ቀጥታ, አሜሪካ በኢራን ጦርነት እስካሁን ምን ያህል የጦር አውሮፕላኖችን አጣች?

ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው አርብ ዕለት በኢራን የተከሰከሰውን ተዋጊ ጄት አብራሪ እና የጦር መሣሪያ ባለሙያ ፍለጋ የተሰማሩ ሁለት የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ከኢራን መነሳት አልቻሉም። አውሮፕላኖቹ በጠላት እጅ እንዳይወድቁ በሚል እንዲወድሙ መደረጉ ተዘግቧል። አሜሪካ ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘው በዚህ የኢራን ጦርነት ውስጥ ምን ያህል አውሮፕላኖችን አጥታለች?

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ በኢራን ጦርነት ያጣቻቸው የጦር አውሮፕላኖች

    በኢራን የወደቀን አውሮፕላን ፍርስራሽ የሚያሳይ

    የፎቶው ባለመብት, Social media

    እንደ አሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እና የምሥል ትንተናዎች ከሆነ አሜሪካ እስካሁን ድረስ በጦርነቱ ቢያንስ ዘጠኝ አውሮፕላኖችን አጥታለች።

    መጋቢት 27 2018 ዓ.ም.- ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤፍ-15ኢ” ተዋጊ ጄትን ለማገዝ የተጓዙ ሁለት የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ከኢራን መነሳት አልቻሉም። አውሮፕላኖቹ በጠላት እጅ እንዳይወድቁ በሚል እንዲወድሙ መደረጉ ተዘግቧል። የተረጋገጡ ምሥሎች አውሮፕላኖቹ በማዕከላዊ ኢራን እንደወደሙ አሳይተዋል። ቢቢሲ ቨሪፋይ የአውሮፕላኖቹን ዓይነት ለመለየት ባለሙያዎችን ጠይቋል።

    መጋቢት 25- በማዕከላዊ ኢራን ተዋጊ ጄት ተመትቶ ወድቋል። ባለሙያዎች ከስብርባሪው ባገኙት መረጃ ተመትቶ የወደቀው ጄት “ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኤግል” የተባለው የአሜሪካ ተዋጊ ጄት መሆኑን ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ቀን ኒዮርክ ታይምስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው “ኤ-10” የተባለ ጄት በባሕረ ሰላጤው ተከስክሷል። አብራሪው ቀድሞ ተመንጥቆ በመውጣት ሊተርፍ ችሏል።

    መጋቢት 20- ማረጋገጥ የቻልነው ምሥል “ኢ-13” የተባለ አውሮፕላን የኢራንን ጥቃት ተከትሎ በሳዑዲ አረቢያ ልዑል ሱልጣን አየር ጣቢያ ለሁለት መከፈሉን ያሳያል።

    መጋቢት 3- “ኬሲ-135” የተባለ የነዳጅ መሙያ አውሮፕላን በምዕራብ ኢራቅ ተከስክሶ ስድስት ወታደሮች ሕይወታቸው ማለፉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) አስታውቋል። ክስተቱ እየተመረመረ ቢሆንም ኮማንዱ በጠላት አሊያም በወዳጅ አገራት ተኩስ አለመውደቁን ግን ጠቁሟል።

    የካቲት 23- ሦስት የአሜሪካ “ኤፍ-15ኢ” ጄቶች ሴንትኮም “በወዳጅ አገራት ያልተጠበቀ ክስተት” ሲል በገለፀው ሁነት በኩዌት ወድቀዋል። ስድስቱም አባላት አስቀድመው መውጣት መቻላቸውንም አክሏል። ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተንቀሳቃሽ ምሥል ማረጋገጥ እንደቻለው ጄቶቹ በኩዌት ከተማ ምዕራባዊ ክፍል ወደ መሬት ሲሽከረከሩ ነበር።

  2. በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ ዓለም በስጋት የሚጠብቃቸው ቀጣይ ሰዓታት

    የአሜሪካ ኤፍ-15ኢ ተዋጊ ጄቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ አውዳሚ ጥቃት ይፈጸማልበማለት ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የሰዓታት ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በአንድ በኩል ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘው ጥቃታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ ኢራንም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ አገራት ላይ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ካልተከበረ ኢራንን “ወደ ድንጋይ ዘመን” ይመልሳታል ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ሰዓት እየተቆጠሩ ናቸው።

    ይህ የኢራንን የሲቪል የኃይል ማመንጫ ተቋማትን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደርጋል የተባው የትራምፕ ዛቻ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ “የጦር ወንጀል ነው” በማለት ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።

    ይህ ሁሉ የጥቃት እና የውድመት ዜና እየተሰማ ባለበት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው። በፓኪስታን መሪነት የሚደረገው ጥረት ወደ ወሳኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

    ፓኪስታን ጦርነቱን ለማብቃት በአሸማጋይነት “አዎንታዊ እና ውጤታማ ጥረት” እያደረገች መሆኑን በኢስላማባድ የኢራን አምባሳደር ጠቅሰው በሂደቱም “ወሳኝ እና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ደረጃ ላይ እየተደረሰ” መሆኑን ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል አሜሪካ በአስቸኳይ ከተኩስ አቁም እንዲደረስ እና ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣላችው ዕቀባ ካነሳች በኋላ ቀጣይ የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ ሃሳብ ብታቀርብም፤ ኢራን ግን የራሷን የድርድር ሃሳብ በመቅረብ ውድቅ አድርጋዋለች።

    ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት የተከፈተባት ጦርነት በዘላቂነት እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ እና በጥቃቱ ለደረሰባት ውድመት የመልሶ ግንባታ ሃሳብን አቅርባለች።

    እየተካሄዱ ያሉት ንግግሮች በፍጥነት ተቋጭተው በቀጣይ ሰዓታት ውስጥ ከስምምነት ካልደረሰ አሜሪካ ባላት ኃይል ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ እርምጃ እንደምትወስድ፣ ኢራንም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ሁሉን አቀፍ አጸፋ እንደምትመልስ እየዛቱ ነው።

    ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ያሉት መጪዎቹ ሰዓታት ለኢራን ብቻ ሳይሆን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ብሎም ለመላው ዓለም መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች የሚተላለፉበት ሊሆኑ ይችላሉ።

    መላው ዓለምም ምን ሊከሰት እንደሚችል በስጋት እና በጉጉት እየጠበቀ ነው።

  3. የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ 13 ሺህ ዒላማዎችን መደብደቧን አስታወቀች

    "ኤፒክ ፊዩሪ" በተባለው የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ የመጀመሪያ ቀን ይፋ የሆነ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, US CENTCOM

    እስራኤል በኢራን ተጨማሪ ጥቃቶችን መፈፀሟን ሪፖርት ካደረገች በኋላ የአሜሪካ ጦር ጦርነቱ ከተጀመረ ከየካቲት 21 ወዲህ 13 ሺህ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን እያካሄደች ባለችው እና “ኤፒክ ፉዩሪ” ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ዘመቻ ከ155 በላይ የኢራን መርከቦችን መውደማቸውን አሊያም መጎዳታቸውንም አስታውቃለች።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (ሴንትኮም) ከደበደባቸው ዒላማዎች መካከል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና መስሪያ ቤት፣ የአየር መቃወሚያ ስርዓት፣ የባላስቲክ ሚሳኤል ጣቢያዎች እና የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ሰርጓጅ መርከቦች ይገኙበታል ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ዜና ወኪል የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,665 ንፁሃንን ጨምሮ 3,500 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

  4. ኢራን ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት” እንደተፈፀመባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቡድን ገለፀ

    ሠኞ እለት በፈተፈፀመ ጥቃት የወደመ ሕንፃ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል-አሜሪካ ጦርነት በኢራን ከተጀመረ ወዲህ 1,600 የሚሆኑ ንፁኃንን ጨምሮ 3,500 የሚሆኑ ሰዎች በአገሪቱ እንደተገደሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የዜና ወኪል (ሀራና) አስታውቋል።

    ትናንት ሠኞ ብቻ 59 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 58 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን በምሽት ዳሰሳው ገልጿል።

    ያለፉት 24 ሰዓታት “ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ከተፈፀሙት ጥቃቶች ከፍተኛ መጠን ነው” ብሏል።

    ሠኞ ዕለት በቴህራን የሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርስቲ፣ በመኖሪያ ሕንፃ እና በኬሚካል ፋብሪካ ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ትላልቅ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

    ቡድኑ በመስክ ሪፖርት፣ ከአካባቢው ምንጮች፣ ከሕክምና እና ድንገተኛ አደጋ ምንጮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረቶች እንዲሁም ከፎቶግራፎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ከመንግሥት ባለሥልጣናት መግለጫዎች በመጭመቅ አሃዛዊ መረጃውን እንደሚያጠናክር ገልጿል።

  5. የፀጥታው ምክር ቤት በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን ለመጠበቅ ድምፅ ሊሰጥ ነው

    አሜሪካ ቋሚ አባል የሆነችበት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ወር ሲሰበሰብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢራን ለአብዛኛው መርከቦች የተዘጋውን ቁልፍ የባሕረ ሰላጤው መተላለፊያ ለማስከፈት ድምፅ ይሰጣል።

    የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በሆነቸው ባሕሬን የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት ቀርቦ የነበረ እና ወደዚህ ሳምንት የተላለፈ ነው።

    የውሳኔ ሀሳቡ ይዘት መጀመሪያ ከቀረበ በኋላ ማሻሻያ እንደተደረገበት ታውቋል።

    በመጀመሪያው ረቂቅ አባል አገራት “ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እና ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃዎችን እንዲወስዱ “ይፈቅዳል።”

    አዲሱ ማሻሻያ ደግሞ ደኅንነት የተሞላበት ጉዞ ለማድረግ “ጥረቶችን ማቀናጀት፣ ተፈጥሯዊ መከላከል፣ ከሁኔታው ጋር የሚመጣጠን እርምጃ” “በጥብቅ እንደሚያበረታታ” ይጠቅሳል።

  6. የእስራኤል ጦር ኢራናውያን ዛሬ ባቡር እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀ

    ባቡር የሚሳፈሩ መንገደኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ጦር በይፋዊ የማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ በፋርስ ቋንቋ ባሰፈረው መልዕክት በኢራን የሚኖሩ ሰዎች “ለደህንነታችሁ” በማለት ”በባቡር ከመጓዝ ተቆጠቡ” ብሏል።

    ማስጠንቀቂያው በመላው አገሪቱ ለሚኖሩ ኢራናውያን መሆኑን የገለጸው ጦሩ በኢራን ሰዓት አቆጣጠር “እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት” ድረስ ማስጠንቀቂያው እንደሚቆይ ገልጿል።

    አክሎም “በባቡር ውስጥ መሆን አና በባር ሃዲዶች አቅራቢያ መገኘት ሕይወታችሁን አደጋ ላይ ይጥለዋል” ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመላው ኢራን የሚገኘው የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛታቸውን ተከትሎ ነው።

    ሠኞ ምሽት የእስራኤል ጦር ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ያላቸውን "የቴህራን መሠረተ ልማቶችን" ዒላማ በማድረግ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀሙን እና የሄዝቦላህ አባላትን መግደሉንም ገልጿል።

    ከዚህ ውጭም የእስራኤል ጦር ከኢራን ወደ እስራኤል የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን መቀልበሱን አስታውቋል።

  7. የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ቡድን በኢራን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ነው ሲል አስጠነቀቀ

    ሌሊቱን በቴህራን እና በካራጅ በርካታ ጥቃቶቸ ተፈጽመዋል

    የፎቶው ባለመብት, vahidonline

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ጥቃቶች በመላው ኢራን እየተፈጸሙ በመሆናቸው ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታወቀ።

    እአአ ከመጋቢት 17 እስከ ሚያዚያ 3 ባለው ጊዜ ውስጥ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ ገበያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች እና የባህል ቅርስ ስፍራዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲል ቡድኑ ገልጿል።

    ኦቻ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጋቢት 30 ድረስ ከ2,100 በላይ ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን፣ ከ27,900 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ 3.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጦርነቱ እንደጎዳቸው አስታውቋል።

    እናም ከጦርነቱ መጀመሪያ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ሳምንታት ከ115,000 በላይ የሰላማዊ ሰዎች መገልገያዎች ተጎድተዋል ሲል አክሎ ተናግሯል።

    ኦቻ በተጨማሪም "ወሳኝ በሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና የኢንዱስትሪ መንደሮች ላይ የተካሄደው ጥቃት የመብራት፣ የውሃ እና የቴሌኮሙኒኬሽንን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስተጓጎሉ ፈጣን እና ረዥም ጊዜ የሚቆይ የአካባቢ እና የጤና አደጋዎችን አስከትሏል" ብሏል።

  8. በኩዌት ሌሊቱን በተፈጸመ ጥቃት አሜሪካውያን ተጎዱ

    ኢራን በኩዌት አሊ አለ ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት 15 አሜሪካውያን ጉዳት እንደረሰባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ተናገሩ።

    አንድ ባለሥልጣን አብዛኛዎቹ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 373 የአሜሪካ ጦር አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    ከእነዚህ መካከል 330ዎቹ ወደ ሥራቸው ሲመለሱ አምስቱ ግን ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ለሲቢኤስ ተናግሯል።

  9. ትራምፕ በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ላይ ምን አሉ?

    ዶኣነልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ትናንት ምሽት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት፣ የሲአይኤ ዳይሬክተሩ ጆን ራትክሊፍ እንዲሁም የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄነራል ዳን ኬይን በዋይት ሐውስ መግለጫ ሰጥተዋል።

    መግለጫው ያተኮረው አርብ ዐዕለት በኢራን ተመትቶ የተከሰከሰው ተዋጊ ጄት ውስጥ የነበሩ ሁለቱ የአሜሪካ አየር ኃይል አባላትን ለማዳን ስለተካሄደው ዘመቻ ማብራራት ነበር።

    የትራምፕ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የበረራ አባላቱን ለማዳን የተደረገውን "ጀግንነት" ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ማክሰኞ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደገና ካልተከፈተ አሜሪካ በኢራን የኃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።

    "መላው አገሪቱ በአንድ ሌሊት ሊጠፋ ይችላል፤ ያ ምሽት ደግሞ ነገ ማታ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

    የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ኢራን ወደ "ድንጋይ ዘመን" ትመለሳለች ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።

    "ድልድይ አይኖራቸውም" ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ምንም አይነት የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም" ሲሉም ዝተዋል።

    በዜና መግለጫው ላይ የተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች እነሆ፡

    • ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለይ ሁለተኛውን የአየር ኃይል አባል ፍለጋ ለማግኘት በተካሄደው የ48 ሰዓታት የሕይወት አድን ጥረት ሁሉም የሠራዊቱ አባላት ሙሉ ዕምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
    • “በጣም አደገኛ ተልዕኮ” መሆኑ እንደተነገራቸው ያስረዱት ትራምፕ ነገር ግን “የሚገባው እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” ብለዋል።
    • አንድ የዜና ተቋም አንድ ፓይለት መጥፋቱን ከዘገበ በኋላ ተልእኮው ችግር ገጥሞት እና ከባድ አድርጎት ነበር ያሉት ትራምፕ የኢራን ባለሥልጣናትም ከዘገባው በኋላ የአየር ኃይል አባሉን ለመያዝ የራሳቸውን ዘመቻ መክፈታቸወን ተናግረዋል። ዋናውን የመረጃ ምንጩን ለማግኘት የአሜሪካ ባለስልጣናት ጠንክረው እየሰሩ ነው ብለዋል።
    • ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ከኢራን ጋር የሚደረግ ማንኛውም አዲስ ስምምነት በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ በኩል “ነፃ የነዳጅ ዘይት ፍሰት” መፍቀድን ማካተት አለበት ብለዋል ።
    • አሜሪካ የኢራን መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዳግመኛ ከዛቱ በኋላ የአሜሪካ ዘመቻ “ነፃነታቸውን ለማግኘት ለመሰቃየት ፈቃደኞች ለሆኑ” ኢራናውያን ጠቃሚ ነው ብለዋል።
  10. ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢራን ለጋዜጠኞች ምን አሉ?

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ዓመታዊ የትንሳዔ በዓል ላይ ተገኝተው የኢራን ጦርነትን በሚመለከት ምላሽ ሰጥተዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ምን አሉ?

    • ትራምፕ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ የኢራንን ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በድጋሚ ዝተዋል። “የማይከፍቱ ከሆነ ድልድይ አይኖራቸውም፤ የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም። ምንም አይኖራቸውም” ካሉ በኋላ “ከዚህ በላይ መሄድ አልችልም፤ ከእነዚህ ከሁለቱ በላይ የከፋ ነገር አለ” ብለዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የአሜሪካን ተዋጊ አውሮፕላን መትታ የጣለችው በክህሎት ሳይሆን “በአጋጣሚ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ሆኖም “አሁን ምናልባት በውስጣቸው ብዙ ጥይት ቀዳዳ ያላቸው አንዳንድ ሄሊኮፕተሮች አሉን” ብለዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም ያሉ ሲሆን፣ "እብዶች ናቸው እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በእብዶች እጅ ማስገባት አንችልም" ብለዋል።
    • አክለውም እንደ "እኔ ቢሆን ኖሮ የኢራንን ሰፊ የነዳጅ ዘይት ክምችት እወስድ ነበር" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው “በርካታ ገንዘብ አገኝበት ነበር” ብለዋል።
    • ትራምፕ በርካታ አሜሪካውያን በኢራን የሚያካሄዱትን ጦርነት ቢቃወሙም አሁንም ጦርነቱን የሚቃወሙ “ጅሎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
    • ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ድረስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ የመጨረሻው መሆኑን ተናግረው፤ ኢራን ለአሜሪካ ጦርነቱ እንዲያበቃ ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ የሰጠችውን ምላሽ “ወሳኝ” ነገር ግን “በቂ ያልሆነ” ሲሉ ገልጸውታል።
  11. ኢራን አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ዕቅድ ውድቅ አደረገች

    አምስተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢራን ጦርነት በርካታ ውድመቶች ተመዝግበዋል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ኢርና ቴህራን አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ ምላሽ መስጠቷን ዘገበ።

    እንደ ኢርና ዘገባ ከሆነ ኢራን የቀረበላትን የተኩስ አቁም ጥሪ በቋሚነት ጦርነቱን ማቆም አስፈላጊ ነው በሚል ውድቅ አድርጋለች።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቴህራን አሜሪካ ላቀረበችው የተኩስ አቁም ምክረ ሃሳብ ምላሿን በፓኪስታን በኩል ማስገባቷን ዘግበዋል።

    የዜና ወኪሉ ኢራን ለአሜሪካ ያቀረበችው ባለ አስር ነጥብ ምላሽ የተኩስ አቁምን ውድቅ የሚያደርግ እና በቋሚነት ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት መኖር አለበት የሚል መሆኑን ዘግቧል።

    ኢራን ለአምስት ሳምንታት የዘለቀው ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም በመጠየቅ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት የቀረበላትን የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ አድርጋለች።

    ኢራን ለአሜሪካ በሰጠችው ምላሽ ውስጥ "በቀጣናው ያለው ጦርነት እንዲቆም ፣ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ውስጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድን የሚያረጋግጥ አሰራር እንዲኖር፣ እንዲሁም መልሶ ግንባታ እና ማዕቀቦችን ማንሳትን እንዲካተቱ" የሚሉ ፍላጎቶቿን ዘርዝራለች።

    ኢርና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በተደጋጋሚ የጊዜ ገደብ በማራዘም ከቀድሞ ዛቻዎቻቸው ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን" አክሎ ዘግቧል።

    ትራምፕ እስከ ማክሰኞ ዕለት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፈት ከሆነ በቴህራን ላይ “ሲኦል” ይወርዳል ሲሉ “ድልድዮችን እና የኃይል ማመንጫዎችን” እንደሚያጠቁ ዝተዋል።

  12. ዩኤኢ የኢራን እርምጃ የባሕረ ሰላጤውን አገራት ወደ አሜሪካ የሚገፋ ነው አለች

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ በዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል

    የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ በዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን እና “በእኛ እና በሌሎች አገራት ላይ እየዘነበ ያለውን ሚሳዔል እና ድሮን” ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮችን መፍታት የማይችል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረግ አስጠነቀቀች።

    የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ በሰጡት መግለጫ አገራቸው ግጭቱ እንዲቆም እንደምትፈልግ ተናግረው ነገር ግን ወደፊት በቀጣናው ውስጥ ቀጣይነት ያለው አለመረጋጋትን የሚፈጥር እንዳይሆን ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በጥነምረት ጥቃት ከከፈቱባት ወዲህ ኢራን የዓለም ዋና የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዘግታለች።

    በየቀኑ በጣት የሚቆጠሩ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ብቻ በወሽመጡ የሚያልፉ ሲሆን ይህ ግን ከተለመደው ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።

    የኢራን ስትራቴጂ የባህረ ሰላጤውን አገራት ከዋሽንግተን ጋር ያላቸውን የደህንነት ትስስር ሊያጠናክር እና የእስራኤልን ተፅዕኖ በቀጣናው ላይ የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት "በእጥፍ" እንደምታሳድግም አክለው ተናግረዋል።

    “የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በማንኛውም አገር ታግቶ መያዝ አይችልም” ያሉት አማካሪው፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንደ የባህር ኃይል ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ባትሆንም፣ “በወሽመጡ ውስጥ የሚደረግ የባህር ጉዞን ለማረጋገጥ በአሜሪካ የሚመራ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ጥረት” ትቀላቀላለች ብለዋል።

  13. የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሰላማዊ ሰዎች መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት "ተቀባይነት የለውም" አሉ

    የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ

    የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ ማድረግ ሕገወጥ ነው አሉ። ፕሬዚዳንቱ አክለውም በኢራን ያለውን ጦርነት የሚያስቆመው “ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ብቻ ነው” ብለዋል።

    አንቶኒዮ ኮስታ በኤክስ ገጻቸው ላይ “የሲቪሊያን መሠረተ ልማቶችን በስም ለመዘርዘር የኤነርጂ ተቋማትን፣ ዒላማ ማድረግ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

    የፕሬዚዳንቱ መግለጫ የተሰማው ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም የማይከፈት ከሆነ የኢራናውያንን መሠረተ ልማቶች እንደሚያወድሙ ከዛቱ በኋላ ነው።

    የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መስራች ዋና አቃቤ ሕግ ሉዊስ ሞሪኖ ኦካምፖ ቀደም ሲል ለቢቢሲ በኢራን የሚደረገው ጦርነት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ በሆነ መልኩ አንድ አገር ላይ ጥቃት የመክፈት ወንጀል ጋር ይስተካከላል ብለዋል።

    ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች አሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥሱ ነገሮችን ሲያደርጉ መመልከታቸውን በመግለጽ ያ "በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው" የሚገልጽ ግልጽ ደብዳቤ ፈርመዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ማርቭዳሽት የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ “በጠላት ጥቃት” ዒላማ ተደርጓል ሲሉ ዘግበዋል።

    የፋርስ ዜና ወኪል ጥቃቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን ዘግቧል።

    የታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ የማርቭዳሽት ካውንቲ አስተዳዳሪ ቢሮን ጠቅሶ በኢንዱስትሪው ላይ “ይህ ነው የሚባል ጉዳት አልደረሰም” ብሏል።

    ቀደም ሲል እስራኤል በደቡብ ኢራን በአሳሉያህ በሳውዝ ፓርስ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተናግራ ነበር።

  14. ዛሬ ሰኞ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ነገሮች

    በቤይሩት ትልቁ ሆስፒታል አቅራቢያ የእስራኤል ጦር የፈጸመው የአየር ድብደባ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, በቤይሩት ትልቁ ሆስፒታል አቅራቢያ የእስራኤል ጦር የፈጸመው የአየር ድብደባ
    • እስራኤል በአሳሉዬህ የሚገኘውን የኢራን ቁልፍ የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ መደብደቧን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ገለፁ።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን በርካታ የምርት ክፍሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ዘግበዋል፤ ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም።
    • እስራኤል ጥቃቱን የፈጸመችው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በኢራን መሠረተ ልማት ላይ ትልቅ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።
    • ኢራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚያልፍበትን ሆርሙዝ እንደገና ካልከፈተች ማክሰኞ ዕለት "የኃይል ማመንጫ እና የድልድይ ቀን" ይሆናል ብለዋል።
    • ይህ በእንዲህ እንዳለ በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን፣ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የኢራን አብዮታዊ ዘብ የደኅንነት ኃላፊን መግደሉን ተናግሯል።
    • በሰሜን እስራኤል አራት ሰዎች የኢራን ጥቃትን ተከትሎ ሲገደሉ በሊባኖስ የማያቋርጥ የውጊያ ጄቶች ድምፅ እየተሰማ መሆኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።
  15. እስራኤል የሄዝቦላህ አመራርን ለመግደል በፈጸመችው ጥቃት በስህተት ቡድኑን የሚቃወም ፖለቲከኛ ተገደለ

    በአብዛኛው ክርስትያኖች በሆኑ ግለሰቦች የተዋቀረው የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ፒየር ሞኡዋድን

    የፎቶው ባለመብት, Lebanese Forces Party

    የምስሉ መግለጫ, በአብዛኛው ክርስቲያኖች በሆኑ ግለሰቦች የተዋቀረው የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ፒየር ሞኡዋድን

    እስራኤል እሁድ ዕለት በሊባኖስ የሄዝቦላህ አባልን ለመግደል ባደረገችው ሙከራ በስህተት ቡድኑን አጥብቆ የሚቃወም ከፍተኛ የፖለቲካ ቡድን መሪ ተገደለ።

    በጉዳይ ላይ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ጥቃቱ የታሰበውን ዒላማ መግደል እንዳልቻለ ገልጾ፣ በሲቪሎች ላይ “ለደረሰው ጉዳት መጸጸቱን" ገልጿል።

    በአብዛኛው ክርስቲያኖች በሆኑ ግለሰቦች የተዋቀረው የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ፣ በአንድ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር ፒየር ሞኡዋድን እና ባለቤቱን ፍላቪያን እንደገደለ አስታውቋል።

    የመኖሪያ ሕንጻው የሚገኘው ከቤይሩት በስተምሥራቅ በምትገኘው አይን ሳዴህ በምትባል በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች መኖሪያ በሆነችው ከተማ ውስጥ ነው።

    የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ጥቃቱ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶችን እንደገደለ አስታውቋል።

    የአካባቢው ከንቲባ ሟቾቹ ይኖሩ የነበረው ከዒላማው በታች ባለ አንድ ፎቅ ውስጥ ነበር ብለዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "በርካታ የማይመለከታቸው ግለሰቦች በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው መመልከት ችለናል" ብሏል።

    የሊባኖስ ኃይሎች ፓርቲ ፒየር ሞአዋድ "ተዋጊም ሆነ ወታደራዊ ዒላማ አልነበረም" ካለ በኋላ ከአሰቃቂው ጥቃት በፊት ከቤተሰቡ ጋር የትንሳዔ በዓልን እያከበረ እንደነበር ተናግሯል።

    ፓርቲው ሄዝቦላህን አውግዞ ጥቃቱ የተከሰተው ወታደራዊ ግጭቶች ወደ መኖሪያ መንደሮች ዘልቀው እየመጡ በመሆናቸው ነው ብሏል።

  16. እስራኤል የኢራን ቁልፍ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካን መደብደቧን አስታወቀች

    ይህ እአአ በ2014 ምስል በኢራን በአሳሉዬህ አቅራቢያ፣ በካንጋን ከተማ የሚገኘውን የደቡብ ፓርስን የጋዝ መስክ ያሳያል። የኢዝራኤል ካትዝ መግለጫ አዲሱ ጥቃት የተፈፀመበትን ትክክለኛ ቦታ አልገለጸም።

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ይህ እአአ በ2014 ምስል በኢራን በአሳሉዬህ አቅራቢያ፣ በካንጋን ከተማ የሚገኘውን የደቡብ ፓርስን የጋዝ መስክ ያሳያል። የኢዝራኤል ካትዝ መግለጫ አዲሱ ጥቃት የተፈፀመበትን ትክክለኛ ቦታ አልገለጸም።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በኢራን የፔትሮኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ላይ ድብደባ መፈጸሙን ገለጹ።

    ሚኒስቴሩ አክለውም ጦሩ “በሙሉ ኃይሉ” የኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንዲቀጥል ታዝዟል ብለዋል።

    “የእስራኤል መከላከያ በኢራን ግዙፉ የሆነውን እና [በአሳሉያህ] የሚገኘውን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽሟል ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በሌላ ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጨምረው ገልጸዋል።

    “ለኢራን የፔትሮኬሚካል የውጭ ንግድ በጥምረት 85 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል ስለዚህ አገልግሎት አይሰጡም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

    ካትዝ አክለውም በአሳሉያህ የሚገኘው ፋብሪካ የአገሪቱን ግማሽ የፔትሮኬሚካል ምርቶች የሚያመርት ነበር ብለዋል።

    ታስኒም የዜና ወኪል በበኩሉ ሁለት የፔትሮኬሚካል ኩባንያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዘግቧል።

    ካትዝ የኢራን ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ ጥቃት መፈጸሟን የገለጹት የፋርስ የዜና ወኪል በአሳሉያህ ከሚገኘው በሳውዝ ፓርስ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ብዙ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

  17. ኢራን በእስራአል ሃይፋ አካባቢ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

    በእስራኤል ሚሳዔል የተመታው አካባቢ

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የኢራን ሚሳዔል በሃይፋ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ አራት ሰዎች መግደሉ ተገለጸ።

    የጸጥታ አካላት ቦምቡ ከወደቀ በኋላ ባለመፈንዳቱ የሕይወት አድን ሠራተኞችን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ገልጸዋል።

    እንደ የእስራኤል ባለሥልጣናት ገለጻ በጥቃቱ የተመታው ቤት ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎችን ለማውጣት የጎረቤት ግድግዳን መሰርሰር አስፈልጎ ነበር።

    ጥቃቱ ከደረሰበት ሕንጻ ማዶ የምትኖረው ሞር ባረል፣ የእስራኤል በርካታ የአየር መቃወሚያዎች እያሉ እንኳን የኢራንን የሚሳዔል ጥቃት እያሰጉ መኖር በአደጋ የታጀበ ነው፤ ምናልባት ደህንነትህ የተጠበቀ ወይንም በማንኛውም ሰኮንዶች ለአደጋ እንደመጋለጥ ያለ የሕይወት ቁማር ነው ብላለች።

    እስራኤል የቴህራንን ባሌስቲክ ሚሳዔል መምታት በመቻሏ ውጤታማ አንደሆነች ብትገልጽም ኢራን ግን ዒላማ የምታደርገው የእስራኤልን የደህንነት ስሜት ነው ሲሉ ነዋሪዎቿ በምሬት ይናገራሉ።

    ያንን ደግሞ አንድ ሕንጻ ላይ በሚፈጸም ጥቃት መምታት ይቻላል ሲሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

  18. ኢራን በኩዌት የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

    ኢራን በኩዌት ከዚህ ቀደም 'የደረሰባቸውን ጥቃት በመሸሽ' ወደ ቡቢያን ደሴት የተወሰዱ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

    የአሜሪካ ጦር ኩዌት ወደሚገኘው ቡቢያን ደሴት ከተወሰደ በኋላ የኢራን ሚሳዔል ዒላማ መሆኑን የቴህራን ባለሥልጣናት በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለት የኢራን ካታም አል አንቢያ ዋና መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በቪዲዮ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በደሴቱ ላይ የሚገኙ የሳተላይት እና ጦር መሣሪያዎችን መምታታቸውን ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ኢብራሂም ዞልፋቅሪ ጥቃቱን የፈጸሙት በድሮን በመታገዝ መሆኑን መግለጻቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ ወታደሮቿን ከዚህ ቀደም የነበሩበት አሪፍጃን የጦር ሠፈር በቴህራን ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ወደ ደሴቲቱ ማዛወሯን ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

    ቡቢያን የኩዌት ትልቁ ደሴት ሲሆን በባሕረ ሰላጤው ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ላይ ይገኛል።

    ኢራን በኩዌት ላይ የሚሳዔል ጥቃት ከፈጸመች በኋላ በስብርባሪዎች ስድስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር።

  19. ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ለአሸማጋዮች ምላሽ ማዘጋጀቷን አስታወቀች

    የፓኪስታን  ጦር አዛዥ ባለፈው መስከረም ወር በዋይት ሐውስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በድርድሩ ላይ የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር (መሐል ላይ) መሪ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተዘግቧል

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የእስራኤል-አሜሪካ እና የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት እየሠሩ ላሉ አሸማጋዮች ቴህራን ምላሽ ማዘጋጀቷን ተናገሩ።

    ይህ የኢራን አስተያየት የመጣው ሮይተርስ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳቸው ምንጮች ፓኪስታን ጦርነቱን ለማስቆም አዲስ ዕቅድ በመንደፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው የሚል ዘገባ ካወጣ በኋላ ነው።

    በኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዋቢ የተደረጉት እስማኤል ባጊ በአሸማጋዮች በኩል የቀረበው የአሜሪካ ባለ 15 ነጥብ ዕቅድ “በምንም መንገድ ለእኛ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

    ጦርነቱን ለመቋጨት ያለሙ ድርድሮች “የጦር ወንጀል ለመፈፀም በማስጠንቀቂያ እና በዛቻ የተሞሉ ናቸው” ሲሉ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ቃል አቀባዩ ይልቁንም “በራሳችን ፍላጎት እና ግምገማ” ኢራን አቋሟን የምታሳውቅበትን ሰነድ አጠናቅራለች ብለዋል።

    “ከመጀመሪያው ጀምሮ ምን እንደምንፈልግ እና እንዲታለፉ የማንፈቅዳቸው ቀይ መስመሮች ምን እንደሆኑ እናውቃለን። እናም አሁንም አቋማችን ግልፅ ነው። ይህ ንግግር ከተጀመረበት ቅፅበት አንስቶ መልሶቻችን ዝግጁ ነበሩ” በማለት ኢራን የራሷን ምላሽ ማዘጋጀቷን ጠቁመው፤ “ጊዜው ሲደረስ ዝርዝሩን እናሳውቃለን” ሲሉ አክለዋል።

    ሮይተርስ እና አክሲዮስ የተኩስ አቁም ዕቅድ ለአሜሪካ እና ለኢራን መቅረቡን ዘግበዋል

    እስካሁን የምናውቀው፦

    እንደ ዘገባዎች ከሆነ የቀረበው ዕቅድ ሁለት ደረጃዎች አሉት። ዕቅዱ አፋጣኝ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚል ሲሆን፤ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ የተጠናከረ ስምምነት ይከተለዋል። የአሜሪካው የዜና ምnእጭ አክሲዮስ አደራዳሪዎች የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መምከራቸውን ጠቁሟል።

    እንደ አክሲዮስ ከሆነ በድርድሩ ፓኪስታን፣ ግብፅ እና ቱርክ እየተሳተፉ ነው። የፓኪስታን የጦር አዛዥ አሲም ሙኒር “ምሽቱን ሙሉ” ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር መረጃ ሲለዋወጡ እንደነበር ሮይተርስ የዜና ወኪል አክሏል።

    አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አካል መሆኑን ውድቅ አድርገዋል።

    የድርድር ወሬዎች እየተሰሙ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን እንድትከፍት እስከ ማክሰኞ ቀነ ገደብ መጣላቸውን ተከትሎ ነው።

    እስከአሁን የማናውቀው፦

    የተኩስ አቁም ዕቅዱን በተመለከተ የኢራን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስተያየት እየተጠበቀ ነው።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ የጥቃቶች ዛቻ እና የኒውክሌር መርሃ ግብርን የመሰሉ ቁልፍ የጦርነቱ ማጠንጠኛ ነጥቦች በስምምነቱ እንዴት እንደታዩ አይታወቅም።

    አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ከዚህ ቀድም ያልተሳኩትን የስምምነት ዕቅዶች ለአብነትም ባለ 15 ነጥቡን የአሜሪካ የስምምነት ሃሳብ ምን ያህል እንደሚያንፀባርቅ አይታወቅም።

    በጦርነቱ በርካታ ጥቃቶች እየተፈፀመባቸው ያሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት በዚህ ስምምነት እንዴት እንደታዩም የሚታወቅ ነገር የለም።

    በሁለቱም ወገኖች ምላሽ ለመስጠት የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ ስለመኖሩም እንዲሁ።

  20. ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተጠቁ “የማያዳግም” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንደዛቱት በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ “የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ” ምላሽ እንደምትሰጥ ኢራን አስጠነቀቀች።

    ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማክሰኞን በቀነ ገደብነት ካስቀመጡ በኋላ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በአገራቸው ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ ምላሻቸው ከባድ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

    አራግቺ “ያለጥርጥር [አሜሪካ] ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጦር ኃይሎች የማያዳግም እና ሁሉን አቀፍ ምላሽ ይጠብቃታል” በማለት ለፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን-ኖዌል ባሮት ተናግረዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረውም የአሜሪካ ዛቻ “የጦር ወንጀልን እና የዘር ማጥፋትን ተቀባይነት የሚያደርግ ነው” በማለት ከስሰዋል።

    ከፈረንሳዩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ስለተደረገው ውይይት በኢራን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል የወጣው ዘገባ ላይ ባሮት በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በቀጣናው ያለውን ውጥረት የሚያባብስ መሆኑን በመጥቀስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲደረግ ጠይቀዋል።