የካሜሩን ፕሬዝዳንት በ43 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንት ሊሾሙ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በዕድሜ ትልቁ የዓለም መሪ የሆኑት የካሜሩን ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ፤ በፓርላማ የድጋፍ የጸደቀውን አወዛጋቢውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተከትሎ ለአራት አስርት ዓመታት በቆየው የሥልጣን ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንት ሊያገኙ ነው።
የ93 ዓመቱ ቢያ አንድ ነገር ቢሆኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት መንበሩን ተረክበው የሥልጣን ዘመኑን ያጠናቅቃሉ።
የምክትል ፕሬዝዳንቱ ቦታ የተሰረዘው በአውሮፓውያኑ 1972 ነበር። ከዚህ ቀደም የሴኔት መሪው አዲስ ምርጫ እስኪከናወን ድረስ ፕሬዝዳንት ሆነው እንደሠሩ ይጠበቅባቸው ነበር።
ተቃዋሚዎች ማሻሻያዎቹ በችኮላ የተዘጋጁ እና ሥልጣንን ለማጠናከር የታለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። አንድ የቢያ ፓርቲ ሴናተር ጭምር ሂደቱን "አጠራጣሪ" ሲሉ ገልጸውታል።
የቢያን የጤና ሁኔታ በተመለከተ ተደጋጋሚ ግምቶች ሲነገሩ ቢቆዩም በግልጽ ውይይት አልተደረገባቸውም። ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ለረዥም ጊዜ ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው ከቆዩ በኋላ ብቅ በማለት ስለሞታቸው የሚዘዋወሩ ወሬዎችን ያጣጥላሉ ያደርጋሉ።
ቅዳሜ ዕለት የሁለቱም የፓርላማ ምክር ቤቶች ባደረጉት የጋራ ስብሰባ የሕገ መንግሥቱን ለውጥ የሚያረጋግጠውን ሕግ ፀድቋል። በ200 የሕግ አውጪዎች ድጋፍ፣ በ18 ተቃውሞ እና በአራት ድምጸ ተአቅቦ ያለፈው ሕግ ለመጽደቅ የፕሬዝዳንቱን ፊርማ ይጠብቃል።
ደጋፊዎቹ እንዳሉት ፕሬዝዳንቱን በመወከል የሚሠራ ሰው ስለሚኖር ረቂቅ ሕጉ የመንግሥትን አሠራር ያሻሽላል። የሴኔቱን የውክልና ሸክም በህግ አውጪዎች ላይ እንዲሆን ያስችላል ሲሉ አክለዋል።
ማሻሻያው ከመደረጉ በፊት የሴኔቱ መሪ ፕሬዝዳንቱ ከሞቱ ወይም መምራት ካልቻሉ ለጊዜው ስልጣኑን እንዲረከቡ ሕገ መንግሥቱ ይፈቅድ ነበር። በመቀጠልም ምርጫ ይካሄዳል።
የፀደቀው ሕግ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የሚመረጠው በምርጫ ሳይሆን በፕሬዝዳንቱ እንደሆነ ይገልጻል፤ የቀረውን የሰባት ዓመት የሥልጣን ዘመን እንደሚረከብም ያስረዳል።
ተቃዋሚዎቹ ሕጉ ሰፊ ምክክር ሳይደረግበት እንደቀረበ ተናግረዋል።
በፓርላማው ስድስት ተወካዮች ያሉት የሶሻል ዴሞክራቲክ ግንባር (ኤስዲኤፍ) ከድምጸዕ መስጠት ሂደቱ ራሱን አግልሏል። ምክትል ፕሬዝዳንትን በቀጥታ ከመሾም ይልቅ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በጋራ እንዲመረጡ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት አድርጓል።
ፓርቲው በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክልሎች መካከል ያለውን የቋንቋ ልዩነት የሚያንፀባርቅ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌም ጠይቋል። ኤስዲኤፍ ከ1972 በፊት እንደነበረው የአገሪቱን ሁለቱን ከፍተኛ ሥልጣናት የካሜሩን ሁለቱ ማህበረሰቦች እንዲጋሩት ፈልጎ ነበር።
"ይህ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ የፖለቲካ ለውጥ ጊዜ ሊሆን ይችል ነበር፣ ነገር ግን ያመለጠ ታሪካዊ ዕድል ነው" ሲሉ የኤስዲኤፍ ሊቀመንበር ጆሹዋ ኦሲህ ተናግረዋል።
የካሜሩን የሬይኔሳንስ ሙቭመንት መሪ የሆኑት ሞሪስ ካምቶ በበኩላቸው ማሻሻያው በገዢው ፓርቲ "የተካሄደ ሕገ መንግሥታዊ እና ተቋማዊ መፈንቅለ መንግሥት" እንደሆነ ገልጸዋል።
ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንቱ "የሪፐብሊካን ንጉሣዊ አገዛዝ" እየፈለጉ እንደሆነ ተከራክሯል።
እአአ ከ1961 እስከ 1972 ካሜሩን የአገሪቱን የፈረንሳይኛ እና እንግሊዘኛ ተናጋሪ ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚያከብር የፌዴራል ስርዓት ስር ትከተል ነበር።
በወቅቱ የምክትል ፕሬዝዳንት ሥልጣን ነበር። በ1972 የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ አገሪቱን ወደ አሃዳዊ መንግሥት ካዛወረ በኋላ ኃላፊነቱ ተሽሯል።












