ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚቀጥለው ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ውስጥ ኢራንን በኃይለኛው እንደሚመቱ ተናገሩ

የአሜሪካ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ኢራን ላይ “እጅግ ኃይለኛ” የሆነ ጥቃት በመፈጸም የጀመሩትን ተግባር “በጣም በፍጥነት” እንደሚያጠናቅቁ አስታወቁ። ትራምፕ ትናንት ምሽት ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር የአሜሪካ ጦር በኢራን ጦርነት ሊደርስባቸው የፈለጋቸውን ግቦችን ለማሳካት መቃረቡን ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ያለመ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው

    የተፈጥሮ ጋዝ የሚያጓጉዝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዩናይትድ ኪንግደም 30 አገራት የሚሳተፉበት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት ያለመ ጉባዔን ልታስተናግድ ነው።

    ጉባዔው የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበትን ይህንን የባሕር መስመር ለማስከፈት የሚኖሩ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ አማራጮች ላይ ይነጋገራል ተብሎ እጠበቃል።

    ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ ጦርነት ከከፈቱባት ወዲህ በወሽመጡ ላይ የሚንቀሳቀሱ በርካታ መርከቦች ላይ ጥቃት ሰንዝራለች።

    በወሽመጡ ላይ የሚደረገው የመርከብ እንቅስቃሴ በዚህ የተነሳ ክፉኛ መስተጓጎሉ ተገልጿል።

    ረቡዕ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መተላለፊያውን ዳግም ለማስከፈት “ቢዘገዩም ወኔያቸውን ማጠናከር አለባቸው" ብለዋል።

    ትራምፕ አጋሮቻቸውን ሆርሙዝን ማስከፈት “አስቀድመው ሊያደርጉት ይገባ ነበር” ያሉ ሲሆን፣ አክለውም “ወደ ወሽመጡ ሄዱ፤ እና ውሰዱ፤ ተከላከሉ። ለራሳችሁ ተጠቀሙበት” ብለዋል።

    ዋሽንግተን በተደጋጋሚ አጋሮቿን ወሽመጡን ለመከላከል ወይም ጦርነቱ ለመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም በማለት ስትኮንን ቆይታለች።

    ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች አገራት ይህንን የዋሽንግተን ትችት ተከትሎ ወሽመጡን ለመጠበቅ በጦርነቱ ውስጥ ሳይሳተፉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲመለከቱ አስገድዷቸዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቬት ኩፐር ሐሙስ ዕለት በበይነ መረብ የሚካሄደውን ጉባዔ ይመራሉ ተብሏል።

    ጉባዔው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ኢራን በንግድ መርከቦች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታቆም የፈረሙ አገራትን ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል።

    የአገራቱ መግለጫ በተወሰኑ የባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች ድጋፍ አግኝቶ ነበር።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥቃት ከከፈቱባቸው አገራት ወይም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ውጪ ወሽመጡ ለሌሎች መርከቦች ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።

    ኒውዝሩም አፍሪካ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ቃል አቀባዩ እስማኤል ባግሃዒ፣ "ከባለሥልጣኖቻችን ጋር አስፈላጊው ትብብር ከተደረገ በኋላ" መርከቦች እንዲያልፉ ይደረጋሉ ብለዋል።

  2. ሩሲያ የኢራን ጦርነት እንዲቋጭ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሩሲያ የኢራን ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጾ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀጣናው መሪዎች ጋር መነጋገር መቀጠላቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ እንደተናገሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    “ፕሬዝዳንቱ እነዚህን ግንኙነቶች ቀጥለዋል፤ በሆነ መንገድ አገልግሎታችን ከተፈለገ በእርግጥም በተቻለ ፍጥነት ወታደራዊው ሁኔታ ወደ ሰላም እንዲሸጋገር ለማረጋገጥ አስተዋጾአችንን ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉ ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ አባልነት ለማስወጣት እያሰቡ እንደሆነ ስለመናገራቸው ለሩሲያው ቃል አቀባይ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፤ ሩሲያ ኔቶን የምትመለከተው እንደ ጠበኛ ጥምረት እንደሆነ በመግለጽ ምላሽ መስጠታቸው ሮይተርስ ዘግቧል።

  3. የኢራን ጦር ዋና አዛዥ የአገሪቱ ሠራዊት ለማንኛውም የጠላት ጥቃት እንዲዘጋጅ አዘዙ

    የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሃታሚ

    የፎቶው ባለመብት, tasnim

    የኢራን ጦር አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሃታሚ፤ ሠራዊቱ አመራሮች “የጠላትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥንቃቄ” እንዲከታተሉ እና ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመከላከል እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲዘጋጁ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተዘገበ።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒው ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጠላት በመሬት ዘመቻ ለመክፈት የሚሞክር ከሆነ “አንድም ሰው መትረፍ የለበትም” ሲሉ ለሠራዊቱ አዛዦች ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ዋና አዛዡ በመላው ኢራን ከሚገኙ የጦር አየር መከላከያ እንዲሁም የምድር፣ አየር እና ባሕር ኃይሎች አመራሮች ጋር እንደተነጋገሩ ዘገባው ያመለክታል። የጠላትን ጠበኛ ድርጊቶች ለመጋፈጥ እንዲቻል የኢራን ጦር ጥቃት ለመፈጸም እና ለመከላከል ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

