አሜሪካ የሟቹን የኢራን ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ ዘመዶችን ማሰሯን አስታወቀች

ጄኔራል ቃሴም ሶሌይማኒን በ2020 ኢራቅ ውስጥ በተፈጸመው የአሜሪካ የአየር ጥቃት ተገድለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄኔራል ቃሴም ሶሌይማኒን በ2020 ኢራቅ ውስጥ በተፈጸመው የአሜሪካ የአየር ጥቃት ተገድለዋል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሟቹ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ የቅርብ ዘመዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሃሚድህ ሶሌይማኒን አፍሻርን እና የልጇን ሕጋዊ የአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ መሰረዙን መስሪያ ቤቱ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የሱሌይማኒን ልጅ ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ክስ አስተባብላ፤ የታሰሩት ግለሰቦች ከአባቷ ጋር "ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው" ተናግራለች።

የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ የነበሩት ሱሌይማኒን በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ በ2020 ኢራቅ ውስጥ በተፈጸመው የአሜሪካ የአየር ጥቃት ተገድለዋል።

በሩቢዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ሁለቱ ሴቶች በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስከባሪ ኃይል (አይስ) ቁጥጥር ስር እንዳሉ እና ከአገሪቱ እስኪባረሩ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

በኤክስ ላይ ባወጡት መግለጫ ሱሌይማኒ አፍሻር እና ሴት ልጇ "በዩናይትድ ስቴትስ በቅንጦት የሚኖሩ የግሪን ካርድ ባለቤቶች" መሆናቸውን አክለዋል።

በ2015 ወደ አሜሪካ በቱሪስት ቪዛ ከገቡ በኋላ ሱሌይማኒ አፍሻር በ2019 ጥገኝነት አግኝተው በ2021 የግሪን ካርድ ባለቤት ሆነዋል ሲል የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

በ2025 የዜግነት ማመልከቻ ሲያቀርቡ የግሪን ካርዳቸውን ከተቀበሉ በኋላ አራት ጊዜ ኢራንን እንደጎበኙ መግለጻቸውን መምሪያው አስታውቋል።

"ወደ ኢራን ያደረገቻቸው ጉዞዎች የጥገኝነት ጥያቄዎቿ ማጭበርበር ያለባቸው መሆናቸውን ያሳያል" ሲልም ገልጿል።

መምሪያው አክሎም የሱሌይማኒ አፍሻር ልጅ ሳሪናሳዳት ሆሴኒ በ2015 በተማሪ ቪዛ ወደ አሜሪካ መጥታ በ2019 ጥገኝነት፤ በ2023 ደግሞ ግሪን ካርድ እንደተሰጣት አስታውቋል።

ሶሌይማኒ አፍሻር "ኢራን ውስጥ ያለውን አምባገነናዊ እና አሸባሪ አገዛዝ በግልጽ ትደግፍ" እና በማህበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ "የኢራን አገዛዝ ፕሮፓጋንዳን" ታስተዋውቅ ነበር ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል።

የሱሌይማኒ አፍሻር ባል አሜሪካ እንዳይገባ ታግዷል ሲል መግለጫው ገልጿል። ሚኒስትሩ የሱሌይማኒ አፍሻርን ባል በስም አልጠቀሰም።

የሱሌይማኒ ልጅ ናርጄስ ሶሌይማኒ በመግለጫዋ "በአሜሪካ የታሰሩት ግለሰቦች ከሰማዕቱ ሱሌይማኒ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጠቀሱት ውንጀላዎች የተሳሳቱ ናቸው" ብላለች።

አሜሪካ "በጣም ደካማ እና ዋጋ ቢስ ሆናለች። በትልቅ ሰው ላይ ውሸት እየፈጠረች ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጥበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ቢጠይቅም "ምንም የሚጨምረው ነገር የለም" እንደሌለው አስታውቋል።

የታዋቂው ኢራን የኩድስ ኃይል መሪ የነበሩት ጄነራል ሱሌይማኒ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን መርተዋል።

የ62 ዓመቱ ጄነራል ከሌሎች በኢራን ከሚደገፉ ሚሊሻዎች ጋር በባግዳድ አየር ማረፊያ ተገድለዋል።