አሜሪካዊውን የአየር ኃይል አባል ለማዳን ኢራን ውስጥ ስለተደረገው ዘመቻ እስካሁን የምናውቀው

የልዩ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በዘመቻው በርካታ አውሮፕላኖች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል ወደታሮች ተሳትፈዋል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አሜሪካ አርብ ዕለት በደቡባዊ ኢራን ተመትቶ የወደቀውን ኤፍ-15 ተዋጊ ጄት አብራሪ ማዳን መቻሏን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ጦር በታሪኩ ካካሄዳቸው "ድፍረት ከተሞላባቸው የፍለጋ እና የማዳን ዘመቻዎች መካከል አንዱ" የሆነውን ተግባር መፈጸሙን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ጠዋት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል። አብራሪው "አሁን ሰላም እና ደህና" እንደሆነም አክለዋል።

የአሜሪካው ተዋጊ ጄት ሁለት የአየር ኃይል አባላትን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ ሲመታ ሁለቱም ተስፈንጥረው ወጥተዋል። የመጀመሪያው አብራሪ አውሮፕላኑ ከተመታ በኋላ በዕለቱ ተገኝቷል።

የኢራን ባለሥልጣናት የጦር አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው በአየር መከላከያ ሥርዓት እንደሆነ ገልጸዋል።

የማዳን ዘመቻውን እና እንዴት ተካሄደ የሚለውን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ገና እየወጡ ነው። እስካሁን ያወቅናቸውን መረጃዎች እነሆ፦

 ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተመትቶ የወደቀው ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄት ከአየር ወደ ምድር የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ወይም የአየር ላይ ውጊያዎችን ማድረግ ይችላል

የአየር ኃይል አባሉን እንዴት መታደግ ተቻለ?

ተዋጊ ጄቱ ደቡብ ኢራን ውስጥ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ አሜሪካ እና ኢራን የጠፋውን ወታደር ለማግኘት ሽቅድድም ላይ ነበሩ።

አሜሪካዊው የነበረበት ሁኔታ ግልጽ ባይሆንም ለዘመቻው ቅርበት ያለው አንድ ምንጭ ደቡባዊ ኢራን ውስጥ "ከባድ" ውጊያ የነበረበት የፍለጋ እና የማዳን ዘመቻ ሲካሄድ እንደነበር ገልጿል።

በማዳን ዘመቻው ወቅት የአሜሪካ እና ኢራን ኃይሎች ሲታኮሱ እንደነበር ቢቢሲ ተገንዝቧል። አብራሪው ጉዳት የደረሰበት አውሮፕላኑ በተመታበት ወቅት ወደ ላይ ተስፈንጥሮ ሲወጣ እንደሆነ ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተመታው ጄት አብራሪዎችን የመታደግ ሥራው እጅግ ውስብስብ እና አጣዳፊ ነበር። ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ የውጊያ ፍለጋ እና የማዳን ዘመቻ የሚባል ሲሆን፣ የአሜሪካ ጦር እና አጋሮቹ ዝግጅት ሲያደርጉበት ቆይተዋል።

ከዚህ ተልዕኮ ጀርባ ካሉት የአየር ኃይል አሃዶች መካከል የተወሰኑት እጅግ የሠለጠኑ እና ልዩ የሠራዊት አባላትን ይዘዋል።

ብዙውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ዘመቻ የሚካሄደው በጠላት ግዛት ውስጥ ዝቅ ብለው በሚበርሩ ሄሊኮፕተሮች እንዲሁም በአካባቢው ጥቃት በሚፈጽሙ እና ቅኝት በሚያደርጉ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ነው።

ትራምፕ በማበኅራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው እንደገለጹት ሲፈለግ የነበረው ኮሎኔል "በኢራን አደገኛ ተራሮች ውስጥ ከጠላት መስመር ጀርባ ሆኖ ከሰዓት ወደ ሰዓት ሊደርሱበት እየተቃረቡ በነበሩ ጠላቶቻችን ሲታደን ነበር" ብለዋል።

ዘመቻውን ሲመሩ የነበሩ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአየር ኃይል አባሉን አድራሻ "ለ24 ሰዓታት" ሲከታተሉ እንደነበረም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው የሲቢኤስ ኒውስ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው በማዳን ዘመቻው ውስጥ ሲአይሴ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

