በሆርሙዝ ላይ ለተመድ የቀረበው ውሳኔ በሩሲያ እና በቻይና ውድቅ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለሆርሙዝ ወሽመጥ በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግ በባሕረ ሰላጤው አገራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሩሲያ እና በቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ውድቅ ሆነ።
ከምክር ቤቱ አባለት አስራ አንዱ የውሳኔ ሃሳቡን ሲደግፉ፣ ፓኪስታን እና ኮሎምቢያ ድምጻቸውን አቅበዋል፤ ሩሲያ እና ቻይና ስለተቃወሙት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
የውሳኔ ሃሳቡ ረቂቅ ላይ ለሳምንታት ድርድር ሲደረግ ቆይቶ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ወታደራዊ ኃይል መጠቀምን የሚፈቅደው ክፍል እንዲቀር ተደርጎ አገራት የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ በሚል ተለውጦ ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስሰብባን የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አብዱላጢፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ በሰብሳቢነት መሩት ነበር።
ሰብሳቢው ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት የውሳኔ ሃሳቡ አዲስ ሁኔታን የሚፈረር ሳይሆን፣ በሆርሙዝ ላይ ኢራን የፈጠረችውን ተደጋጋሚ ችግር ለማስቆም አስፈላጊ በመሆኑ የቀረበ ነው ሲሉ አስረድተው ነበር።
የውሳኔ ሃሳቡ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ መስመሮችን በመሳሪያነት መጠቀምን በማበረታታት ከሆርሙዝ ባሻገር በሌሎችም ቦታዎች እንዲደገም በማድረግ ዓለምን ወደ ሕግ አልነባት ያሸጋግራታል ብለዋል።
ውሳኔውን ድምጽን በድምጽ በመሻር ውድቅ ያደረጉት ቻይና እና ሩሲያ በሆርሙዝ መዘጋት እምብዛም ችግር እንዳልገጠማቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ቻይና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦቻቸው ያለችግር መተላለፍ ከቻሉ አገራት መከካል እንዷ ስትሆን፣ ሩሲያ ደግሞ ተጥሎባት የነበረው የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት ላልቶላታል።

















