሬት ላይ ያለውን የልማት ሥራ" እንደሸፈነው በመጥቀስ በተለያዩ ዘርፎች ተገኝተዋል ያሏቸውን ስኬቶች ዘርዝረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የሌተናንት ጄነራል ታደሰ የሥልጣን ዘመን የተራዘመው የፌደራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ መሠረት ነው።

በትግራይ የተካሄደው የሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም የወጣው እና 2015 ላይ የተሻረው ደንብም ተጠቅሷል።

የመጀመሪያው ደንብ ቢሻርም ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም. የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ ማውጣቱ ይታወሳል።

ይህ ደንብ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር "በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ" በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሾም ደንግጓል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ፤ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ክልሉን ሲመሩ ከነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ሥልጣኑን የተረከቡት ባለፈው ዓመት በዚሁ ዕለት መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. ነበር።

ታደሰ ትግራይ ክልል እንዲመሩ የተሾሙት የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በሚያስችል ሁኔታ ተሻሽሎ ነው። በአዋጁ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን ሁለት ጊዜ ከአንድ ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ መራዘም ይችላል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ  ሪፖርት ያቀረቡበት ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ የሚራዘመው "በክልሉ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ካደረገው ሁኔታ ውስብስብነት አኳያ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ" እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

አዋጁ ይህንን የቆይታ ጊዜ የማራዘም ሥልጣን የሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ነው። አፈ ጉባኤው አገኘሁ ተሻገር የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ በድጋሚ እንዲራዘም ውሳኔ ስለማሳለፋቸው እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

በዚህ አዋጅ ላይ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ አፈ ጉባኤው በሚያስተላልፉት ውሳኔ ላይ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሊመላከቱ" የመቻሉ ጉዳይ ነው። ታደሰ ባለፈው ዓመት ላይ ሥልጣኑን ሲረከቡ በስምንት ጉዳዮችን ለመፈጸም ቃል የገቡበትን ሰነድ መፈረማቸው ይታወሳል።

"ከሕገ መንግሥቱን" እና "ከሀገር ሉዐላዊነት"፤ "ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ" እንዲሁም የቀድሞ ታጣቂዎች "ትጥቅ መፍታት" እና "መልሶ መቋቋም" ተግባር "በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ የማድረግ" ከተጣሉባቸው ኃላፊነቶች መካከል ናቸው።

ትግራይ ክልልን "ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ" ማድረግ እንዲሁም "የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ" ተግባር "እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር" የማድረግ ጉዳዮችም ተካትተዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በትናንትናው ዕለት የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ እና መግባባት ላይ ተደርሶ እንደሆነ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ከቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የሰፈሩት ዋነኛዎቹ ተግባራት ተሳክተዋል ለማለት አስቸጋሪ ነው።

በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አልተመቻቹም። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በትግራይ "አስቻይ ሁኔታ ባለመፈጠሩ" በክልል ሊያደርግ የነበረውን "የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች ልየታ መድረክ" በአዲስ አበባ አካሂዷል።

እንደ ወልቃይት ወዳሉ አካባቢዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራም ይሄ ነው የሚባል እርምጃ አልተወሰደበትም። ይልቁንም በፌደራል እና ትግራይ ኃይሎች ክልሉን ከአማራ እና አፋር ጋር በሚያዋስኑ ስፍራዎች ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።

የፌደራል መንግሥት ለትግራይ የሚሰጠው የድጎማ በጀት እንዲሁም ወደ ክልሉ መድረስ የነበረበት የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል።