በነዳጅ ምክንያት ግብፅ ሱቆች እና ምግብ ቤቶችን በጊዜ ስትዘጋ ፤ አውስትራሊያ የሕዝብ ትራንስፖርትን ነጻ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የሚገኘውን የነዳጅ ዋጋ ተከትሎ ግብፅ ሱቆች እና ምግብ ቤቶችን በጊዜ እንዲዘጉ ስትወስን፤ አውስትራሊያ በበኩሏ የሕዝብ ትራንስፖርትን ነጻ እንዲሆን አዘዘች።
በግብፅ ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና ካፌዎች በጊዜ እንዲዘጉ በመወሰን ጊዜያዊ እርምጃዎችን ወሰደች።
የችርቻሮ ሱቆች እና ምግብ ቤቶች ከማክሰኞ ጀምሮ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ እንዲዘጉ ተወስኗል።
በግብፅ መንግሥት ይፋ ከተደረጉት "ልዩ እርምጃዎች" ውስጥ የመንገድ መብራቶችን እና የመንገድ ዳር ማስታወቂያዎችን ማደብዘዝን ጨምሮ በሳምንት አንድ ቀን ከቤት መሥራትን ያካትታሉ።
ግብፅ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቷ ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል።
የወሽመጡ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በምግብ፣ በመድኃኒት እና በሌሎች እቃዎች ዋጋ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ግብፅ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ ባይኖራትም ከውጭ በሚገባው ነዳጅ ላይ ያላት ጥገኝነት በሸቀጦች አቅርቦት ላይ ጫና መፍጠሩ ታውቋል።
የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞስጣፋ ማድቡሊ ቅዳሜ ዕለት እንደገለጹት የአገሪቱ የነዳጅ ወጪ በጥር ወር ከነበረበት በእጥፍ አድጎ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሆቴሎች እና የቱሪስት መስህቦች ቦታዎች ከኃይል ቁጠባ እርምጃዎቹ ነፃ ይሆናሉ ብሏል መንግሥት። ቱሪዝም የግብፅን አንድ አስረኛ ኢኮኖሚ እንደሚሸፍን ይገመታል።
ማሪዮት እና ኮስሞፖሊታንን ጨምሮ በካይሮ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሆቴሎች ለአርኤፍአይ እንደተናገሩት፤ የኃይል መቆራረጥ ቢከሰት በሚል ጀነሬተሮችን ከመግዛት ባለፈ ምግብ ቤቶቻቸውን ለእንግዶች ክፍት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
አብዛኞቹ ሠራተኞች በሳምንት ለአንድ ቀን ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ቢነገራቸውም፤ እንደ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ አስፈላጊ ሠራተኞችን አይካተትም ተብሏል።
የግብፅ መንግስት የነዳጅን እና የሕዝብ ትራንስፖርትን ዋጋን ጨምሯል።
ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቁ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ከማዘግየት በተጨማሪ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች የነዳጅ አበልን በአንድ ሦስተኛ መቀነሱን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሌላ በኩል አውስትራሊያ የሕዝብ ትራንስፖርት ነፃ እንዲሆን ወሰነች።
በአውስራሊያ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነዳጅ ማደያዎች ያላቸው ቤንዚን እና ናፍጣ እየተሟጠጠ መምጣቱን እና ዋጋውም የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከነበረው እስከ 85 በመቶ መጨመሩ ታውቋል።
ይህንን ተከትሎም በሜልበርን፣ በጂሎንግ ጨምሮ በቪክቶሪያ ግዛቶች የሕዝብ ትራንስፖርት በሚያዝያ ወር ነፃ ይሆናል ተብሏል። ይህም የኑሮ ውድነትን ጫና እንደሚቀንስ ተስፋ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ነዋሪዎች ከበፊቱ በበለጠ አውቶቡሶችን፣ ባቡሮችን እና ቀላል ባቡሮችን በመጠቀም በነዳጅ ላይ ያለውን የፍላጎት ጫና ይቀንሳል ብለዋል ባለሥልጣናት።
ነዳጅ ለመግዛት የሚደረገው ሩጫ ጫና መፍጠሩን ባለሥልጣናት ገልጸው እስካሁን ድረስ ግን በነዳጅ አቅርቦት ላይ ቅናሽ እንደሌለ ተናግረዋል።















