ትራምፕ ከማክሰኞ በፊት ሆርሙዝ የማይከፈት ከሆነ ኢራን "ሲኦል" እንደምትሆን አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ከማክሰኞ በፊት የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ አገሪቱን “ሲኦል” እንደሚያደርጉ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሠራጩት መልዕክት ላይ የኢራን ባለሥልጣናት ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ካልከፈቱ የኢራንን ሲቪል መሠረተ ልማቶች ዒላማ እንደሚያደርጉ ዝተዋል።
ይህ አጸያፊ ቃላትን የያዘው የፕሬዝዳንቱ መልዕክት የተላለፈው ፕራምፕ ለኢራን ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሰኞ ዕለት ሊያበቃ በተቃረበበት ጊዜ ነው።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽሁፋቸው ላይ “ማክሰኞ የኃይል ማመንጫዎች፣ የድልድዮች ቀን ይሆናል፤ በኢራን ውስጥ ሁሉም በአንድ ጊዜ ይጠናቀቃሉ። ያንን [ጥቃት] የሚመስል አይኖርም!!! እናንተ [...]፣ [. . .] ሆርሙዝን ክፈቱ ወይም በሲኦል ውስጥ ትኖራላችሁ - ታያላቸሁ! ምስጋና ለአላህ ይሁን። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ. ትራፕ”
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።
መጀመሪያ፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም. ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች “ከትልቁ ጀምሮ ያሏት የኃይል ማመንጫዎች ፍረስርሳቸው ይወጣል” ብለው ዝተው ነበር።
ሁለተኛው፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ከኢራን ጋር “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ንግግር’ መደረጉን በመግለጽ የጥቃቱን ቀነ ገደብ በአምስት ቀናት አራዘሙት።
ሦስተኛው፡ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም. ደግሞ “በኢራን መንግሥት ጥያቄ መሠረት” የኃይል መሠረተ ልማቶችን የማጥቃት ቀነ ገደባቸውን በ10 ቀናት ማራዘማቸውን ሰኞ መጋቢት 28ን የመጨረሻው ቀን አደረጉት።
የ48 ሰዓታት ማስጠንቀቂያ፡ የሰኞው ቀነ ገደብ በተቃረበበት ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ “መአት” ከማዝነቸባው በፊት “48 ሰዓታት” እንደቀሩ አስጠንቅቀው ነበር።
አዲሱ ማስጠንቀቂያ፡ እሁድ ከሰዓት በኋላ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሆርሙዝ በቀሩት ሰዓታት ውስጥ የማይከፈት ከነሆ ኢራን ‘ሲኦል” እንደምትሆን ዝተዋል።
* ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ያሰፈሯቸው ቃላት ሙሉ በሙሉ በዜናው ውስጥ አልተካተቱም።

