የተዋጊ ጄቱ የመሣሪያ ሥርዓት መኮንን የሆነው ኮሎኔል ያለበት ቦታ ከመታወቁ አስቀድሞ ሲአይኤ ግለሰቡ እንደተገኘ እና ከአገሪቱ እያስወጡት እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ አሠራጭቶ ነበር።

ይህ የማሳሳቻ ዘመቻ እየተካሄደ ሳለም ተቋሙ ያሉትን አቅሞች በመጠቀም የአየር ኃይል አባሉ የሚገኝበትን ተራራማ ቦታ ማግኘት እንደቻለ አንድ ባለሥልጣን እንደነገሩት ሲቢኤስ ዘግቧል።

ከዚያም ተቋሙ የወታደሩን ትክክለኛ አድራሻ ለአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እና ለዋይት ሐውስ ሰጥቷል ተብሏል።

ይህ መረጃ የደረሳቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ወዲያውኑ የነፍስ አድን ዘመቻ እንዲጀመር ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን፣ ሲአይኤም ከአብራሪው ጋር የተያያዙ የቀጥታ መረጃዎችን ሲያቀርብ ነበር።

 ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 1988 ጥቅም ላይ የዋለው "ኤፍ-15ኢ" በአሁኑ ሰዓት ዋጋው 100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው

የአሜሪካ ጦር በርካታ አውሮፕላኖችን ወደ ኢራን እንደላከ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ አንድም አሜሪካዊ ሳይገደል እና ሳይጎዳ ዘመቻው እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል።

የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን በበኩሉ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች የጠፋውን ወታደር ሲፈልጉ የነበሩ የአሜሪካ ድሮኖችን መትተው መጣላቸውን ዘግበዋል።

ወታደሩን በሕይወት ማግኘት እንደምትፈልግ የገለጸችው ኢራን፤ አሜሪካዊውን ለሚይዙ ዜጎች ሽልማት አቅርባም ነበር።

የተመታው ጄት አባላት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን ለማለፍ የሚያስችል ከፍተኛ ሥልጠና የወሰዱ ናቸው።

'ዲፌስን ፕራዮሪቲ' የተሰኘው ወታደራዊ ትንተና የባለሙያዎች ቡድ ን(ቲንክ ታንክ) ዳይሬክተር የሆኑት ጄኔፈር ካቫናግህ፤ እዚህ ሁኔታ ወስጥ የሚሆኑ ወታደሮች "ቅድሚያ የሚሰጡት ዋነኛ ነገር በሕይወት መቆየት እና አለመያዝ ነው" ይላሉ።

"አካላዊ ብቃት እንዳላቸው እና እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርጋቸው ጉዳት እንዳልደረሰባቸው በማሰብ፤ በተቻለ ፍጥነት ከሚያርፉበት ስፍራ እንዲሸሹ እንዲሁም ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ እንዲደበቁ ተደርገው ሠልጥነዋል" በማለት ያስረዳሉ።

በተጨማሪም ያለ ምግብ ወይም ውሃ አልያም በአካባቢው የሚጠቅማቸው ነገር ሳያገኙ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ስለሚያስችሏቸው ዘዴዎች ሥልጠና እንደሚወስዱ ካቫናግህ ይናገራሉ።

ተዋጊው ጄት የት እና መች ተመታ?

የኢራን መገናኛ ብዙኃን አገሪቱ ጦር ደቡባዊው ግዛት ውስጥ የአሜሪካ ጄትን መምታቱን የዘገቡት አርብ ዕለት ነበር።

ኤፍ-15 ተዋጊ ጄት የተመታበት ትክክለኛ ቦታ እስካሁን አልተረጋገጠም። ይሁን እንጂ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ኮህጊሉዬህ እና ቦየር አህማድ እንዲሁም ካሁዜስታን ተሰኙት ሁለት ግዛቶች በተደጋጋሚ ጠቅሰዋል።

የተመታው ጄት ውስጥ የነበሩት ሁለት የአየር ኃይል አባላት ናቸው። የጄቱ አብራሪ የተገኘው በዘመቻው የመጀመሪያ ሰዓታት ውስጥ ነው።

የመታደግ ዘመቻው ኤ-10 ዋርቶግ አውሮፕላንንም ያካትት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ አውሮፕላን በባሕረ ሰላጤው ሲበርር እንደተመታ ተገልጿል። አብራሪው ተስፈንጥሮ እንደወጣ እና በኋላ ላይ እንደተገኘም ተሰምቷል።

