ዩኤኢ የኢራን እርምጃ የባሕረ ሰላጤውን አገራት ወደ አሜሪካ የሚገፋ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን እና “በእኛ እና በሌሎች አገራት ላይ እየዘነበ ያለውን ሚሳዔል እና ድሮን” ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮችን መፍታት የማይችል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረግ አስጠነቀቀች።
የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ በሰጡት መግለጫ አገራቸው ግጭቱ እንዲቆም እንደምትፈልግ ተናግረው ነገር ግን ወደፊት በቀጣናው ውስጥ ቀጣይነት ያለው አለመረጋጋትን የሚፈጥር እንዳይሆን ተናግረዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በጥነምረት ጥቃት ከከፈቱባት ወዲህ ኢራን የዓለም ዋና የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዘግታለች።
በየቀኑ በጣት የሚቆጠሩ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ብቻ በወሽመጡ የሚያልፉ ሲሆን ይህ ግን ከተለመደው ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።
የኢራን ስትራቴጂ የባህረ ሰላጤውን አገራት ከዋሽንግተን ጋር ያላቸውን የደህንነት ትስስር ሊያጠናክር እና የእስራኤልን ተፅዕኖ በቀጣናው ላይ የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት "በእጥፍ" እንደምታሳድግም አክለው ተናግረዋል።
“የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በማንኛውም አገር ታግቶ መያዝ አይችልም” ያሉት አማካሪው፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደ የባህር ኃይል ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ባትሆንም፣ “በወሽመጡ ውስጥ የሚደረግ የባህር ጉዞን ለማረጋገጥ በአሜሪካ የሚመራ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ጥረት” ትቀላቀላለች ብለዋል።















