አሜሪካ እና እስራኤል ብዙዎቹን የኢራን መሪዎችን ገድለዋል፤ ትራምፕ ከማን ጋር ሊደራደሩ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ጦር ያለምንም ተጨማሪ ፈቃድ የትኛውንም የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ዒላማ እንዲያደረግ መታዘዙን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ተናግረዋል።
ይህንን ያሉት ጦሩ የቴህራን የደኅንነት እና የስለላ ሚኒስቴሮችን፤ አሊ ላሪጃኒ እና እስማኤል ኻቲብን መግደሉን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው።
ካትዝ "ጠቅላየ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና እኔ ጦሩ ለደኅንነት እና ለውሳኔ ሰጪ አካል ቅርብ የሆነን የኢራን ባለሥልጣን ያለምንም ተጨማሪ ፈቃድ እንዲያስወግድ ፈቃድ ሰጥተናል" ብለዋል።
ነገር ግን እነዚህ ባለሥልጣናት በኢራን የሥልጣን ተዋረድ ውስጥ ምን ያሀል ወሳኝ ሚና ነበራቸው? አሁን አገሪቱን በበላይነት እያስተዳደረ ያለው ማን ነው?

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ - ጠቅላይ መሪ [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, IRANIAN LEADER PRESS OFFICE / HANDOUT via Getty
አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በከፈቱበት የመጀመሪያው ቀን የጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደል ብዙዎችን ያስደነገጠ ሆኗል።
የ86 ዓመቱ አዛውንት እአአ በ1979 የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን የመሠረቱትን አያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒን ከተኩ በኋላ ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል አገሪቱን መርተዋል።
ኻሜኒ የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ እና የጦር ኃይሎች እንዲሁም የአብዮታዊ ዘቡ ዋና አዛዥ በመሆን በኢራን ውስጥ ከፍተኛውን ሥልጣን ነበር።
ምንም እንኳን ማንኛውንም ፖሊሲ ውድቅ ማድረግ እና ባለሥልጣንን በፈቃዳቸው መሾም ቢችሉም አምባገነን የሚባሉ መሪ አልነበሩም።
እጅግ ውስብስብ እና ተፎካካሪ በሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በመሆን አገሪቱን የመሩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፤ በኢራን ለውጥ ፈላጊዎች እና በወግ አጥባቂዎች መካከል ባለ ውዝግብ መካከል ተረጋግተው አገሪቱን መርተዋል።
ነገር ግን ኻሜኒ የተቃውሞ ድምጾች እንዲሰሙ ወይም ውድቅ ያደረጓቸው ፖሊሲዎች እንዲረቀቁ አልፎ አልፎ ይፈቅዳሉ።
ሞጅታባ ኻሜኒ - ጠቅላይ መሪ [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን ተክተው ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝብ ታይተው፣ በቪዲዮ ተቀርጸው ወይም ፎቶግራፍ ተነስተው አያውቁም።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ አዲሱ ጠቅላይ መሪ ቴህራን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወላጆቻቸው እና ወንድማቸው በተገደሉበት ወቅት "ቆስለዋል ምናልባትም አካላቸው ጎድሏል" ብለዋል።
ሞጅታባ ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ በተነበበው የመጀመሪያ መግለጫቸው የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በጦርነቱ የተገደሉ ዜጎቻቸውን ደም "እንደሚበቀሉ" ዝተዋል።
አሊ ላሪጃኒ - የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ም/ቤት ፀሐፊ [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, COURTNEY BONNEAU/Middle East Images/AFP via Getty Images
አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት ከልጃቸው ጋር የተገደሉት የ68 ዓመቱ አሊ ላሪጃኒ ከኻሜኒ ሞት በኋላ ከተገደሉ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን መካከል አንዱ ናቸው።
የቀድሞ የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ እአአ በ2004 ለኻሜኒ የደኅንነት አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ለአስር ዓመታት ያገለገሉት የኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ብሮድካስት ኃላፊ በመሆን ነው።
ላሪጃኒ ከ2005-07 የኢራን ዋና የኒውክሌር ተደራዳሪ ነበሩ።
ነገር ግን በወቅቱ ከፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።
ለ12 ዓመታት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ይህም ከየትኛውም ተሿሚ በላይ በኃላፊነቱ ላይ የቆዩ ያደርጋቸዋል።
ላሪጃኒ በጠቅላይ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ኻሜኒን የሚወክሉ ሲሆን፣ በታኅሣሥ እና ጥር በኢራን በተካሄደው ተቃውሞ ላይ የባሲጅ ሚሊሻ ኃይሎችን ጨምሮ ተቀቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጠንካራ እርምጃ መውሰዳቸው በስፋት ይገለጻል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በእነዚህ የተቃውሞ ሠልፎች ቢያንስ 6,508 ሰዎች ሲገደሉ 53,000 ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የኢራን የመከላከያ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሪር አድሚራል አሊ ሻምኻኒ [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የኢራን የደኅንነት እና የኒውክሌር ፖሊሲ አውጪ ቁልፍ ሰው እና ብቸኛው የኢራን ሪር አድሚራል የነበሩት የኻሜኒ የቅርብ አማካሪ አሊ ሻምኻኒ የካቲት 21 በቴህራን ላይ በተፈፀመው ጥቃት ተገድለዋል።
ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ለ12 ቀናት በእስራኤልእና በኢራን መካከል በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቤታቸው ላይ ከተፈፀመው ጥቃት በሕይወት ተርፈዋል።
በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት ሻምኻኒ ከአብዮታዊ ዘብ አዛዦች መካከል አንዱ ነበሩ።
ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ውስጥ በርካታ ቁልፍ ኃላፊነቶችን ተረክበው ሠርተዋል።
ከእነዚህም መካከል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የባሕር ኃይል አዛዥ እና የጠቅላይ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ የተካሄዱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በማፈን ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ ፓክፑር - የአብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images
ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ፓክፑርም በየካቲት 21 በቴህራን ላይ በተፈፀመው ጥቃት መገደላቸውን የኢራን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ለ16 ዓመታት የአብዮታዊ ዘብ የምድር ጦር አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ጄነራሉ የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ የነበሩት ሆሴይን ሳላሚ በ12 ቀኑ ጦርነት ከተገደሉ በኋላ ቦታቸውን ተረክበዋል።
ማሱድ ፔዜሽኪያን - ፕሬዝዳንት [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, IRANIAN PRESIDENCY / HANDOUT via Getty
የለውጥ አቀንቃኙ ማሱድ ፔዜሽኪያን በ12 የሃይማኖት ሊቃውንት እና የሕግ ባለሙያዎች የሚመራው ምክር ቤትን የማጣሪያ ሂደት በማለፍ በሐምሌ 6/2024 የኢራን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
የ71 ዓመቱ የቀድሞ የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ እና የኢራን ፓርላማ አባል የአገሪቱን ዝነኛ የሥነ ምግባር ፖሊስ በመተቸታቸው ይታወቀሉ።
እንዲሁም "ኅብረት እና አንድነት" ለማምጣት፣ ኢራን ከዓለም መገለሏ እንዲያበቃ እንደሚያደርጉ ቃል ከገቡ በኋላ ትኩረት ስበዋል።
መጋቢት 11 2026 ፔዜሽኪያን በኤክስ ገጻቸው ላይ ኢራን "በአካባቢው ሰላም ላይ ያላትን ቁርጠኝነት" አረጋግጠው ጽፈዋል።
ከአምስት ቀናት በኋላ "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ጦርነት እንዲያወግዝ" ሲሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ "ወራሪዎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲያከብሩ እንዲያሳምን እንጠብቃለን" በማለት በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ - የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ የአብዮታዊ ዘብ ደንብ ልብሳቸውን በሲቪል ልብስ በመቀየር የሥርዓቱ ቀልፍ ሰው ሆነዋል።
የአውሮፕላን አብራሪ የሆኑት አፈ ጉባዔው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን ብርቱ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ አራት ጊዜ ተወዳድረው ተሸንፈዋል።
የ64 ዓመቱ ጋሊባፍ አሁንም ጦርነቱን በመምራት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ይመስላል።
በኢራን የኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ዐይን ላጠፋ ዐይን የሚለው መርኅ ተግባራዊ ሆኗል፣ አዲስ የግጭት ምዕራፍ ተጀምሯል" ሲሉ ጽፈዋል።
ማክሰኞ መጋቢት 24/2026 ጋሊባፍ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ንግግር ስለመጀመሯ የወጡ ሪፖርቶችን ተከትሎ ደግሞ "ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አልተደረገም፤ ይህ የሐሰት መረጃ የፋይናንስ እና የነዳጅ ገበያዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም አሜሪካ እና እስራኤል ከገቡበት ማጥ ለመውጣት እየተጠቀሙበት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም "የኢራን ሕዝብ አጥቂዎቹን የተሟላ እና ጸጸት ውስጥ በሚከት ሁኔታ መቅጣት ይፈልጋል። ይህ ግብ እስኪሳካ ድረስ ሁሉም የኢራን ባለሥልጣናት ከጠቅላይ መሪያቸው እና ከሕዝባቸው ጎን በጽናት ይቆማሉ" ብለዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ጎላምሬዛ ሱሌይማኒ - የባሲጅ አዛዥ [የተገደሉ]
የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አንደዘገቡት የባሲጅ አዛዥ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ጎላምሬዛ ሱሌይማኒ መጋቢት 17/2026 በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈፀመው ጥቃት ተገድለዋል።
ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሬዛ ራዳን - የፖሊስ አዛዥ [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images
የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሬዛ ራዳን ጥብቅ የማኅበራዊ ሕጎችን የማስከበር እና ተቃውሞዎችን የማፈን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 የሂጃብ ሕግን የሚጥሱ ሴቶችን ለመለየት እና ለመቅጣት በሚል የክትትል ካሜራዎችን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመውን 'ዕቅድ' ይፋ አድርገዋል። ይህንን ሕግ ጥሰው የሚገኙ መኪናቸው ይወረሳል የንግድ ተቋሞቻቸውም ይዘጋሉ።
በቅርቡ ደግሞ ራዳን በተቃዋሚዎች ላይ ጠንከር ያለ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት ላይ ፖሊስ "በጠላት ጥያቄ" ወደ ጎዳና የሚወጣን ማንኛውንም ሰው "እንደ ጠላት" እንደሚመለከተው አስጠንቅቀዋል።
ጎላምሆሴይን ሞህሴኒ ኢጄይ - ዋና ዳኛ [በሕይወት ያሉ]
የኢራን ዋና ዳኛ ጎላምሆሴይን ሞህሴኒ ኤጄይ በጥር ወር ከጦርነቱ ቀደም ብሎ በተደረጉ ተቃውሞዎች ወቅት በአመፅ ድርጊቶች የተከሰሱ ሰዎችን በተመለከተ "ምንም ዓይነት ምህረት" እንደማይኖር አስጠንቅቀዋል።
ብርጋዴር ጄነራል እስካንዳር ሞሜኒ - የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር [በሕይወት ያሉ]
ከአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2024 ጀምሮ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል እስካንዳር ሞሜኒ ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ሪፐብሊክ ዘብ እና ከፖሊስ ዕዝ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው።
ብርጋዴር ጄነራል ኢስማኤል ቃኒ በእስላማዊ ዘብ የቁድስ ኃይል አዛዥ [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, Fatemeh Bahrami/Anadolu via Getty Images
በኢራን መገናኛ ብዙኃን "የሌቫንት ጄነራል" በመባል የሚታወቁት ብርጋዴር ጄነራል ኢስማኤል ቃኒ በ2020 በአብዮታዊ ዘብ የቁድስ ኃይል አዛዥ ሆነው ተሾሙ።
በአውሮፓውያኑ 2012 የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ በተለይም በጋምቢያ ለሚገኙ የቁድስ ኃይል አባላት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እና የጦር መሳሪያ በማቅረባቸው ማዕቀብ ጥሎባቸዋል።
ኢስማኤል ኻቲብ - የስለላ ሚኒስትር [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, ABEDIN via EPA
ኢስማኤል ኻቲብ በ2021 በአደጋ በሞቱት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ የኢራን የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
አሊ ኻሜኒን ጨምሮ በበርካታ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች ስር የእስልምና ሕግ ተምረዋል።
እንዲሁም በኢራን የስለላ ሚኒስቴር እና በጠቅላይ መሪው ቢሮ ውስጥ የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን የኻቲብ ሞትን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት የእስራኤል የአየር ጥቃት ኢራንን "በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል" ብለዋል።
ሜጀር ጄነራል አብዶራሂም ሙሳቪ - የኢራን የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም [የተገደሉ]

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ኢራን የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አብዶራሂም ሙሳቪ ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር አገራቸው ከእስራኤል ጋር ባካሄደችው የ12 ቀን ጦርነት በቴህራን ላይ በተፈፀመ ጥቃት የተገደሉትን ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ባጌሪን ተክተው ነበር በቦታው ተሹመዋል።
ሳዴግ ላሪጃኒ - የግልግል እና ግብረገብ ምክር ቤት ሊቀመንበር [በሕይወት ያሉ]
የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የነበሩት የአሊ ላሪጃኒ ወንድም የሆኑት ሳዴግ ላሪጃኒ የፓርላማ እና የሕገ መንግሥት ተቆጣጣሪ ምክር ቤት የበላይ ጠባቂ የሆነውን ምክር ቤት ሊቀመንበር ናቸው።
አባስ አራጋቺ - ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር [በሕይወት ያሉ]

የፎቶው ባለመብት, Karim JAAFAR / AFP via Getty Images
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እና በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ መካከል ንግግሮች ስለመደረጋቸው የሚወጡ ዘገባዎች ቢኖሩም ውይይቶች ግን ገና ያልዳበሩ እንደሆኑ ተገልጿል።
መጋቢት 15/2026 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለሲቢኤስ ኒውስ ኢራን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ጦርነት "የተኩስ አቁም ስምምነት ጠይቃ አታውቅም" ብለዋል።
"ይህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አሜሪካ የመረጡት ጦርነት ነው፤ እናም ራሳችንን የመከላከል ሥራችንን እንቀጥላለን" ሲሉ አክለዋል።
ብርጋዴር ጄነራል አዚዝ ናስርዛዴህ - የመከላከያ ሚኒስትር [የተገደሉ]
የመከላከያ ሚኒስትሩ ብርጋዴር ጄኔራል አዚዝ ናስርዛዴህ የካቲት 21/2026 በዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ በተፈፀመው ጥቃት ተገድለዋል።
የኢራን መሪዎችን ዒላማ ማድረግ ምን አሳካ?
የአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄኔራል ዳን ኬይን የዩናይትድ ስቴትስ እና የእስራኤል ዕቅድ የኢራንን አገዛዝ "ማዘናጋት እና ግራ መጋባት" ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
አሜሪካም ሆነች እስራኤል ጦርነቱ በተጀመረባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ በቴህራን የአገዛዝ ለውጥ ለማምጣት ዓላማ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባጋሩት የቪዲዮ መልዕክት ኢራናውያን "መንግሥታችሁን ገልብጡ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን ሕዝብ "እንዲነሳ" ጥሪ ካቀረቡት ጋር የተጣጣመ ነው።
ነገር ግን ሰማዕትነት ትልቅ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ዋጋ ተደርጎ በሚቆጠርባት አገር ውስጥ የእነዚህ ከፍተኛ መሪዎች ሞት የውድቀት ሳይሆን የቀጣይነት ማሳያ ተደርጎ እየቀረበ ነው።
በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ እንባ የተናነቀው ጋዜጠኛ የአሊ ኻሜኒ ሞትን "ጣፋጭ፣ ንፁህ የሰማዕትነት ጽዋ ተጎንጭተው ወደ ታላቁ ሰማያዊ መንግሥት ተቀላቀሉ" ሲል ተደምጧል።
ከሁለት ሳምንታት በላይ በኋላ የአሊ ላሪጃኒን ሞት ሲዘግብ ደግሞ "የሰማዕታት ንፁህ ነፍስ የፈጣሪ ጻድቅ አገልጋይ ሰማዕት ዶ/ር አሊ ላሪጃኒን ንፁህ ነፍስ ተቀበሉ። ለኢራን እድገት እና ለእስላማዊ አብዮት የዕድሜ ልክ ትግል ካደረጉ በኋላ፣ በመጨረሻ የረዥም ጊዜ ምኞታቸውን አሳክተዋል፣ መለኮታዊውን ጥሪ ተቀብለዋል፤ እናም በአገልግሎት ሸለቆ ውስጥ የሰማዕትነትን ጣፋጭ ጸጋ በክብር አግኝተዋል።"