በኤፍ-14ኢ አውሮፕላን ውስጥ የነበረውን አብራሪ ይዞ ሲጓዝ የነበረ ሄሊኮፕተር በአነስተኛ መሣሪያ ተመትቶ ውስጡ የነበሩ አባላት እንደተጎዱ፤ ነገር ግን በሰላም እንዳረፉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በአገሪቱ ተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደር ጎሳዎች የመታደግ ተልዕኮው አካል የነበሩ ሁለት 'ብላክ ሃውክ' ሄሊኮፕተሮችን መምታታቸውን አስታውቋል።

 ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አርብ ዕለት የወጣ እና ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ሦስት የታጠቁ ግለሰቦች ቢያንስ ሁለት 'ብላክ ሃውክ' ሄሊኮፕተሮች ላይ ሲተኩሱ አሳይቷል።

ኢራን ከፍተኛ ጦር ዕዝ፤ ሁለት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ተመትተው የወደቁት በአገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓት አማካኝት እንደሆነ መግለጹን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ኢርና የዜና ወኪል ዘግቧል።

በደቡብ ምዕራባዊ ኢራን የሚገኘው ኮህጊሉዬህ እና ቦየር አህማድ፤ ተራራማ እና አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የያዘ ግዛት ነው።

በአካባቢው የሚገኙት አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለመጠበቅ እንዲሁም መኖሪያቸውን ከዱር እንስሳት እና ከዘራፊዎች ለመጠበቅ መሣሪያ በመታጠቅ ይታወቃሉ።

ከተመታው የአሜሪካ ጄት ጋር ተያይዞ ስሙ እየተነሳ ያለው ሌላኛው ግዛት ካሁዜስታን ደግሞ ነዳጅ እና በርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙበት ነው። ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የያዘው ይህ ግዛት አረቦች፣ ፋርሶች፣ ሎርሶች እና ሌሎች ማኅበረሰቦች ይኖሩበታል።

ተመትቶ ስለወደቀው ተዋጊ ጄት ጥቅም ምን እናውቃለን?

ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄት ከአየር ወደ ምድር ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም የአየር ለአየር ውጊያዎች እንዲፈጽም ሆኖ የተሰሠራ ነው።

ጄቱ ወደ ኢራን የበረረው ድሮኖችን እና ክሩዝ ሚሳዔሎችን በመምታት የመከላከያ የአጸፋ የአየር ጥቃት ለመፈጸም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ጄቱ ከአየር ወደ ምድር ጥቃት በሚፈጽምበት ወቅት ከመተኮሱ በፊት ዒላማው ላይ ጨረር ማስቀጥ ይችላል። በጂፒኤስ የሚመሩ ትክክለኛ ዒላማ መቺ ተተኳሾችን እና ሌሎች ቦንቦችንም የመያዝ አቅም አለው።

የጦር አውሮፕላኑ ሁለት ሰዎችን መያዝ ይችላል። ጄቱን የሚያበርረው ፓይለት ከፊት የሚቀመጥ ሲሆን፣ የመሣሪያ ሥርዓት መኮንኑ ደግሞ የኋለኛው መቀመጫ ላይ ይሆናል።

የመሣሪያ ሥርዓት መኮንኑ ከፊት ለፊቱ አራት ስክሪኖች ይኖሩታል። ዒላማዎችን የመምረጥ እና ለጥቃት ዒላማው ተገቢ የሆነው መሣሪያ በአግባቡ መዘጋጀቱን የማረጋገጥ ኃላፊነቶችን ይወጣል።

ተዋጊ ጄቱ ሁለት ሰዎችን የሚጭን መሆኑ የሥራ ክፍፍል እንዲኖር ያስችላል። በተለይም አብራሪው ከጠላት ለማምለጥ በሚሞክርበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሁለት ሰው መኖሩ እጅግ ጠቃሚ ነው።

የአሜሪካውን ተዋጊ ጄት እንዲወድቅ ያደረገው ምን ትክክለኛ ነገር ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ያዳግታል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንደገለጸው መትቶ ጥሎት ከሆነ ጄቱን ያጠቃው ከምድር ወደ አየር የተወነጨፈ ሚሳዔል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

የኤፍ-15 ጄት ዝርያዎች ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበረ ቢሆንም "ኤፍ-15ኢ" ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በ1988 ነው። የአንዱ ጄት ዋጋ 100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው።