የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ ፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሳዑዲ አረቢያን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካዎችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ከፍተኛ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።
በጥቃቱ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአሜሪካ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ በመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች እና በአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች “የተሳካ ጥቃት” መፈጸሙን አመለክቷል።
ዘቡ እንዳለው ከተቋማቱ በተጨማሪ “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጥቅሞች እና ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላት” ዒላማ መሆናቸውን ገልጿል።
በመግለጫው ላይ ኢራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ሰኞ ዕለት “በአሳሉዬህ የፔትሮኬሚካል ማዕከል” ላይ የተፈጸመባትን ጥቃት ለመበቀል መሆኑ ተጠቅሷል።
አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ “ቀይ መስመራችንን የምታልፍ ከሆነ ምላሻችን ከመካከለኛው ምሥራቅም የሚያልፍ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ እና አጋሮቿ ኢራን ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች ውስን ሆነው ቆይተው” የነበረ መሆኑን ገልጿል።
ይህ ለመልካም ጉርብትና ሲባል ኢራን አሳይታው የነበረው “ቁጥብነት” ዒላማዎችን እንድትለይ አድርጓት መቆየቱን፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ “ይህ ቁጥብነት እንደማይኖር” በመጥቀስ አስፈላጊ በተባሉ ዒላማዎች ላይ “ያለማወላወል” እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።

















