ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ከኢራን ጋር እየተነጋገረች መሆኗን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን፤ ቁልፍ የዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ መዝጋቷ የኤነርጂ ዋጋ እንዲንር እንዲሁም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እየጨመረ ያለ ጫና እንዲያርፍ አድርጓል።
ወሽመጡን ከኢራን ጋር የምትጎራበተው ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ባጋራው ልጥፍ፤ ከቴህራን ባለሥልጣናት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። እንደ መስሪያ ቤቱ ገለጻ የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ኦማን ተገናኝተው በወሽመጡ በኩል “የተሳለጠ” የመርከቦች ጉዞ “ሊረጋገጥ የሚችልባቸው አማራጮችን” በተመለከተ ተወያይተዋል።
ዛሬ እሁድ የተደረገው ንግግር ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ እንደሆነ የገለጸው የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መተላለፊያውን በተመለከተ “በርካታ ርዕዮች እና እቅዶች” እንደቀረቡም አስታውቋል።
ሁለቱ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥ በተመለከተ የመከሩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኙ የመርከብ መተላለፊያ ሰኞ ዕለት የማይከፈት ከሆነ ኢራን ላይ “ሲኦልን” እንደሚያዘንቡ በዛቱ ማግሥት ነው።

















