የባሕረ ሰላጤው አገራት በኢራን ላይ ለምን የአጸፋ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጠቡ?

በዩናይትድ ስቴትስ እና በእስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የሚሳዔል ጥቃቶችን መሰንዘሯን ቀጥላለች።
እስራኤል የዓለም ትልቁ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ የሆነውን የኢራኑን ደቡብ ፓርስ ካጠቃች በኋላ ሐሙስ ዕለት ቴህራን የኳታሩን ራስ ላፋን የኢነርጂ ተቋምን በመምታት ምላሻ ሰጣለች።
ኳታርም ሆነች ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት በኢራን የደረሰባቸውን ተደጋጋሚ ጥቃት ለመበቀል እስካሁን አልሞከሩም። አልመረጡም። ለምን የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ተቆጠቡ? ወደ ጥቃት ሊከታቸው የሚችለውስ ምንድን ነው?
ከፍተኛ ተጋላጭነት እና የተወሰነ ጥቅም
አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 ቀን በኢራን ላይ የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ ሲጀምሩ፣ ቴህራን በፍጥነት የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው በእስራኤል ላይ ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ ጋር በተባባሩት የባሕረ ሰላጤ አገራት ተቋማት ላይ ጭምር ነው።
ባህሬን፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኦማን እና በተለይም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) ሁሉም ዒላማዎቿ ሆነዋል።
በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮችን ከመምታት በተጨማሪ ኢራን የአየር ማረፊያዎችን፣ ሆቴሎችን፣ የመኖሪያ መንደሮችን እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እንደመታች የባሕረ ሰላጤው አገራት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ግን በኢራን ላይ የአጸፋ ጥቃት ከመፈጸም እና በጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ ከመሳተፍ መቆጠብን መርጠዋል።
"ከእነሱ ዕይታ አንጻር ይህ የእነርሱ ጦርነት አይደለም። በበቀል እርምጃ ተጋላጭ ከሆኑ ከተመልካችነት ወደ ዒላማነት ሊቀይራቸው ይችላል። ምክንያቱም ከማግኘት ይልቅ ብዙ የሚያጡት ነገር ይኖራል" ሲሉ የአሜሪካው ሴንተር ፎር ኢንተርናሽን ፖሊሲ ማዕከል ባልደረባው ሲና ቱሲ ተናግረዋል።
ይህ ያለመሳተፍ ውሳኔ የመጣው "ከተጋላጭነት፣ ከስትራቴጂካዊ ስሌት እና ከተገደበ ጥቅም አንጻር ነው" ሲል ቱሲ ገልጸዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት በኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ በመርከብ እና በባለሀብቶች የራስ መተማመን ላይ የተመሠረቱ ምጣኔ ሀብት በመገንባታቸው "ኢራን ሁሉንም ልታሽመደምዳቸው እንደሚቻላት አሳይታለች" ብለዋል ቱሲ።
በተለይም ኢራን ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆኑትን የፋርስ ባሕረ ሰላጤን እና የሆርሙዝን ወሽመጥን እንደ ዋና ነጥብ ማግኛ እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል።
የትሬንድስ ሪሰርች ኤንድ አድቫይዘሪ ከፍተኛ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) ባለሥልጣን የነበሩት ቢላል ሳብ በበኩላቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት ኢራንን አለማጥቃታቸውን ከቀጠሉ "ምንም ዓይነት የአጸፋ ምላሽ ሳይደርስባት ከባድ ጉዳት ሊያደርስባት እንደሚችል ለቴህራን እያሳወቁ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"የአጸፋ ምላሽ ዓላማ በአጭር ጊዜ ኢራን ጥቃቶቿን እንድታቆም ማስገደድ ሲሆን፣ በረጅም ጊዜ ደግሞ ለወደፊቱ የኢራን ጥቃት የተወሰነ የመከላከያ መደላደል መፍጠር ነው" ብለዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት የሚሰነዘሯቸው ማናቸውም ጥቃቶች ጦርነቱን ትርጉም ባለው መልኩ ይቀይራሉ ወይስ ስትራቴጂካዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው? የሚሉት ግልጽ ስላልሆኑ አደጋዎቹ "ከፍተኛ" እንደሚሆኑ አክለዋል።
ለንደን በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ የመከላከያ ጥናት ትምህርት ክፍል በዓለም አቀፍ ደኅንነት መምህር የሆኑት ሮብ ጌስት ፒንፎልድ በበኩላቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት ምላሽ አለመስጠታቸው ከእስራኤል እና ለቀጠናው ካላት ዓላማ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆናቸውም ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
"እስራኤል አሜሪካንን ወደዚህ ጦርነት እንደጎተተች የሚነገር ስሜት አለ" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
'የ2003 መንፈሶች እያንዣበቡ ነው'
ለብዙ የባሕረ ሰላጤው አገራት መሪዎች አሜሪካ ከኢራቅ ጋር የባችው ጦርነት መዘዝ አሁንም በቀጣናው አስተሳሰብ ላይ ትልቅ ቦታ አለው ይላሉ ፒንፎልድ።
በአውሮፓውያኑ 2003 አሜሪካ ኢራቅን ከወረራች በኋላ የሳዳም ሁሴን መንግሥትን በፍጥነት ገለበጠች። ከዚያ በኋላ የተከሰተው ነገር ግን በኢራቅ እና በቀጣና ውስጥ ለአመፅ፣ ለሃይማኖታዊ ብጥብጥ እና ለዓመታት አለመረጋጋት ምክንያት የሆነ የሥልጣን ክፍተት ፈጥሯል።
አሁንም በቀጣናው "የ2003ቱ ዓይነት መንፈስ እያንዣበበ ነው" ይላል ፒንፎልድ።
"በደጃቸው ላይ ለረብሻ እና ላለመረጋጋት በሮችን እንደሚከፍት እና የኢራን ተጽዕኖ ሊያሰፋ ይችላል በሚል ፈርተዋል። ስህተት አለመፈጸማቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።"
ፒንፎልድ አክለውም የባሕረ ሰላጤው አገራት አሜሪካ "ከጦርነት በኋላ ለማሳካት ስለፈገችው ግልጽ የሆነ ዓላማ ወይም አቅጣጫ ሳይኖራት መጨበጫ የሌለው ዘመቻ እያካሄደች ነው።" ከጦርነቱ በኋላም ቀጠናውን "በችግር ውስጥ ትተዋለች" ብለው እንደሚፈሩ ተናግረዋል።
በባሕረ ሰላጤው ውስጥ አሜሪካ እና እስራኤል ይህንን ጦርነት በመጀመራቸው ደስተኛ አለመሆናቸው በስፋት ቢታይም አካባቢያቸውን ለመከላከል ግን በአሜሪካ ወታደራዊ አቅም ላይ በእጅጉ ጥገኛ ሆነው ይቀጥላሉ።
የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ወታደሮች መቀመጫ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በርካታ የባሐረረ ሰላጤ አገራት የስለላ መረጃዎችን ይጋራሉ፤ በአሜሪካ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ላይም ጥገኛ ናቸው።
እንደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ባለሥልጣናት ገለጻ እነዚህ የአየር መከላከያዎች ከኢራን የተተኮሱትን አብዛኞቹን የሚሳዔል ጥቃቶች አክሽፈዋል።
"ምንም እንኳን [የባሕረ ሰላጤው አገራት] ከፖለቲካ አንጻር አሜሪካን ቢጠይቁም፣ ከአሠራር እና ከወታደራዊ አንጻር ግንኙነቱ የተፈተነ እና ፈተናውን በጥሩ ሁኔታ ያለፈ ነው" ይላሉ ፒንፎልድ።
ባለፈው ወር ጥቃቶችን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ ለወታደራዊ ዘመቻዎቿ የተለያዩ ዒላማዎችን አስቀምጣለች፤ የኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን የመገንባት አቅምን ከማጥፋት እስከ አገዛዝ ለውጥ የሚደርሱ ናቸው።
አሁንም ድረስ ግን የባሕረ ሰላጤው መሪዎች ዲፕሎማሲ ጦርነቱን ለማስቆም ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ያስባሉ ይላሉ ፒንፎልድ።
"አንዳቸውም እንዳይተኮስባቸው ለማረጋገጥ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ እና የተወሰነ ድርድር ማድረግ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, EPA
የተከፋፈለ ቀጠና
ኢራን ሁሉንም የባሕረ ሰላጤው አገራትን "በእኩልነት" አላነጣጠረችባቸውም ይላሉ ፒንፎልድ። ይህም ከአገሮቹ ጋር ያላትን የተለያዩ ግንኙነቶች የሚያንጸባርቅ ነው።
ኤምሬትስ በጦርነቱ ወቅት በጣም ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ ነች።