    “የጦርነት ደመና ከአገራችን ላይ መነሳት አለበት፤ የሁሉም ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባል። ምክንያቱም አንድ ቦታ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሆኖ ሕዝባችን ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ጦር አዛዡ ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ውስጥ ኢራን “በኃይለኛው እንደሚመቱ” ከተናገሩ በኋላ ነው። አሜሪካ እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ኢራን ደሴቶች ልታሰማራ ተችላለች የሚለው ስጋትም መናፈስ ከጀመረ ሰንብቷል።

    ትራምፕ ትናንት ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ጦር በኢራን ሊያሳካ የሚፈልጋቸው “ዋነኛ ስትራቴጂክ ግቦች ሊጠናቀቁ እንደተቃረቡ” አንስተዋል። አክለውም ግን በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ኢራን ላይ “እጅግ ኃይለኛ” የሆነ ጥቃት በመፈጸም የጀመሩትን ተግባር “በጣም በፍጥነት” እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል።

  4. ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ ማስወጣት ይችላሉ?

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንዲቋቋም እገዛ ካደረገችበት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንደሚያስወጡ ዝተዋል። ፕሬዝዳንቱ ግን ይህንን ዓይነቱን ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ሲነገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአውሮፓውያኑ 2017 ለመጀሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸውንም በፊት በተደጋጋሚ ኔቶን “የወረቀት ላይ ነብር” በማለት ያጣጥሉት ነበር። “ያረጀ” ሲሉ የሚጠሩት ይህ ጥምረት የአሜሪካን “ሀብት እያስወጣ” መሆኑንም ይናገሩ ነበር።

    በ2019 ደግሞ “በዚህ ዛቻቸው ላይ ወደ እርምጃ ለመግባት እየተዘጋጁ” መሆኑን የሚያሳይ “ግልጽ ምልክት” አሳይተው እንደነበር የቀድሞው የኔቶ ዋጋ ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ በሳተሙት መጽሐፍ ላይ ከትበዋል።

    የጥምረቱን ወታደራዊ ወጪ ሲተቹ የቆዩት ትራምፕ፤ አገራት ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርታቸው ውስጥ ሁለት በመቶውን መከላከያ ላይ ማዋል እንዳለባቸው በሚያዝዘው በአውሮፓውያኑ 2014 የወጣ የኔቶ “መመሪያ” ደስተኛ እንዳልሆኑም ገልጸዋል።

    ይህ መመሪያ ከወጣ በኋላ ሁሉም አባል አገራት በሚባል ደረጃ ወታደራዊ አቅማቸው ላይ የሚያውሉትን በጀት ጨምረዋል። ከፊሉ ይህንን እርምጃ የወሰዱት በትራምፕ ዛቻ ምክንያት ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሩሲያ በኩል እየጨመረ በመጣው ስጋት የተነሳ እንደሆነ የቢቢሲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና ዘገቢ ሊስ ዱሴት ትገልጻለች።

    ኔቶን ለቅቆ የመውጣት ጉዳይ ግን በፕሬዝዳንቱ ብቻ የሚተላለፍ ውሳኔ አይደለም። ፕሬዝዳንቱ የሴኔቱን ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሳያገኙ ወይም በኮንግረስ ሕግ ሳይጸድቅ በተናጠል ከኔቶ መውጣት አይችሉም።

    ይህንን አሠራር የዘረጋው ሕግ በ2024 ሲጸድቅ ድጋፍ ከሰጡት አንዱ አሁን የኢራንን ጦርነት የሚደግፉት የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ናቸው።

    ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት ፎክስ ኒውስ ላይ ቀርበው አሜሪካ የጥምረቱ አባል መሆኗ “አሁንም ለዓላማዋ እየጠቀመ” መሆን እና አለመሆኑን “መልሶ እንደሚመረምር” ተናግረዋል። ሩቢዮ አክለውም ኔቶን “አሜሪካ አውሮፓን ለመደገፍ እንዲሁ የተቀመጠችበት” ጥምረት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

    በአውሮፓውያኑ 2026 መጀመሪያ ላይ ትራምፕ አሜሪካ ኔቶ እርምጃ እንዲወስድ ባታደርግ ኖሮ ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ትቆጣጠር ነበር ብለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2011 አሜሪካ ላይ የ9/11 ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ኔቶ በአንቀጽ 5 መሠረት ለአሜሪካ መጠነ ሰፊ ድጋፍ አድርጓል። ይህ አንቀጽ በአንድ አባል አገር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት እንደሚቆጠር ይደነግጋል። በዚህም የኔቶ ወታደራዊ አቅም በአንቀጽ 5 መሠረት ጥቅም ላይ ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

  5. ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ “አድቃቂ” እና “ሠፊ” ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠነቀቀች

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ፤ አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩት “ትንሽ” ዒላማዎች ላይ እንደነበር በመግለጽ ኢራን “አድቃቂ፣ ሠፊ፣ እና አውዳሚ” ጥቃቶችን እንደምትፈጽም አስጠነቀቁ።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ባለው ታስኒም የዜና ወኪል ላይ የወጣው መግለጫ፤ አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ አቅም እና መሣሪያ በተመለከተ ያላቸው መረጃ “ያልተሟላ” እንደሆነ ጠቅሷል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም የኢራን ወታደራዊ ምርት “የሚካሄደው ጭራሹኑ በማታውቁት ቦታ ነው” ብለዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን የመሣሪያ ክምችት በአብዛኛው እንደደመሰሱ የገለጹበትን ንግግር ቃል አቀባዩ ውድቅ አድርገዋል

    አሜሪካ እና እስራኤል “ለቀሰቀሱት ጥቃት ዋጋ መክፈል አለባቸው” ብለዋል።

  6. የኢራን ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ ሕዝብ "የጠላትነት ስሜት የለንም" ሲሉ ይፋዊ ደብዳቤ ጻፉ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, WANA/Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ኢራን በአሜሪካ ሕዝብ ላይ “የጠላትነት ስሜት የላትም” አሉ።

    አገራቸው “ወረራ ቢፈጸምባትም ጦርነት ቀስቅሳ እንደማታውቅ” የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ “ተደጋጋሚ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ጫና” ሲደርስባት ቢቆይም ሁሌም “በመንግሥታት እና በሚመሩት ሕዝብ መካከል ግልጽ ልዩነት እንደምታሰምር” ተናግረዋል።

    ኢራንን ስጋት ፈጣሪ አድርጎ መሳል “ከታሪካዊ እውነታም ሆነ አሁን ከሚታይ ሀቅ ጋርም የሚጣጣም እንዳልሆነ” በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

    የኢራን ሕዝብ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ወይም በጎረቤት አገራት ሕዝቦች ላይ መጥፎ ፍላጎት እንደሌላቸውም ሲሉም ጠቅሰዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ግንኙነት ከጅምሩ እንደ አሁኑ የሻከረ እንዳልነበረ እና አሜሪካ በአውሮፓውያኑ “1935 መፈንቅለ መንግሥት” ሲደረግ ባሳየችው “ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት” እንደተቃረነ በማንሳት ከስሰዋል።

    አሜሪካ በኢራን ዙሪያ “ከፍተና ቁጥር ያለው ኃይሏን” ማስፈሯን አስታውሰው፤ “ከእነዚህ የጦር ሰፈሮች የተከፈተው የቅርቡ የአሜሪካ ጥቃት ይህ ዓይነቱ ወታደራዊ ሰፈራ ምን ያህል አስጊ እንደሆነ አሳይቷል” ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን ይህንን ደብዳቤያቸውን የጻፉት፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “አዲሱ የኢራን አገዛዝ ፕሬዝዳንት” የተኩስ አቁም ጠይቀዋል ካሉ በኋላ ነው።በኢራኑ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ውስጥ ግን ሊደረስ የሚችል የተኩስ አቁምን በተመለከተ የተጠቀሰ ነገር የለም።

  7. ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ከስምምነት የማይደረስ ከሆነ ኢራንን መሠረተ ልማቶች ክፉኛ እንደሚመቱ ከዛቱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ዋነኛው ድፍድፍ ነዳጅ ብሬንት ዋጋ በአምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቶ ወደ 106 ዶላር ደርሷል።

    ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ ለዓለም የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ወሳኝ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ከሚያስችል ይልቅ የጦርነቱን መቀጠል የሚያመለክት ነገር መናገራቸው ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በንግግራቸው ከመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት የሚፈልጉ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት እንዲሆን ለማድረግ መሪነቱን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

    ጦርነት የተከፈተባት ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት ሆርሙዝን መዝጋቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከመጨመሩም በላይ በዓለም ላይ የአቅርቦት እጥረት ተከስቷል።

    የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ትራምፕ በንግግራቸው ላይ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው የሚካሄደው ጦርነት በቶሎ የሚያበቃበትን ሁኔታ በተመለከተ ምንም ዓይነት ተስፋ ባለመስጠታቸው በነዳጅ ገበያው ላይ አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደሚከፈት እና መስመሩ ለአሜሪካ፣ ለእስራኤል እና ለአጋሮቻቸው ዝግ ሆኖ እንደሚቀጥል ከማሳወቋ በተጨማሪ የባሕር መተላለፊያውን የበለጠ ለመቆጣጠር የሚያስችላትን አዲስ ሕግ አውጥታለች።

  8. የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን “ምን ማሳካት እንደሚፈለግ ግልጽ አይደለም” አሉ

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግን” እንደሚደግፉ ቢገልጹም “ከዚያ በዘለለ ምን ማሳካት እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም” ሲሉ ጥያቄያቸውን አስተጋቡ።

    በኢራን “ምን ማሳካት እንደሚፈለግ ግልጽ አይደለም” ያሉት አልባኔዝ ጦርነቱ “በምን ሁኔታ እንደሚያከትምም በውል አይታወቅም” በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኔዝ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካውያን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

    ጦርነቱ መቼ እንደሚያከትም ትራምፕ የጊዜ ገደብ አስቀምጠው እንደሆነ የተጠየቁት አልባኔዝ፤ “ይሄ ከመጀመሩ በፊት አውስትራሊያ አስተያየቷን አልተጠየቀችም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

    አክለውም “የተባባሰ ነገር ማየት እንደማንፈልግ በግልጽ ተናግሬያለሁ። እንዴት ያልቃል የሚለው ላይም የጠራ መረጃ መኖር አለበት” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው በጦርነቱ “ቀጥተኛ ተሳታፊ” እንዳልሆነች ጠቅሰው “ነገር ግን አውስትራሊያውያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

  9. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሚቀጥለው ሁለት ወይም ሦስት ሳምንት ውስጥ ኢራንን በኃይለኛው እንደሚመቱ ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ኢራን ላይ “እጅግ ኃይለኛ” የሆነ ጥቃት በመፈጸም የጀመሩትን ተግባር “በጣም በፍጥነት” እንደሚያጠናቅቁ አስታወቁ።

    ትራምፕ ትናንት ምሽት ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት በቴሌቪዥን የተላለፈ ንግግር የአሜሪካ ጦር በኢራን ጦርነት ሊያሳካ የፈለጋቸው ግቦች ላይ ለመድረስ መቃረቡን ገልጸዋል። ጦርነቱ መቼ ይጠናቀቃል ለሚለው ግን የጊዜ ሰሌዳ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ትራምፕ ባደረጉት ንግግር፤ በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ውሽመጥ በኩል የሚያልፍ ነዳጅ የሚረከቡ አገራት “ድፍረት” በማሳየት ወሳኙን መተላለፊያ እንዲቆጣጠሩ ጠይቀዋል።

    ትራምፕ 20 ደቂቃ ገደማ የፈጀው የዋይት ሀውስ ንግግራቸው፤ አሜሪካ በዚህ ጦርነት የያዘቻቸው “ዋነኛ ስትራቴጂክ ግቦች ሊጠናቀቁ እንደተቃረቡ” ተናግረዋል። የኢራን ባሕር ኃይል የድሮን እና ባለስቲክ ሚሳኤል ጦሮች “ተደምስሰዋል” ብለዋል።

    “በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ፤ በሚቀጥለው ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት በሚሆን ጊዜ ውስጥ እጅግ በኃይለኛው እንመታቸዋለን” ሲሉ ዝተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን አመራር ጋር “እየተካሄደ ነው” ስላሉት ንግግር ዝርዝር መረጃዎች ከመስጠት ተቆጥበዋል። ድርድርሩ ፍሬ አልባ የሚሆን ከሆነ የኢራንን የኢነርጂ መሠረተ ልማት እንደሚመቱም ጠቁመዋል።

    “ስምምነት ላይ ካልተደረሰ እያንዳንዱን የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ በጣም በኃይለኛው እንመታለን፤ ምናልባትም ተመሳሳይ ጊዜ ላይ” ብለዋል።

    “ምንም እንኳ ከሁሉም አንጻር ቀላሉ ዒላማ ቢሆንም ነዳጃቸውን አልመታንም፤ ምክንያቱም የመትረፍ ወይም መልሶ የመገንባት ትንሽም እንኳ ዕድል አይሰጣቸውም” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ንግግራቸው አስቀድሞ የኢራን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቃለች በማለት ጽፈው ነበር። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቶሎ በሰጠው ምላሽ የፕሬዝዳንቱን ገለጻ “ሐሰት እና መሠረተ ቢስ” ብሎታል።

    ትናንቱ ንግግራቸው ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ የአሜሪካ አጋሮች የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል። “ቢዘገይም ድፍረት አሳዩ” እንዲሁም “እንዲሁ ወደ ወሽመጡ ሄዳችሁ ያዙት” ብለዋል።

    አገራቸውን ከኔቶ የማስወጣት ሐሳብ እንዳላቸው ሲገልጹ የነበሩት ትራምፕ፤ በዚህ ንግግራቸው ከወታደራዊው ጥምረት ጋር ወደፊት ስለሚኖረው ሁኔታ አልጠቀሱም።

  10. አሜሪካ ተኩስ ለማቆም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ቅድመ ሁኔታ አቀረበች

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ ወር ያለፈው ጦርነት የሚቆምበት መንገድን በተመለከተ ከሁሉም ወገን የተለያየ እና የሚቃረን አስተያየት እየተሰነዘረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ጥቃቶች እና የአጸፋ ጥቃቱ ቀጥሏል።

    ትራምፕ ጦርነቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚቆም መናገራቸውን ተከትሎ ኢራን ድርድር ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቧን ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ከኢራን በኩል ተቃራኒ ዜና ወጥቷል።

    የኢራን ቴሌቪዥን ዛሬ ከሰዓት በኋላ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን በኩል የድርድር ጥያቄ ቀርቧል መባሉን “ሐሰት እና መሠረተ ቢስ” ነው መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።

    አሜሪካ እና እስራኤል እያካሄዱት ባለው ጥቃት ኢራን ከባድ ውድመት ቢደርስባትም የአጸፋ ጥቃቷ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ከባድ ፍርሃትን አስፍኗል።

    በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የዓለም ነዳጅ የሚተለላፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋቷ በአብዛኛው ዓለም ክፍል ውስጥ የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ንረት ተከስቷል።

    በዚህም ምክንያት የጦርነቱ ቀስቃሾች አሜሪካ እና አስራኤል እየተወቀሱ ሲሆን፣ ኢራን የባሕር መተላለፊያውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የምትከፍት ከሆነ አሜሪካ ተኩስ ለማቆም እንደምትስማማ እየተዘገበ ነው።

    በተጨማሪም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ “በአሸማጋዮች” በኩል ከኢራን ጋር ንግግር እያደረጉ መሆናቸውን እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ላይ ኢራን የአሜሪካን ቅድመ ሁኔታን እንድትቀበል በምሥጢር መልዕክት እንደተላለፈላት ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ የሆነው አክሲዮስ እንደዘገበው ተኩስ ለማቆም በምላሹ የሆርሙዝ መተላለፊያን ለማስከፈት ንግግር እየተካሄደ ነው።

    ኢራን ግን ከተኩስ አቁም ይልቅ ዘላቂ ጦርነት የማቆም ዋስትና እዲሰጣት በመጠየቅ ሌሎችንም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።

  11. በቴህራን በሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት ደረሰ

    ጉዳት የደረሰበት ቤተክርስቲያን በከፊል

    የፎቶው ባለመብት, Russian Embassy in Iran

    የምስሉ መግለጫ, ጉዳት የደረሰበት ቤተክርስቲያን በከፊል

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ዛሬ በተፈጸመ ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ጉዳት እንደደረሰበት በአገሪቱ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አስታወቀ።

    ኤምባሲው “ቴህራን በሚገኘው የቅዱስ ኒኮላስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ሁለት ጊዜ ጥቃት ተፈጽሞ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ዋና ሕንጻ የእንግዶች ማረፊያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።

    የሩሲያ ኤምባሲ ከፊል ጣሪያው የፈረሰ ሕንጻ እና የተሰባበሩ መስኮቶችን የሚያሳዩ ምሥሎችንም ከመልዕክቱ ጋር አብሮ አጋርቷል።

    በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ለክርስቲያኖች ዋነኛ የሆነው የትንሳዔ በዓል እየተቃረበ ባለበት ጊዜ መሆኑ “የአሜሪካ እና የእስራኤል ወደታራዊ ጀብደኝነት በኢራን የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን የሚሰባሰቡበትን ስፍራ አሳጥቷቸዋል” ሲል ኤምባሲው ወቅሷል።

    የቅዱስ ኒኮላስ ካቴድራል በሩሲያዊው የሥነ ሕንጻ ባለሙያ የተነደፈ ሲሆን፣ በኢራን ብሔራዊ የቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንደ አገሪቱ ቅርስ ተመዝግቧል።

    የሩሲያ ኤምባሲ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት የሲቪል መሠረተ ልማቶችን፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ዒላማ እያደረገ መሆኑን በመገልጽ አውግዞታል።

  12. ኢራን የተኩስ አቁም ጥያቄ ማቅረቧን ትራምፕ ተናገሩ

    መሐመድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ አውንታዊ አስተያየት እየሰጡ ያሉት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራን አዲስ አመራር ፕሬዝዳንት” የተኩስ አቁም ጥያቄ አቅርበዋል አሉ።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “ይህ ሰው እምብዛም አክራሪ አይደለም። ከእሱ ቀደም ሥልጣን ላይ ከነበሩት በተሻለ አዋቂ ነው” ብለዋል።

    ይህንን የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየትን በተመለከተ አስካሁን ከኢራን በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ኢራን ለድርር ጥያቄ አቅርባለች ብለው ቢናገሩም ከኢራን በኩል ግን ጥያቄ አለመቅረቡ በግልጽ ሲነገር ነበር።

    የኢራን ፕሬዝዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጦርነቱ በተኩስ አቁም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ በዘላቂነት መቆም እንዳለበት ከስምምነት መደረስ እንዳላበት አሳውቀዋል።

    አሁንም ኢራን ከስምምነት የምትደርሰው ድጋሚ ጦርነት እንደማይከፈትባት ዋስትና ሲሰጣት ብቻ መሆኑን ቅድመ ሁኔታ አቅርባለች።

    ትራምፕ አክለውም “የሆርሙዝ ወሽመጥ ሲከፈት እና ነጻ ሲሆን የምናስብበት ይሆናል። እስከዚያ ድረስ ግን ኢራንን ወደ ምንምነት ለመለወጥ ማጋየታችንን እንቀጥላለን። ወደ ድንጋይ ዘመን እንመልሳታለን” በማለት ጽፈዋል።

    ትራምፕ አዲሱ የኢራን መሪ በማለት በተደጋሚ እያደነቋቸው ያሉት ፖለቲከኛ ማን እንደሆኑ ለማወቅ እዚህ ያንበቡ ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ንግግር ቁልፍ ሰው እና ቀጣዩ መሪ ይሆናሉ የሚባሉት የኢራን አፈጉባኤ ማን ናቸው?

  13. ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ በአደባባይ ያልታዩት የኢራን ጠቅላይ መሪ መልዕክት አስተላለፉ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጃታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአባታቸውን ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ በአደባባይ ያልታዩት አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ፤ ለሄዝቦላህ መሪ ያላቸውን ድጋፍ በጽሑፍ ገለጹ።

    ጠቅላይ መሪው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ መሪ ኒያም ቃሲምን እንደሚደግፉ በጽሑፋቸው አስፍረዋል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያን ተከትሎ ሄዝቦላህ “ሐዘኑን መግለጹን” ጠቅሰውም ለቡድኑ ምስጋና አቅርበዋል።

    የሞጅትባ አባት የተገደሉት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት የመጀመሪያው ቀን ነበር።

    አዲሱ ጠቅላይ መሪ አባታቸውን ከተኩበት ጊዜ አንስቶ ለሕዝብ አልታዩም።

    እስራኤል አዲሱን ጠቅላይ መሪ ዒላማ እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ዝታለች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ “ማንም አላየውም። ስለዚህ ወይ ሞቷል፤ ወይ ክፉኛ ተጎድቷል” ብለዋል።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር በበኩላቸው ጠቅላይ መሪው በአደባባይ ያልታዩት “ለደኅንነታቸው ሲባል ነው” ብለዋል።

  14. ኢራን ላይ እየተፈጸመ ባለው ጥቃት ከ130 በላይ ታሪካዊ ቅርሶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነገረ

    ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Vahid Online

    አሜሪካ እና እስራኤል እየፈጸሙት ባለው ጥቃት ምክንያት ከ130 በላይ ታራካዊ ቅርሶች መውደማቸውን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኢራን ባሕላዊ ቅርሶች ሚኒስቴር መስክ ላይ ያደረገውን ቅኝት መሠረት በማድረግ በቀረበው ዘገባ ቁጥራቸው 132 የሚሆኑ ታሪካዊ ቅርሶች እና ጥንታዊ ሃውልቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    እየተካሄደ ባለው ጥቃት በኢራን ውስጥ በሚገኙ 18 ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ሃውልቶች እና ሕንጻዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ወድመዋል ብሏል ሚኒስቴሩ።

  15. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን ጦርነት ላይ የያዙትን አቋም እንደማይቀይሩ ተናገሩ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በኢራን ጦርነት የመሳተፍ ዕቅድ እንደሌላቸው ሲናገሩ የቆዩት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ “ምንም ጫጫታ” ቢኖር “አቋሜን አልቀይርም” አሉ።

    የዩናይትድ ኪንግደምን “የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ከአውሮፓ አጋሮች እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የጠበቀ ግንኙነት መኖርን እንደሚጠይቅ”፤ “ይበልጥ ግልጽ” እየሆነ መምጣቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    ስታርመር የኢራን ጦርነትን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ግንኙነታቸው እየሻከረ በመሆኑ ከአውሮፓ ጋር ያላቸውን ትስስር እያጠበቁ እንደሆን ተጠይቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ እንደማይመርጡ በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ ለእኛ ጠቃሚ ይመስለኛል” ብለዋል።

    “መከላከያ እና ደኅንነት፣ የኤነርጂ ልቀት እንዲሁም ኢኮኖሚን በተመለከተ ግን ከአውሮፓ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያስፈልገናል” ሲሉ ተናግረዋል። በአውሮፓ የሚደረግ ጠንካራ ትብብር ከአሜሪካ ጋር ያለ ግንኙነትንም እንደሚያግዝም አክለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር በኢራን ጦርነት ላለመሳተፍ በመወሰናቸው ከፍተኛ ጫና እንደደረሰባቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ጠቅሰዋል። “[የኢራን] ጦርነትን ከመቀላቀል ጋር በተያያዘ አቋሜን እንድቀይር ቀላል የማይባል ጫና ደርሶብኛል፤ በጦርነቱ ላይ አቋሜን አልቀይርም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ጫናው ምንም ይሁን ምን፣ ጫጫታው ምንም ቢሆን እኔ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ፤ በብሔራዊ ጥቅማችን መሠረት መንቀሳቀስ አለብኝ” ብለዋል።

    በዚህ የለንደን አቋም ያልተደሰቱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ለአጋር አገራት መልዕክት አስተላልፈዋል። “እንዴት ለራሳችሁ መዋጋት እንዳለባችሁ መማር መጀመር አለባችሁ፤ ከአሁን በኋላ አሜሪካ ለማገዝ አትደርስላችሁም” ሲሉ ጽፈዋል።

  16. ትራምፕ አሜሪካን ከኔቶ የማስወጣት ጉዳይን “አጥብቀው እያሰቡበት” መሆኑን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በኢራን ጦርነት እገዛ እንዲያደርግላቸው ያቀረቡትን ጥሪ ባለመቀበሉ አሜሪካን ከወታደራዊው ጥምረት ማስወጣትን አጥብቀው እያሰቡበት እንደሆነ ለብሪታኒያው ጋዜጣ ‘ዘ ቴሌግራፍ’ ተናገሩ።

    ኔቶን “የወረቀት ላይ ነብር” ሲሉ የጠሩት ትራምፕ፤ አሜሪካን ከመከላከያ ስምምነቱ የማስወጣት ሃሳብ “ከማጤን መሻገሩን” መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።

