በኢራን እስር ቤት ከሦስት ዓመት በላይ የቆዩት ፈረንሳውያን ጥንዶች አገሪቱን ለቅቀው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን ውስጥ የስለላ ክስ ቀርቦባቸው ከሦስት ዓመት በላይ የሚሆን ጊዜ በእስር ቤት ያሳለፉ ፈረንሳውያን ጥንዶች ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
የ41 ዓመቷ ሴሲል ኮህለ እና የ72 ዓመቱ ዣክ ፓሪስ እአአ የስለላ ክስ ቀርቦቸባው በቁጥጥር ስር የዋሉት በግንቦት 2022 ኢራን ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ሳለ ነበር። ጥንዶቹ ቴህራን በሚገኘው በታዋቂው የኤቪን እስር ቤት የታሰሩ ሲሆን ፈረንሳይ ክሱን መሠረተ ቢስ ስትል ገልጸዋለች።
በህዳር ወር ቢፈቱም በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ውስጥ በቁም እስር ቆይተዋል።
ማክሮን ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ "ይህ [ዜና] ለሁላችንም፤ በተለይም ለቤተሰቦቻቸው እፎይታ ነው" ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም ለኦማን "የሽምግልና ጥረት" ምስጋና አቅርበዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት ጥንዶቹ ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከፈረንሳይ አምባሳደር ጋር በዲፕሎማሲያዊ ከለላ ከኢራን ወጥተው ወደ ጎረቤት አገር አዘርባጃን ተጉዘዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን-ኖኤል ባሮ በበኩላቸው ስለጥንዶቹ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም "በመጨረሻም ነጻ" እንደወጡ እና በስልክ እንዳነጋገሯቸው ተናግረዋል።
"በቅርቡ ከአገራቸው እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደገና ሊያገኙ በመሆኑ ስሜታቸውን እና ደስታቸውን ነግረውኛል" ሲሉ ኤክስ ላይ ጽፈዋል።
የፓሪስ ልጅ አን-ሎሬ ፓሪስ በበኩሏ "ወደ ፈረንሳይ እስኪመለሱ እና እቅፍ እስከምናደርጋቸው እየጠበቅን ነው" ስትል ለኤኤፍፒ ገልጻለች።
ለፈረንሳይ እና ለእስራኤል ትስልላላችሁ የሚል ክስ መመስረቱን ተከትሎ ጥቅምት ላይ የኢራን ፍርድ ቤት ፓሪስ ላይ የ17 ዓመት፤ ኮለር ላይ ደግሞ የ20 ዓመት ፍርድ አስተላልፏል።
ሁለቱ ግለሰቦች የተፈቱት፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ፈረንሳውያንኑን ማህዲህ ኤስፋንዲያሪ በተባለች ኢራናዊት እስረኛ ለመለዋወጥ የተደረገው ስምምነት ሊጠናቀቅ ተቃርቧል ካሉ በኋላ ነው።
በወቅቱ ኮለር እና ፓሪስ የዚህ ስምምነት አካል ሆነ ሊፈቱ እንደሚችሉ ኢራን ብትገልጽም የፈረንሳይ መንግሥት ስለጉዳዩ እውነተኝነት አላረጋገጠም።
ኤስፋንዲያሪ በየካቲት ወር በማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ላይ ሽብርተኝነትን በማወደስ ጥፋተኛ ተብላለች። በየካቲት 2025 በፈረንሳይ ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መያዟን የኢራን ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
የእስፋንዲያሪ ጠበቃ ማክሰኞ ዕለት ለኤኤፍፒ እንደገለጹት የደንበኛቸው የፈረንሳይ የቁም እስር ኮህለ እና ፓሪስ ኢራንን ለቀው እንዲወጡ በመፈቀዱ አብቅቷል።
የኢራን የመንግስት የዜና ወኪል ኢርና እንደዘገበው የኮህለ እና የፓሪስ መፈታት በፈረንሳይ እና በኢራን መካከል በተደረገው ስምምነት አካል መሆኑን እና ኤስፋንዲያሪ ሙሉ በሙሉ መልቀቋን አትቷል።
የፈረንሳይ መንግስት ስለ ስምምነቱ አስተያየት ባይሰጥም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦች "ይህንን ውጤት ለማሳካት" ስላከናወኑት "የረዥም ጊዜ ሥራ" ባሮ ጠቅሰዋል።
"እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የዜጎቻችንን ደህንነት እና ከኢራን በሰላም መውጣታቸውን ላረጋገጡት አምባሳደራችን እና ባልደረቦቻቸው ምስጋና እናቀርባለን" ሲሉ አክለዋል።
የፈረንሳውያኑ መፈታት መረጃ ተሰማው በየካቲት መጨረሻ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ሰፊ ጥቃት ከፍተው በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
ቴህራን በባህረ ሰላጤው በሚገኙ የእስራኤል እና የአሜሪካ ተባባሪ አገራት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ምላሽ ሰጥታለች። ውጊያው በፍጥነት ተባብሶ ወደ ሊባኖስ የተዛመተ ሲሆን በሁሉም ወገኖች በኩል የሟቾች እና የጉዳት መጠን ጨምሯል።
ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት አሜሪካ በአካባቢው የምታደርገው አንዳንድ ዘመቻዎች ቢደግፉም ግን እስካሁን ድረስ ወደ ግጭቱ ተስበው አልገቡም።