ኤምሬትስ እና ባህሬን በአውሮፓውያኑ 2020 ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ አድርገዋል።
በተቃራኒው ደግሞ በኢራን እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ለረጅም ጊዜ ድልድይ ሆና የማደራደር ሚና ያላት ኦማን በቴህራን ብዙም ዒላማ አልተደረገችም።
"ኦማን አዲሱን የኢራን ጠቅላይ መሪ [ሞጅታባ ካሜኒ] እንኳን ደስ አልዎት ያለች ብቸኛዋ የባሕረ ሰላጤው አገር ነበረች። ይህንን ሁኔታ ግን ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት አልተከተሉትም" ሲሉ ፒንፎልድ ተናግረዋል።
የዱባይ ፐብሊክ ፖሊሲ ሪሰርች ሴንተር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ባሃሮን "ኢራን ባህረ ሰላጤውን ወደ ሰፊ ጥምረት እየገፋች ነው" ብለዋል።
"የባሕረ ሰላጤውን አገራት በማጥቃት ኢራን ወደ ጠላትነት እየለወጠቻቸው እና ማንም የማይፈልገውን መጠነ ሰፊ ጦርነት ለመፍጠር እየሞከረች ነው" ሲሉ አክለዋል።
ረቡዕ ዕለት በሳዑዲ አረቢያ የተሰባሰቡት የባሕረ ሰላጤው አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተባበሩት መንግሥታት አንቀጽ 51 መሠረት እራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን አፅንዖት ሰጥተውታል።
የአጸፋ እርምጃ ሊያስከትል የሚችለው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የባሕረ ሰላጤው አገራት ለአሁኑ ወደ አጸፋ እርምጃ ባይገቡም "ሁኔታው በፍጥነት ሊለወጥ ይችላል" ሲሉ የሩሲ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ኤች ኤ ሄሊየር ተናግረዋል። በተለይም የኢራን ጥቃቶች የኃይል መሠረተ ልማቶችን የሚያወድሙ ከሆነ እየተባባሰ ይሄዳል።
አስተሳሰብን ሊቀይር የሚችለው አንደኛው አማራጭ በኢነርጂ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘር ነው ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት የኳታር ራስ ላፋን የኢነርጂ ተቋምን ከደበደበች በኋላ፤ ኢራን በተቋሟቶቿ ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች ከቀጠሉ የአሜሪካን የባሕረ ሰላጤ አጋሮች "ሙሉ በሙሉ እንደምታጠፋ" ቃል ገብታለች።
ሌላኛው ሁኔታውን የሚቀይረው ጉዳይ ደግሞ የኢራን የአካባቢዎች ደጋፊዎች የባሕረ ሰላጤው አገራትን ዒላማ ካደረጉ ነው።
"በሁቲዎች ጥቃት ከደረሰባቸው… ያ አዲስ ግንባር ይከፍታል" ይላሉ ፒንፎልድ።
ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ የባሕረ ሰላጤው አገራት ግጭቱን የአሜሪካ እና የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የራሳቸውም እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ ሲሉ አክለዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የበቀል እርምጃ ባይወስዱም የኢራን ስትራቴጂ "እጅግ በጣም ከፍተኛ አደጋ አለው" ብለዋል ፒንፎልድ።
"ኢራናውያን ከባሕረ ሰላጤው አገሮች ጋር የነበሯቸውን ድልድዮች በሙሉ እያቃጠሉ ነው። ይህ ደግሞ ኢራናውያን ይህንን ግጭት ምን ያህል የኅልውና ጉዳይ እንዳደረጉት ያሳያል" ብለዋል።
ሄሊየር በበኩላቸው የባሕረ ሰላጤው አገሮች በተለይም በሲቪል ዒላማዎች ላይ ኢራን ያለማቋረጥ ጥቃት መሰንዘር መቀጧጠሏን "አይቀበሉትም" ሲሉ አስረድተዋል።
በመጨረሻም የኢራን የባሕረ ሰላጤው አገሮች ዋሽንግተንን ካጠገባቸው እንዲያርቁ ጫና ለማድረግ የምታደርገው ከፍተኛ ስትራቴጂ ላይሳካ እንደሚችል ያስባሉ።
"[እነሱ] አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የተጀመሩትን ጦርነት ቢቃወሙም፤ የራሳቸው ደኅንነት በማስቀደም አሁን በኢራን ላይ ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት እና ከኢራን የሚመጣውን ስጋት ለማስቆም የአሜሪካን ዘመቻ መደገፍ የበለጠ ተስማሚ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters















