ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢራን ለጋዜጠኞች ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ዓመታዊ የትንሳዔ በዓል ላይ ተገኝተው የኢራን ጦርነትን በሚመለከት ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ምን አሉ?
- ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ የኢራንን ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በድጋሚ ዝተዋል። “የማይከፍቱ ከሆነ ድልድይ አይኖራቸውም፤ የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም። ምንም አይኖራቸውም” ካሉ በኋላ “ከዚህ በላይ መሄድ አልችልም፤ ከእነዚህ ከሁለቱ በላይ የከፋ ነገር አለ” ብለዋል።
- ትራምፕ ኢራን የአሜሪካን ተዋጊ አውሮፕላን መትታ የጣለችው በክህሎት ሳይሆን “በአጋጣሚ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ሆኖም “አሁን ምናልባት በውስጣቸው ብዙ ጥይት ቀዳዳ ያላቸው አንዳንድ ሄሊኮፕተሮች አሉን” ብለዋል።
- ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም ያሉ ሲሆን፣ "እብዶች ናቸው እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በእብዶች እጅ ማስገባት አንችልም" ብለዋል።
- አክለውም እንደ "እኔ ቢሆን ኖሮ የኢራንን ሰፊ የነዳጅ ዘይት ክምችት እወስድ ነበር" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው “በርካታ ገንዘብ አገኝበት ነበር” ብለዋል።
- ትራምፕ በርካታ አሜሪካውያን በኢራን የሚያካሄዱትን ጦርነት ቢቃወሙም አሁንም ጦርነቱን የሚቃወሙ “ጅሎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
- ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ድረስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ የመጨረሻው መሆኑን ተናግረው፤ ኢራን ለአሜሪካ ጦርነቱ እንዲያበቃ ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ የሰጠችውን ምላሽ “ወሳኝ” ነገር ግን “በቂ ያልሆነ” ሲሉ ገልጸውታል።

















