የኢራን ጦርነት፡ ኃያላን ያሻቸውን ማድረግ የሚችሉበት አዲሱ የዓለም ሥርዓት ጅማሬ?

ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጀርባ የሚታይ የጦር መሣሪያ እና ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ከተካሄዱት ዋነኘው ሆኖ ሊታይ ይችላል።

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለአስርተ ዓመታት የዓለም አቀፍ ባህሪን የሚቆጣጠሩት ሕጎች የነበራቸውን ተጽዕኖ እያጡ ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ለረዥም ጊዜ፣ ጦርነት እና ዲፕሎማሲ የሚካሄዱት በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች ተቋማት በተቀረጹ ማዕቀፎች ውስጥ ነበር።

እነዚህ ደንቦች እና ስምምነቶች ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ተደርገው ቢተረጎሙም፣ መንግሥታት እንቅስቃሴዎቻቸውን በአጠቃላይ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ለማሳየት ይጥሩ ነበር።

ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በተለምዶ በሕግ ክርክሮች፣ በዲፕሎማሲያዊ ምክክሮች ወይም በዓለም አቀፍ ጥምረት ምሥረታ የታጀቡ ነበሩ።

በዚህ ጦርነት ግን እነዚህ ጉዳዮች በጣም ውስን ሚና ብቻ ያላቸው ይመስላሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት ከዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች ወይም ከብዙ ወገን ፈቃድ ጋር ማስማማት ሳያስፈልግ በወታደራዊ እና በፖለቲካዊ ወይም በደኅንነት ስሌቶች ብቻ ላይ ሆነዋል።

ለኢራን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ መንቀሳቀስ ሙሉ በሙሉ አዲስ አይደለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለአስርተ ዓመታት አገሪቱ ከሰፊ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ውስጥ እና የፖለቲካ መገለል ስር ኖራለች።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥም እነዚያን ውሳኔዎች ለማለፍ ሥርዓት እና ኢኮኖሚያዊ ብልሃቶችን አዘጋጅታለች።

ኢራን በዓለም ላይ ከተጣሉት ሁሉን አቀፍ ማዕቀቦች ሁሉ በአስከፊው ውስጥ ብትሆንም፣ ነዳጅ ወደ ውጭ መላክ እና በአካባቢው ላይ ያላት ተጽዕኖን አስቀጥላለች።

በዚህ ስትራቴጂካዊ ሁኔታ ውስጥ የሚኖር የተካረረ ውጥረት ብዙውን ጊዜ የተሰላ ነው።

ኢራን ከዚህ ቀደም በገጠሟት ቀውሶች ሁሉ የሰጠችው ምላሽ ሰፋ ያለ የቀጣናው ጦርነትን ሳይቀሰቅስ ለተቃዋሚዎቿ ደግሞ የግጭት ወጪን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው።

የዚህ ትልቁ ዓላማ ብዙውን ጊዜ የግጭቱ ተሳታፊዎች ፍጥጫውን ለማርገብ እስኪገደዱ ድረስ በተቃዋሚዎች ላይ የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ጫና መጨመር ነው።

እስራኤልም ብትሆን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወዲያውኑ ወደ ተግባራዊ ገደቦች የማይለወጡበት አካባቢ ውስጥ መንቀሳቀስን የለመደች ናት።

የእስራኤል ወታደራዊ ዶክትሪን መሪዎች ከባድ ስጋት እየተፈጠረ መሆኑን ሲያምኑ ፈጣን እና ቆራጥ እርምጃ መውሰድን ለረጅም ጊዜ ሲከተሉ ቆይተዋል።

ቅጽበታዊ ጥቃት እና ከፍተኛ ኃይል መጠቀም የዚያ አካሄድ ተደጋጋሚ መንገዶች ናቸው።

እስራኤል በቅርብ ዓመታት ውስጥ የፈጸመቻቸው ወታደራዊ ጥቃቶች በዓለም አቀፍ የሕግ መድረኮች፣ በዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት እና በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ጥያቄ ቀርቦባቸዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እስራኤል በተለይም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት በማጠናከር የምትወስዳቸውን ወታደራዊ እርምጃዎቿ እሁንታን አንዲያገኙ አድርጋለች።

ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ሥርዓት ውስጥ በተለየ አቋም ላይ ትገኛለች።

ዋሽንግተን ከአውሮፓውያኑ 1945ቱ በኋላ ባለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ ብቻ አልነበረችም።

የኻርግ ደሴት ካርታ
የምስሉ መግለጫ, የኢራኗ ወሳኝ ደሴት ኻርግ

የዓለም አቀፍ ሕግን በመንደፍ እና በማስቀጠል ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ከጦርነቱ በኋላ ብቅ ያሉት ጥምረቶች፣ ተቋማት እና የሕግ ሥርዓቶች ብዙውን ጊዜ የአሜሪካን ተጽዕኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚሠሩ ነበሩ።

ዩናይትድ ስቴትስ በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ያንን ሥርዓት በግልጽ ለማለፍ የቀረበችው በአውሮፓውያኑ 2003 ኢራቅን በወረረችበት ወቅት ነበር።

በዚያን ጊዜም ቢሆን ዋሽንግተን ጣልቃ ገብነቱን እንደ የሰፊ ጥምረት አለመኖር አካል አድርጋ ለማቅረብ ሞክራ ነበር።

"የፈቃደኝነት ጥምረት" ተብሎ የሚጠራው እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ እና ፖላንድ ያሉ አጋሮችን እንዲሁም የተለያዩ የድጋፍ ደረጃዎችን የሰጡ ሌሎች በርካታ መንግሥታትን ያካተተ ነበር።

ለጦርነቱ ሕጋዊነት ላይ ከፍተኛ ውዝግብ ቢኖርም፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሁንም የኢራቅን ጦርነት በብዙ ወገን አውድ ውስጥ ለማስቀመጥ ሞክራለች።

ይሁን እንጂ በዚህ ጦርነት የተሳተፉ አገራት ለዓለም አቀፍ ሕግ ያላቸው ግድ አነስተኛ ይመስላል። በከፍተኛ ባለሥልጣናት የተሰጡ መግለጫዎችም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ስሜትን ያንፀባርቃሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የፈጸመቻቸው ተከታታይ ጥቃቶች የኢራንን የኻርግ ደሴት አብዛኛውን ክፍል "ሙሉ በሙሉ እንዳወደመ" ለኤንቢሲ ኒውስ ሲናገሩ "ለጨዋታ ብቻ ጥቂት ተጨማሪ ጊዜ ልንደበድበው እንችላለን" ብለዋል።

እንደዚህ ዓይነት አስተያየቶች ከተለመዱት የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻዎች ጋር ሲነጻጸርሩ የበለጠ ቀጥተኛ እና ዲፕሎማሲያዊ ያልሆነ አቀራረብን መከተላቸውን ያሳያሉ።

በዚህ አዲስ አካሄድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደ የፖሊሲ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል።

አሜሪካ ተቀናቃኝ ባለቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በረዥም ጊዜ አጋሮቿ ላይም ታሪፎች እና የንግድ ገደቦች ጥላለች።

የአውሮፓ መንግሥታት፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች የኔቶ አጋሮችን ጨምሮ፣ ከመከላከያ ወጪ እና ከስደተኞች ጋር በተያያዘ በሚከተሉት ፖሊሲ እንዲሁም ከሩሲያ ጋር ባላቸው ግንኙነት ከዋሽንግተን ትችት ገጥሟቸዋል።

እንደነዚህ ያሉት ፖሊሲዎች በተለይም ሌሎች ግዛቶች በተቀመጡት ዓለም አቀፍ ደንቦች መሠረት መሥራታቸውን ከቀጠሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሊመስሉ ይችላሉ።

ሆኖም የረጅም ጊዜ አንድምታዎች ብዙም ግልጽ አይደሉም።

ሥርዓቱን በዋነኛነት ያበጃጁት በእነዚህ ሕጎች ላይ ያነሰ ትኩረት መስጠት ከጀመሩ፣ ሌሎች መንግሥታትም በእነሱ ላይ ብዙም ገደብ እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል።

ኢራን ቀደም ሲል በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ የነበራት ባህሪ በአንድ ወቅት እንዲህ ያሉ ገደቦች በአመራሯ እንዴት ይታዩ እንደነበር ያሳያል።

በ2025 ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው የ12 ቀናቱን ጦርነት ጨምሮ ቀደም ባሉት ቀውሶች ወቅት፣ ቴህራን በወታደራዊ መንገድ ምላሽ ብትሰጥም እንኳ የራሷን ስትራቴጂካዊ ቀይ መስመሮች በአብዛኛው ጠብቃለች።

ምንም እንኳን ግጭቱ ከተለመደው ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ የተለየ ቢሆንም፣ የኢራን የአጸፋ እርምጃ የተመጠነ ነበር።

ካርታ

ኢራን በኳታር በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የአል ኡዴይድ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ላይ ሚሳዔሎችን ስታስወነጭፍ፣ ከጥቃቱ በፊት ለኳታርም ሆነ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት መደበኛ ያልሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር።

ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ የቴህራን የአጸፋ እርምጃ ሰፋ ያለ ግጭትን ለማስወገድ በጥንቃቄ የተሰላ ይመስላል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ግጭት እነዚህ የዓለም ሥርዓቶች ቦታዎችን ያጡ ይመስላሉ።

በመጀመሪያው የጥቃት ማዕበል ጠቅላይ መሪዋ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የተገደሉባት ኢራን፣ በአረቢያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ በሚገኙ የአሜሪካ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽማ ወታደራዊ ማዕከሎችን፣ የሲቪል ዒላማዎችን እና መሠረተ ልማቶችን አጥቅታለች።

በተመሳሳይ ጊዜ የኢራን እርምጃ በዓለም ወሳኝ ከሆኑት የነዳጅ ዘይት መተላለፊያዎች አንዱ በሆነው በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል ያለውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ውጤታማ በሆነ መንገድ አስተጓጉሏል።

የዚህ ወሽመጥ መዘጋት ውጤት የታየው ወዲያውኑ ነበር።

በዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ የታየው በፍጥነት ነበር።

በዚህም የተነሳ በማዕቀብ ውስጥ የነበረችው ሩሲያ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ተፈጥሮላታል፤ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲላላ ተደርጎ የተወሰነ ነዳጇን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች።

ሩሲያ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ካገኘች ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች።

የአውሮፓ ኅብረት በዚህ እርምጃ ላይ ተቃውሞ ቢኖረውም በሞስኮ ላይ የተጣለው የማዕቀብ ጫናም ቀንሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻይና ምናልባት ዓለም አቀፍ ደንቦች ምን ያህል ርቀት ሊለዋወጡ እንደሚችሉ እና በምን አቅጣጫ ሊሄዱ እንደሚችሉ በቅርበት ትከታተላለች።

አውሮፓ በአሁኑ ጊዜ ነገሮች እየሄዱበት ያለው አቅጣጫ ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ እንዳላት ይታያል። ኅብረቱ የሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢኖሩም ከዩኬ ጋር በመሆን በአብዛኛው ሁኔታዎችን በሚፈልጉት መልኩ ከመቅረጽ ይልቅ የሚሆነውን መመልከት መርጠዋል።

ስለዚህ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተነሳው ግዙፍ ጥያቄ ከአንድ ግጭት ውጤት በላይ ይዘልቃል።

ይህም ከአውሮፓውያኑ 1945 ጀምሮ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እና ፖለቲካን የቀረፀውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ዘላቂነት ይመለከታል።

ምንም እንኳን ሥርዓቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባያገኝም እንዲሁም ብዙ ጊዜ ክርክር ቢደረግበትም ሥልጣን የሚተገበርበትን ማዕቀፍ አቅርቧል።

ያ ማዕቀፍ እየተዳከመ ከቀጠለ፣ ውጤቱ ብዙም የማይገመት ዓለም አቀፍ ሁኔታን መፍጠር ሊሆን ይችላል።

በዚህ ውስጥ መንግሥታት በጋራ ሕጎች ላይ ብዙም ጥገኛ ሳይሆኑ በራሳቸው የተናጠል አቅም ላይ ብቻ ይደገፋሉ።

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሥርዓቱን መጀመሪያ የነደፉት አገራት እንኳን መሸርሸሩ ለመገመት አስቸጋሪ የሆኑ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል።