አንድ ጉንዳን በ220 ዶላር የሚሸጥበት ዓለም አቀፍ ጥቁር ገበያ

የፎቶው ባለመብት, Dino Martins
ጉንዳኖች በኬንያ ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆኑ ሰነባበተ። በዝናባማ ወቅት እንደ ጊልጊል ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ጉንዳኖች አብዝተው ይንቀሳቀሳሉ።
በሺዎች የሚቆጠሩ የጉንዳን ጉብታዎች (anthills) መመልከትም የተለመደ ነው።
ጊልጊል አርሶ አደሮች የሚበዙበት የሪፍት ቫሊ አካባቢ ነው። የሕገ ወጥ ጉንዳን ዝውውር ማዕከል ሆኗል።
ወንዶቹ ጉንዳኖች አነስተኛ ክንፍ ሰውነታቸው ላይ ይታያል። ሴቶች ጉንዳኖች እንቁላል የሚፈለፍሉት ወቅት ነው።
በዚህ ወቅት ንግሥት ጉንዳኖችን የሚያድኑ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ይሰማራሉ። ሕገ ወጥ የጉንዳኖች ሽያጭ ዓለም አቀፍ ሰንሰለት አለው።
በንግሥት የሚመሩት ጉንዳኖች ሥራ የሚያከናውኑበት እና ኑሮ የሚገፉበት ማኅበራዊ መዋቅር (ant colony) አላቸው። ይሄንን ተፈጥሯዊ ትዕይንት መመልከት የሚሹ ሰዎች በሕገ ወጥ ገበያ ጉንዳኖችን ይሸምታሉ።
ጉንዳኖቹ ከተያዙ በኋላ በጠርሙስ ማስቀመጫ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል። በጠርሙሱ ሳሉ ማኅበራዊ መዋቅራቸውን ሲገነቡም ይታያል።
አፍሪካ የሚኖሩ ግዙፍ የጉንዳን ንግሥቶች ቀይ ቀለም አላቸው። በዓለም አቀፍ ገበያ በስፋት ተፈላጊ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ።
በጥቁር ገበያ አንድ ንግሥት ጉንዳን እስከ 220 ዶላር ይሸጣል።
አንድ እንቁላል የምትጥል ንግሥት መላውን የጉንዳን ማኅበራዊ መዋቅር መገንባት ትችላለች።
በአንድ ወቅት የጉንዳን ሽያጭ ደላላ የነበረ ግለሰብ "ሕገ ወጥ መሆኑን አላውቅም ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የውጭ አገር ገዢዎችን ከአገር ውስጥ ጉንዳን አዳኞች ጋር ያገናኝ ነበር።
በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኙት የጉንዳን ዓይነቶች (Messor cephalotes) በተለየ የሚታወቁት ጥራጥሬ በመሰብሰው ነው። የጉንዳን ሰብሳቢዎችን ትኩረትም የሳቡት ለዚህ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢቢሲ ያነጋገረው የቀድሞ ደላላ "አንድ የውጭ ዜጋ ንግሥት ጉንዳኖችን በከፍተኛ ዋጋ እየገዛ መሆኑን ነገረኝ። እዚህ አካባቢ ደግሞ በቀላሉ ይገኛሉ" ብሏል።
ጠዋት ላይ የጉንዳኖቹን ጉብታ ማግኘት እንደሚቻል ይናገራል። የውጭ አገራት ዜጎች ቦታው ድረስ ጉንዳኖቹን አይሰበስቡም።
ከተማ አቅራቢያ ሆነው ሆቴል በመከራየት ጉንዳኖቹ እስከሚያመጡላቸው ይጠብቃሉ።
"መኪና ውስጥ ሆነው ይጠብቃሉ። ጉንዳኖቹን በትንሽዬ ቱቦ ውስጥ አድርገን እንወስድላቸዋለን። አንዳንዴም ጉንዳኖቹን የምናስቀምጥበት የመርፌ ሲሪንጅ ይሰጡናል" ይላል የቀድሞው ደላላ።
ባለፈው ዓመት ጊልጊል አቅራቢያ በሚገኘው ናይቫሻ ከተማ አካባቢ 5,000 ንግሥት ጉንዳኖች በአንድ ሆቴል ክፍል ተገኝተዋል። ሕገ ወጥ የጉንዳኖች ዝውውር ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ የታወቀውም በዚህ አጋጣሚ ነበር።
የኬንያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ እንዳለው ተጠርጣሪዎቹ የቤልጂየም፣ የቬትናም እና የኬንያ ዜጎች ናቸው።
የመርፌ ሲሪንጅን በእርጥብ ጥጥ ይሞሉና ጉንዳኖቹን በውስጡ ይከታሉ። ይሄ ዘዴ ጉንዳኖቹ እስከ ሁለት ወር በሕይወት እንዲቆዩ ይረዳል።
ጉንዳኖቹ ወደ አውሮፓ እና እስያ ተወስደው ሊሸጡ ነበር። ሕገ ወጥ የጉንዳኖች ዝውውር ሳይንቲስቶችን እና ባለሥልጣናትም አስደንግጧል።
በምሥራቅ አፍሪካ እንደ ዝሆን እና አውራሪስ ያሉ እንሰሳት ለሕገ ወጥ ግብይት ተጋላጭ ናቸው። የጉንዳኖች ሽያጭ ግን ያልተጠበቀ ሆኗል።
ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው 'አንትስ አር አስ' መደብር እንደሚለው የአፍሪካ ጉንዳኖች በከፍተኛ መጠን ይፈለጋሉ።
ንግሥት ጉዳንኖችን ማግኘት ቀላል ስላልሆነ ብዙውን ጊዜ በቶሎ ከገበያ ያልቃሉ።
መደብሩ የአፍሪካ ጉንዳኖች "ብዙዎች የሚፈልጓቸው ናቸው" ይላል።
የሥነ ሕይወት አጥኚ ዲኖ ማርቲንስ "ሥራዬ ነፍሳትን ማጥናት ቢሆንም የጉንዳኖች ሽያጭ አስደንቆኛል" ይላል።
በኬንያ ወደ 600 የሚጠጉ የጉንዳን ዓይነቶች እንዳሉ ባለሙያው ይናገራል።
በጥቁር ገበያ እየተሸጡ ያሉት ንግሥት ጉንዳኖች እስከ 25 ሚሊሜትር ይረዝማሉ። አንድ ንግሥት ሙሉ ሕይወቷን እንቁላል ትፈለፍላለች።
"በጣም አስደናቂ የጉንዳን ዓይነት ናቸው። ትልልቅ የጉንዳኖች ቡድን ይገነባሉ። አስገራሚ ባህሪ ያሳያሉ። ሰዎች ስለማይተናኮሉ አብሮ መኖር ይቻላል" ሲል ዲኖ ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, KWS
ንግሥት ጉንዳኖች ከብዙ ወንድ ጉንዳኖች ጋር ግንኙነት ይፈጽማሉ። ከዚያ በኋላ ወንዶቹ "ሥራቸውን ይጨርሳሉ። ወይ ይሞታሉ፤ አልያም ይበላሉ" ይላል ባለሙያው።
ንግሥቷ ጉንዳን ከዚያ በኋላ እንቁላሎች ፈልፍላ ግዛቷን ታስፋፋለች።
ግዛቱን የሚጠብቁት እና ሥራ የሚያከናውኑት ሴት ጉንዳኖች ናቸው። ሴቶቹ ጉንዳኖች እስከ መቶ ሺዎች ይደርሳሉ።
"ጎጇቸው እስከ 50 ወይም 70 ዓመታት ይኖራል። ናይሮቢ አቅራቢያ 40 ዓመት ያስቆጠሩ ጎጆዎችን እጎበኛለሁ" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ንግሥት ጉንዳን ከሞተች ግዛቷ ይፈርሳል። ሠራተኞቹም ሌላ የሚኖሩበት ግዛት ይፈልጋሉ።
ጉንዳኖች ሰብላቸውን የሚወሩባቸው ኬንያውያን አርሶ አደሮች የጉንዳን ግዛቶችን ያወድማሉ።
በጎጆው ውስጥ ተደብቃ የምትኖረውን ንግሥት ጉንዳንም ፈልገው ያጠፋሉ።
ጉንዳኖች ጎጇቸው ሲነቀነቅ ለማምለጥ ሲሞክሩ መያዝ እንደሚቻል የቀድሞው የጉንዳን ደላላ ለቢቢሲ ገልጿል።
"ሰዎች መታሰራቸውን ዜና ላይ ስመለከት ሥራውን አቆምኩ" ይላል።
በጉንዳን ዝውውር የተከሰሱት ሰዎች ካሳ እንዲከፍሉ እና 12 ወራት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸዋል። 7,700 ዶላር ካሳ እንደሚከፍሉ ተገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ከኬንያ እንዲወጡም ተደርጓል።
የጉንዳን ዝውውሩ ዋነኛ አቀነባባሪ የነበረ ቻይናዊ ከኬንያ በሌላ ፓስፖርት አምልጦ ነበር። ከሰሞኑ ግን 2,000 ንግሥት ጉንዳኖች በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ይዞ ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና ላይ በማተኮር ስለ ጉንዳን ንግድ በአውሮፓውያኑ በ2023 ጥናት በሠራው ቡድን ውስጥ የሚገኘው ዤንጋያንግ ዋንግ "የጉንዳኖች መሸጥ ብዝኃ ሕይወቱን ያላላዋል" ይላል።
በሺንሹን ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነው ባለሙያው እንደሚለው ጉንዳኖች በመስታወት ሳጥን ውስጥ ተቀምጠው እንዲኖሩ ይደረጋል።
ሥራቸውን ሲያከናውኑ ለማየት የሚያስችል ነው።
"ጉድጓድ ሲቆፍሩ፣ ድልድይ ሲሠሩ፣ ምግብ ሲሰበስቡ እና ንግሥታቸውን ሲጠብቁ ይታያሉ። ስለ ጉንዳኖች ባህሪ እና አኗኗር ለማወቅ እንዲሁም ለማጥናት ጥሩ መንገድ ነው" ሲል ያብራራል።
ሆኖም ግን እንሰሳቱን በዚህ መንገድ ማኖር ጎጂ እንደሆነ በጥናታቸው ደርሰውበታል።
በቻይና በስድስት ወራት ውስጥ ከ58 ሺህ በላይ የጉንዳን ቡድኖች ለገበያ ቀርበዋል። ከእነዚህ ጉንዳኖች አንድ አራተኛው ዝርያቸው በቻይና የማይገኙ ናቸው።
ጉንዳኖችን ወደ ቻይና ማስገባት ሕገ ወጥ ነው።
"ጉንዳኖችን የሚጎዳው ንግድ ከቀጠለ ከመኖሪያ ቦታቸው እየሸሹ ደን ውስጥ መኖር ይጀምራሉ" ይላል ዤንጋያንግ።
የምሥራቅ አፍሪካ ንግሥት ጉንዳኖች በቻይና በዋነኛነት ይሸጣሉ።
እነዚህ ጉንዳኖች ከተለያዩ ዕጽዋት ዝርያዎችን በመሰብሰብ በዓለም ቁጥር አንድ የጉንዳን ዝርያ ናቸው።
በዚህ ምክንያትም በምሥራቃዊ ቻይና የሰብል ግብርና ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ያስረዳል።
በኬንያ የአካባቢ ጥበቃ ላይም ጫና ያሳድራል።
"ዝርያ የሚሰበስቡ ጥቃቅን ነፍሳት ብዝኃ ሕይወትን ያስጠብቃሉ። የሳር እና የሌሎችም ዕጽዋት ዝርያዎችን ይበትናሉ። ጉንዳኖቹን መሸጥ ይሄን ያዛባል" ሲል የሥነ ሕይወት ተመራማሪው ዲኖ ያስረዳል።
በኬንያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ እና ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆነው ሙኮኒ ዋታይ "ንግሥት ጉንዳኖችን ከግዛታቸው ማስወጣት ብዝኃ ሕይወቱን ያዛባል" ይላል።
ልዩ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ዓለም አቀፍ ስምምነትን ተከትለው ከኬንያ ጉንዳኖች መሰብሰብ ይችላሉ።
ይህም ጉንዳኖቹ ለሚገኙበት አካባቢ ማኅበረሰብ ትርፍ ማጋራትን መሠረት ያደረገ አሠራር ነው።
የኬንያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ እንደሚለው ግን እስካሁን ድረስ ስምምነቱ አልተተገበረም።
ምን ያህል ጉንዳኖች እንደተሰበሰቡ እና የት እንደሚሄዱ ግልጽ መረጃ አለመገኘቱ አንደኛው ምክንያት ነው።
አደጋ የተጋረጠባቸውን እንሰሳት በሚጠብቀው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት ጉንዳኖች ከለላ እንዲያገኙ የተፈጥሮ ሃብት ተሟጋቾች እየጠየቁ ነው።
የዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነት አጥኚ ሰርጊዮ ሄንሪኬስ "በዚህ የጥበቃ ዝርዝር ውስጥ የተካተተ አንድም የጉንዳን ዝርያ የለም" ይላል።
ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሌለ የጉንዳኖቹን ዝውውር እና ሽያጭ መቆጣጠር አይቻልም።
የኬንያ የዱር ጥበቃ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ የተሻለ ፍተሻ የሚደረግበት መንገድ ተዘርግቶ የጉንዳን ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲቻል ይፈልጋል።
የሥነ ሕይወት ባለሙያው እንደሚናገረው በሕገ ወጥ መንገድ ከሚዘዋወሩ ጉንዳኖች መካከል በቁጥጥር ሥር የሚውሉት ውስን ቁጥር ያላቸው ናቸው።
"አሁን ማንም ሰው ትክክለኛውን ቁጥር መገመት አይችልም" ይላል።
ጋዜጠኛ ቻርልስ ኦንያንጎ-ኦቦ በበኩሉ ኬንያ ከዓለም አቀፍ ገበያ የምታገኘውን ትርፍ ማሰብ አለባት ሲል ይከራከራል።
"ጉንዳኖች እንደ ወርቅ ወይም አልማዝ አያልቁም። የሥነ ሕይወት ሃብት ናቸው። ጉንዳኖችን ማራባት ይቻላል። በአንድ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ጉንዳኖች ይራባሉ/ይዋለዳሉ። ጉንዳኖችን እንደተሰረቀ ቅርስ መውሰድ የለብንም" ይላል።
የኬንያ ምክር ቤት ጉንዳኖችን ጨምሮ የዱር እንሰሳት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡበትን ፖሊሲ ባለፈው ዓመት አጽድቋል።
ጉንዳኖችን በተገቢው መንገድ በመነገድ ገቢ ለማግኘት ያለመ ሲሆን፣ ማኅበረሰብንም በገንዘብ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
ቁጥጥር የሚደረግበት የጉንዳን ንግድ በጊልጊል ለውጥ ማምጣት ይችል ይሆናል። በከፍተኛ ገንዘብ የሚሸጡ ንግሥት ጉንዳኖችን በአትክልት እና ፍራፍሬ አካባቢ ማራባት አንደኛው መንገድ ነው።