    የብሪታኒያው ጋዜጣ ከጦርነቱ በኋላ አሜሪካን ከኔቶ አባልነት የማስወጣት ዕቅድ ይዘው እንደሆን ጠይቋቸዋል። ትራምፕ ሲመልሱ፤ “አዎ፤ ከማጤን ባሻገር ጊዜው ደርሷል ብዬ መናገር እችላለሁ። የወረቀት ላይ ነብር እንደሆኑ ሁሌም አውቅ ነበር፤ በነገራችን ላይ ፑቲንም ይህንን ያውቃል” ብለዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የዓለም የኤነርጂ እቅርቦት ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ አድርጋለች። በዚህ ምክንያት ጫና የበረታባቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕም ኔቶ እና አጋሮቻቸው ወሽመጡን ለማስከፈት እገዛ እንዲያደርጉ ሲጠይቁ ሰንብተዋል። ከኔቶም ሆነ ከአገራት ያገኙት ምላሽ ግን አዎንታዊ አልሆነም።

    ትራምፕ ከጋዜጣው ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ኔቶ ሊያግዛቸው አለመንቀሳቀሱ “ለማመን የሚከብድ” እንደሆነ ተናግረዋል። ጥምረቱን ለማሳመን ያን ያህል አለመጎትጎታቸውን የተናገሩት ትራምፕ፤ ወዲያውኑ መንቀሳቀስ ነበረባቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

    “ዩክሬንን ጨምሮ ወዲያውኑ ነበር የደረስንላቸው። ዩክሬን ችግራችን አልነበረችም። ፈተና ነበር፤ እኛም ደርሰንላቸዋል። ሁሉም ቢሆን ስንደርስላቸው ነበር። ለእኛ [ግን] አልደረሱልንም” ሲሉ ለቴሌግራፍ ተናግረዋል።

    ትራምፕ በዚህ ቃለ መጠይቃቸው በጦርነቱ እንደማትሳተፍ የገለጸችላቸውን ዩናይትድ ኪንግደምንም ወርፈዋል። “የባሕር ኃይል እንኳን የላችሁም። በጣም አርጅታችኋል፤ አውሮፕላን ጫኝ መርከቦቻችሁን አይሠሩም” ብለዋል።

  17. ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን የኢራን ጦርነት በቶሎ እንዲያበቃ እንደሚፈልጉ ጥናት አሳየ

    የተቃውሞ ሰልፍ ላይ 'ጦርነት ይቁም' የሚል መፈክር የያዘች ሰልፈኛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከአሜሪካ ዜጎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የትራምፕ አስተዳደር ያስቀመጣቸው ግቦች ሳይሳኩም ቢሆን አገራቸው በኢራን ጦርነት ውስጥ ያላት ተሳትፎ በቶሎ እንዲያበቃ እንደሚፈልጉ የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳ ማሳየቱን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

    ሮይተርስ እና የሕዝብ አስተያየት ኩባንያው ‘አይፒኤስኦኤስ’ ባደረጉት ዳሰሳ ከተሳተፉ አሜሪካውያን ውስጥ 66 በመቶው ጦርነቱ እንዲቆም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። 27 በመቶ ያህሉ ደግሞ ጦርነቱ ለተራዘመ ጊዜ ቢቆይም እንኳ አሜሪካ ሁሉንም ግቦቿን ለማሳካት መሥራት አለባት የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ዘገባው ያመለክታል።

    ዘገባው እንደሚያሳየው፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ከሆኑ ሪፐብሊካኖች መካከል 40 በመቶ ያህሉ ግቦች ሳይሳኩም ቢሆን ጦርነቱ በቶሎ እንዲቋጭ ይፈልጋሉ። 57 በመቶው በአንጻሩ አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ ለተራዘመ ጊዜ መቆየቷን ይደግፋሉ።

    አንድ ወር በተሻገረው የኢራን ጦርነት ምክንያት መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በኤነርጂ ዘርፍ ላይ ክርኑን ያጠነከረው ጦርነት የነዳጅ አቅርቦት እንዲስተጓጎል እና ዋጋውም እንዲንር ምክንያት ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።

    በጥናቱ ከተሳተፉ 60 በመቶ አስተያየት ሰጪዎች ውስጥ 60 በመቶው ለጦርነቱ ጅማሬ ምክንያት የሆነውን የአሜሪካ ጥቃትን አይቀበሉትም። በዳሰሳው ከተሳተፉት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መካከል 35 በመቶው ደግሞ በኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እንደደገፉ ሮይተርስ ዘግቧል።

  18. በኤምሬትስ፣ በኳታር፣ በባህሬን፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በኩዌት ላይ የቀጠለው የኢራን ጥቃት

    ኢራን ውስጥ የተመታ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ባልተቋረጠ ጥቃት ውስጥ ያለችው ኢራን በአጸፋው በዙሪያዋ ባሉ አገራት ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው

    በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቃት ስር የምትገኘው ኢራን ወደ እስራኤል ከምትተኩሳቸው ሚሳዔሎች በተጨማሪ በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ በአጸፋ የምትወስደው እርምጃ ቀጥሏል።

