ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአገራቸው የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እየቀረበባቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዳንት ትራምፕ ኢራን ከተቀመጠላት የጊዜ ገደብን በፊት ስምምነት ላይ ካልሰደረች “ሥልጣኔዋ በአንድ ሌሊት ያከትማል” ማለታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
በተለይ የትራምፕ ፓርቲ ተቀናቃኝ የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴዎች በቶሎ መፍትሄ እንዲፈለግ እየጠየቁ ነው።
በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር "ይህ ግለሰብ በጣሙን የታመመ ሰው ነው። ይህንን የግድየለሽነት ጦርነት ለመቃወም ፈቃደኛ ያልሆኑ እያንዳንዳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ለትኛውም ዓይነት አስከፊ ዳፋ ኃላፊነት አለባቸው" ሲሉ ሪፐብሊካንን ወቅሰዋል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪው ሐኪን ጄፍሪስ በበኩላቸው "ዶናልድ ትራምፕ በግዴለሽነት የገባበት የኢራን ጦርነት ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሳያስገባን በፊት ምክር ቤቱ ማስቆም አለበት። ይህንን እብደት በማስቆም በኩል ሁሉም ሪፐብሊካኖች ብሔራዊ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።
የምክር ቤት አባሉ ጄሰን ክሮው ደግሞ የአንድን አገር "ሥልጣኔን ለማጥፋት መዛት የጦር ወንጀል ነው። በተደጋጋሚ እንዳልኩት ጦር ሠራዊታችን ሕጋዊ ትዕዛዞችን ብቻ ነው መከተል ያለበት። መልካም ህሊና ያላቸው ሁሉም አሜሪካውያን ይህንን ድርጊት መቃወም አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል ጂም ማክጋቨርን “ይህ የለየለት ክፋት ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የጦር ወንጀል ለመፈጸም የሚሰነዝረው የዘር ማጥፋት ዛቻ በፌደራል እና በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ነው" በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር ነቅፈዋል።

















