ትራምፕ፤ ኢራን የተዋጊ ጄት አብራሪውን ለማግኘት “እየተቃረበች ነበር” አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የኢራን ጦር በግዛቱ ውስጥ ተመትቶ የወደቀውን የአሜሪካ ተዋጊ ጄት አባል ለማግኘት “ከፍተኛ ቁጥር” ያለው ኃይል አሰማርቶ እና ወታደሩን ለማግኘት “እየተቃረበ” እንደነበር ገለጹ።
አሜሪካ ከአርብ ዕለት ጀምሮ ስትፈልገው የነበረውን የአየር ኃይል አባሏን ማግኘቷን ዛሬ ጠዋት አስታውቃለች። ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባሰፈሩት አዲስ መልዕክት “በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳውን እና እጅግ ጀግና የሆነውን የኤፍ-15 አባል/መኮንን ከኢራን ተራራሮች ጥልቅ ውስጥ ታድገነዋል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ “እጅግ የተከበረ ኮሎኔል” ሲሉ የገለጹትን ወታደር፤ የኢራን ጦር “አጥብቆ፣ በብዙ ቁጥር እየፈለገው እና [ለማግኘትም] እየተቃረ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።
አሜሪካ ወታደሯን ለማግኘት በርካታ አውሮፕላኖችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አሰማርታ ነበር። ዘመቻው የሚካሄደው በኢራን ግዛት ውስጥ በመሆኑም አደገኛ እንደሚሆን ባለሙያዎች ሲገልጹ ነበር።
ትራምፕም በልጥፋቸው “ይህ አይነቱ ስምሪት ‘በሰው እና መሣሪያ’ ላይ በሚያመጣው አደጋ ምክንያን ብዙውን ጊዜ የማይሞከር” እንደሆነ ገልጸዋል።
“ሁለተኛው ስምሪት የተደረገው አብራሪውን በእኩለ ቀን ከታደግንበት ከመጀመሪያው [ዘመቻ] በኋላ ነው፤ [የመጀመሪያው ስምሪት] ያልተለመደ እና በኢራን ሰማይ ላይ ሰባት ሰዓታትን ያሳለፍንበት ነው” ብለዋል።
ዘመቻውን “አስገራሚ የጀግንነት እና ተሰጥኦ ትዕይት” ሲሉ ገለጹት ትራምፕ፤ ነገ ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
