    ኤምሬትስ: ከኢራን የተተኮሰ ሚሳዔል ተመትቶ ሲከሽፍ ስብርባሪው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ነዋሪ የሆነ አንድ ባንግላዲሻዊ ሠራተኛን ገድሏል።

    ኳታር: የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ትራንስፖርት ንግድ ማዕከል እንዳስታወቀው አንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከኳታር የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ በሚገኝ የውሃ አካል ላይ “በሁለት ተወንጫፊዎች” ተመትቷል።

    ባህሬን: የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል ዛሬ ጠዋት የተሰማ ሲሆን፣ የኳታር የአገር ውስጥ ጉዳይ እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች “በኢራን ጥቃት የተነሳን እሳት” ለማጥፋት መሰማራታቸውን አስታውቋል።

    ሳዑዲ አረቢያ: የመከላከያ ሚኒስቴሯ ዛሬ ጠዋት ሁለት ድሮኖችን እና ትናንት ሌሊት ሌሎች ተጨማሪ ድሮኖችን መትቶ ማክሸፉን አስታውቋል።

    ኩዌት: የአገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዳለው በዋና ከተማዋ ባለው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የሚገኝ የነዳጅ ማከማቻዎች በኢራን ድሮኖች ዒላማ መደረጋቸውን አሳውቋል። ጨምሮም በጥቃቱ “ከፍተኛ እሳት” ተነስቶ “ከፍተኛ ጉዳት” ቢደርስም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።

  19. ሊባኖስ ላይ ተጠናክሮ የቀጠለው የእስራኤል ጥቃት

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ቤይሩት ውስጥ የእስራኤል ሚሳዔል አንድ ሕንጻን የመታበት ቅጽበት

    ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሄደ ባለባት የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ አንድ የሄዝቦላህ አዛዥ እና ሌላ ከፍተኛ አመራር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የእስራኤል ጦር አስታወቀ።

    ጦሩ ሌሊቱን ቤይሩት ውስጥ በሁለት ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ በርካታ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የደኅንነት ባለሥልጣናት ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ ሲጓዝ የነበረ አንድ መኪና ከእስራኤል ድሮን በተወነጨፉ በርካታ ሚሳዔሎች መመታቱን የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ማክሰኞ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    አንድ ወር ባለፈው እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ጥቃት እስካሁን ድረስ ቢያንስ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

  20. ቻይና እና ፓኪስታን የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት ባለ አምስት ነጥብ የስምምነት ዕቅድ አቀረቡ

    ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቻይና እና ፓኪስታን፤ የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት አፋጣኝ ተኩስ አቁም ማድረግን እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ መልሶ መክፈትን የሚያካትት ባለ አምስት ነጥብ የስምምነት ዕቅድ አቀረቡ።

    የሰላም ዕቅዱ የተረቀው የፓኪስታነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ጦርነቱን እንዲያበቃ ለማደራደር በምታደርገው ጥረት የቻይናን ድጋፍ ለመጠየቅ ወደ ቤይጂንግ ከተጓዙ በኋላ ነው።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ሁለቱ አገራት “ሰላምን ለማስፈን አዲስ ጥረት” እያደረጉ ነው።

    ቻይን የኢራን ጦርነትን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሰጠችው ምላሽ የቀዘቀዘ ነው። ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያላት ቻይና ከሌሎች የእስያ አገራት በተለየ ለከፋ የነዳጅ እጥረት የተጋለጠች አይደለችም።

    ይሁን እንጂ ቀውሱ የሚቀጥል ከሆነ ለዓለም ገበያ ምርት የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች የሚገኙበት የቻይና የኢንዱስትሪ እምብርት በረጅም ጊዜ ሂደት ተጽዕኖ ሊደርስበት ይችላል የሚል ስጋት አለ።

    ይልቁንም የኢራን ጦርነት ጥላውን ያጠላው የፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ መሻት በሆነው መረጋጋት ላይ ነው። ቻይና እንድታድግ እና ምርቶቿን ለውጭ አገራት እንድታቀርብ ከተፈለገ የዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት የሰፈነበት ሊሆን ይገባል።

    አሁን የኢራን ጦርነት ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ መሻገሩን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ነው። የቻይና መንግሥትም ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ የሚያደርገውን ጥረት አሳድጓል።

    የአገሪቱ መንግሥት ከዚህ ቀደምም በመካለኛው ምሥራቅ የሰላም ፈጣሪነት ሚናን ሲጫወት ነበር፤ ይህም በአውሮፓውያኑ 2023 ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደረገ ሲሆን በዚህም አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።

    ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ከ14 የፍልስጤም ክንፎች የተወጣጡ መሪዎችን ሰብስቦ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲመሠረት አድርጓል።

    የአሁኑን የስምምነት ዕቅድ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል የተቀባይነት ምልክት አልታየም። ነገር ግን ይህ ተነሳሽነት እንዲቀጥል ግፊት ማድረግ ፕሬዝዳንት ዢ፤ ከሌሎቹ የዓለም ኃያል አገራት መሪዎች ሲነጻጸሩ ገለልተኛ አደራዳሪ እና ሰላም ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ ያስችላቸዋል።