አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙት እና እየተራቀቁ የመጡት የበይነ መረብ አጭበርባሪዎች

በሰሜን ዮርክሻየር የምትኖረው እና በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ክርስቲ እአአ በ2024 ቱርክ ውስጥ እንደሚሠራ እና እንግሊዛዊ ነጋዴ እንደሆነ ከሚናገር ሰው ጋር የፍቅር ጓደኛ በሚያገኛኝ ድረ ገጽ አማካኝነት ተዋወቀች።
በባህር ዳርቻ ላይ ሆኖ በስፖርት የዳበረ ሰውነቱን እና በገንዘብ ረገድ ከበቂ በላይ እንዳለው የሚያሳይ ፎቶውን አጋርቷል። 600 ሺህ ዶላር ባንክ ውስጥ እንደቆጠበ ሊያሳምናትም የባንክ ድረ ገጽን ተጠቅሟል።
ከሁለት ሳምንታት መጻጻፍ በኋላ ስልኩን እና ኮምፒዩተሩን እንደተሰረቀ ይነግራታል። ስልክ እንድትገዛለት እና በገንዘቧ አንዳንድ ሂሳቦችን እንድትከፍልለትም ይጠይቃታል። ቀጥሎ የተከሰተው ነገር አጭበርባሪዎች የሚከተሉትን ዓለም አቀፍ አካሄድ ያሳያል።
ክርስቲ ከዩኬ ስልክ ገዝታ በሰሜናዊ ቆጵሮስ ወደሚገኝ አንድ አፓርታማ ላከች። ግለሰቡ ለሥራ ወደ ቆጵሮስ መሄዱን ነግሯታል። ቀጥሎም በሁለት ወራት ውስጥ ከባንክ አካውንቷ 80 ሺህ ፓውንድ አስተላልፋለታለች። የምትወደው ሰው ችግር ውስጥ እንዳለ በማመን ከቤተሰቧ 50 ሺህ ፓውንድ ተበድራ ጭምር ነው የላከችለት። የባንክ አካውንቱን ሲለቀቅለት በፍጥነት እንደሚከፍላት ቃል በገባለት መሠረት ነው ገንዘቡን የላከችለት።
የስልኩ መጨረሻ ሌጎስ፣ ናይጄሪያ ሆነ። 80 ሺህ ፓውንዱ ደግሞ በገንዘብ ማስተላለፊያዎች በኩል የናይጄሪያ፣ የሮማኒያ እና የሌሎች የአውሮፓ ስሞች ላላቸው ሰዎች ተላልፏል። ግለሰቡ ብሪታኒያዊ ሳይሆን ናይጄሪያዊ ነበር። ዓላማውን ለማሳካትም የድምፅ ማስመሰያዎችን ተጠቅሟል።
ክርስቲን ካገኛት በኋላ ያሳያት የባንክ ድረ ገጽ ጭምር በአሜሪካ ባልቲሞር ከተማ የተመዘገበ በጣም የተራቀቀ ሐሰተኛ ድረ ገጽ ሆኖ ተገኘ።

ባለሞያዎች እንደሚሉት በ2020ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኮቪድ ገደቦች መጣል ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የማጭበርበር ድርጊቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ዓለም አቀፍ የፀረ-ማጭበርበር ጥምረት እንደገለጸው ከሆነ በመላው ዓለም በማጭበርበር ምክንያት በዓመት ከግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ይበላል።
እንደ ባርክሌይስ ዘገባ እአአ በ2024 እና 2025 መካከል ባለው የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከክርስቲ ጋር የሚመሳሰሉ ማጭበርበሮች ከ20 በመቶ በላይ ጨምረዋል።
የለንደን ከተማ ፖሊስ በበኩሉ ከክርስቲ ጋር በሚመሳሰል መልኩ በ2024 ብቻ በዩናይትድ ኪንግደም 106 ሚሊዮን ፓውንድ እንደተጭበረበረ አስታውቋል።
የክርስቲ ታሪክ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የማታለል ባህሪ ጥሩ ማሳያ ነው።
መጭበርበሮቹ እየጨመሩ በመሄዳቸው መንግሥታት እና ኩባንያዎች አጭበርባሪዎችን ለማስቆም ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜም ማጭበርበርን ለመዋጋት በአገሮች መካከል የጋራ ስምምነት ተፈራርሟል። የወንጀል ብልሃቶች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ መጥተዋል።
ብዙዎቹም አገራት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚቸገሩባቸው የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ናቸው።
እንደ ክርስቲ ያሉ ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን እንዳያጭበረብሩ ለመከላከል ብዙ አገራት ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ ወይ የሚል ጥያቄ ይቀርባሉ።
ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር የተስፋፋው ማጭበርበር
ማጭበርበር ብዙውን ጊዜ በጽሑፍ፣ በስልክ ወይም በኢሜል ገንዘብዎን ወይም መረጃዎን እንዲያጡ ማድረግ ነው። በዋናነትም አንድ ሰው ገንዘብ እንዲልኩለት ለማድረግ የሚዋሽዎት አካሄድ ነው።
ማጭበርበር በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በጣም የተለመደ ወንጀል ሲሆን በግለሰቦች ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ይይዛል።
የዩኬ መንግሥት 70 በመቶ የሚሆኑት ማጭበርበሮች ከውጭ አገር የሚመጡ እና ብዙውን ጊዜ በወንጀል ቡድኖች በኩል የሚከሰቱ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት ከ2020 ጀምሮ በኮቪድ ገደብ ወቅት የዜጎቻቸውን እንቅስቃሴ በመገደባቸው ሰዎች በበይነ መረብ ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ጀምረዋል።
በበይነመረብ የሚደረጉ ግብይቶች እና ግንኙነቶች በመጨመራቸው ማጭበርበር ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር የበለጠ ቅርርብ ተፈጥሯል።
የቪዲዮ ማስመሰል፣ ድምጾች፣ ድረ ገጾች እና ጽሑፎች በጣም የተለመዱ ከመሆናቸውም በላይ አጭበርባሪዎች ዋትስአፕ ጨምሮ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸውን ጨምረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎች ሥራ በማቆማቸው በወንጀል ቡድኖች ሊመለመሉ የሚችሉ አዳዲስ የሠራተኛ ኃይል ፈጥረዋል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ቢሮ ተጠባባቂ ኃላፊ የሆኑት ኢሊያስ ቻትዚስ ተናግረዋል። የወንጀል መረቦችን ለመበጣጠስ ደግሞ በጣም ከባድ ነው።
"ከእነዚህ ማጭበርበሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ሕገ ወጥ በሆኑ አካባቢዎች ወይም በታጠቁ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚከናወኑ በመሆናቸው የመንግሥታት ቁጥጥር ላይኖራቸው ይችላል።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምያንማር በማጭበርበሪያ ማዕከሎቿ የታወቀች አገር ሆናለች።
እነዚህ መነሻቸው በ1990ዎቹ ሕገ-ወጥ ቁማር መጫወቻዎች ከተቋቋሙበት ጊዜ ጋር ይያያዛል።
በወረርሽኙ ወቅት እነዚህ ሕንፃዎች የማጭበርበሪያ ማዕከላት ሆነው እያገለገሉ ነበር። ወታደራዊው ጁንታ በ2021 ሥልጣን ሲይዝ የእርስ በርስ ጦርነት በመከሰቱ ወንጀለኞች በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ትርምስ እንዲጠቀሙ ከመርዳት ባለፈ የማጭበርበሪያ ማዕከላትም ተስፋፍተዋል።
ተጎጂዎችን የሚፈጥሩት ተጎጂዎች
የበይነ መረብ አጭበርባሪው ረዓሸዑ ተጎጂ ሊሆኑ መቻላቸው ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል።
በትውልድ አገራቸው ሥራ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች ለሥራ ወደ ሌላ አገር ተታለው ይሄዳሉ። ወደ ማጭበርበሪያ ማዕከላት ገብተው ለአሰሪዎቻቸው የሰዎችን ገንዘብ እንዲሰርቁ ይገደዳሉ።
ቢቢሲ በቅርቡ በታይላንድ እና በካምቦዲያ መካከል በድንበር ውዝግብ ወቅት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ በሽሽት የተተዉ ግዙፍ የበይነ መረብ ማጭበርበር የሚፈጸምበትን ግቢ ጎብኝቷል።
በማዕከሉ ተስፋ አስቆራጭ እና ምቹ ያልሆነ የኑሮ እና የሥራ ሁኔታ እንደነበር መመልከት ችለናል። በግቢው ካሉት ክፍሎች በአንዱ ግድግዳ ላይ "ከሁሉም ቦታ ገንዘብ ይገኛል" የሚል መልእክት በቻይንኛ ተጽፎበታል።
'ሠራተኞች' ወደ መጸዳጃ ቤት የሄዱበትን ጊዜ እና ምን ያህል ጊዜ እንደቆዩ የሚያሳዩ መዝገቦች፣ የሐሰት የፖሊስ ደንብ ልብሶች እና ሐሰተኛ የፖሊስ መጥሪያዎች ተገኝተዋል። እነዚህም ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲያስረክቡ ለማስፈራራት የተነደፉ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, LULU LUO/BBC
ሰዎችን ወደ ማጭበርበሪያ ማዕከላት እንዲሄዱ ማድረግ በራሱ ማጭበርበር ነው።
ተጎጂው በአውሮፕላን ማረፊያው ሲደርስ መምህርነት ወይም የደንበኛ ተቀባይነት ሥራ እንዳገኙ እንደሚነገራቸው ይታመናል።
"ግቢው ውስጥ እስኪገቡ እና ሙሉ በሙሉ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ውስጥ እስኪወድቁ ድረስ ሁሉም ነገር ሕጋዊ ይመስላል" ይላሉ ቻትዚስ። "ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ችግሩ ይጀምራል። ፓስፖርታቸውም ይወሰዳል።"
በእነዚህ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ውስጥ ያሉ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ተጎጂዎችን በማጭበርበር የተወሰነ ገንዘብ እንዲያስገቡ የተቀመጠላቸውን ግብ ለማሳካት ረዥም እና ከባድ ፈረቃዎችን ለመሥራት ይገደዳሉ።
እነዚህን ግቦች አለማሳካት ለብቻ እስር፣ ድብደባ ወይም የበለጠ የከፋ አያያዝ ወዳለበት ግቢ የመዛወር አደጋ ሊኖረው ይችላል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ተጎጂ "ይህንን ማጭበርበሪያ ለመፈጸም የተገደደ በሌላኛው ወገን የሚገኝ ተጎጂ ሊኖር ይችላል" ሲሉ ቻትዚስ ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እነዚህ የማጭበርበሪያ ማዕከላት በደቡብ ምሥራቅ እስያ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሕንድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባሉ አገሮችም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው።
አንዳንድ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ቀን ላይ ሕጋዊ ሥራዎችን ሌሊት ደግሞ የማታለል ተግባር ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል።
ለምሳሌ በሰሜን ምሥራቅ ሕንድ ሕጋዊ የጥሪ ማዕከላት ሌሊት ላይ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ይሆናሉ። አጭበርባሪዎቹ እንግሊዘኛን በመጠቀም የጊዜ ልዩነትን በመጠቀም በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ውስጥ ሰዎችን ዒላማ ያደርጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የለንደን ከተማ የፖሊስ መኮንን ኒክ ኮርት በአሁን ወቅት የኢንተርፖል የፋይናንስ ወንጀል እና የፀረ ሙስና ማዕከል ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ነው።
ከሃብታም አገሮች የመጡ ሰዎች በውጭ አገር ያለውን እውነታ መረዳት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
"ከፍተኛ ወታደራዊ እጀባ ከሌለ በስተቀር ሕገ ወጥ በሆኑ ቦታዎች የሕግ አስከባሪ ፖሊሶች መግባት የማይችሉባቸው ሲሆን በአካባቢው የሚከፈለው ደመወዝ ዝቅተኛ በመሆኑ በማጭበርበር ውስጥ የመሳተፍ ጥቅሞች እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።"
አጭበርባሪዎችን መቋቋም
ባለፈው ወር በተባበሩት መንግሥታት እና በኢንተርፖል ተሰናድቶ በቪዬና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የማጭበርበር ጉባኤ ላይ ከዩኬ፣ ከቻይና እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመጡትን ጨምሮ አንድ ሺህ 400 እንግዶች ተሳትፈዋል።
እንደዚህ ያሉ ስብሰባዎች እአአ ከ2024 ጀምሮ እየተካሄዱ ቢቆዩም ይህ ትልቅ እንደነበር መመስከር ይቻላል። የመንግሥት ሚኒስትሮች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የሕግ አስከባሪዎች ተሳትፈዋል። በመጨረሻ ላይም በአንዳንድ አገራት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የጋራ ስምምነት ተፈርሟል።
በጉባዔው ላይ ከ120 አገሮች ውስጥ 44ቱ "ማጭበርበርን ከምንጩ ለመከላከል እና የተጎጂዎችን ድጋፍ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።"
ብዙ አገሮች ስምምነቱን እንደሚፈርሙ ተስፋ ቢደረግም ለትብብሩ ቁርጠኛ ያልሆኑ ብዙ አገሮች አሁንም አሉ።
በስብሰባው ላይ የተገኙ እንደ የአውሮፓ አገሮች፣ ደቡብ ኮሪያ እና አውስትራሊያ ያሉ ሀብታም አገሮች በብዛት ተጎጂ በመሆናቸው ይህንን ጉዳይ ለመፍታት የበለጠ ፍላጎት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ብዙዎቹ የማጭበርበር ሥራዎች የሚናወኑባቸው በተለይም እንደ ምያንማር፣ ምዕራብ አፍሪካ እና ደቡብ እስያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ለመከላከል የሚያስችል ሀብት ባይኖራቸውም የበለጠ እንዲያደርጉ እየተጠየቁ ነው።
ወንጀለኞች ድሆችን በመጠቀም በሕጋዊ መንገድ ሠርተው የማያገኙትን ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ መበዝበዛቸው ያለውን አለመመጣጠን ያሳያል።
አንዳንድ አገሮች ለሕዝባቸው ኅልውና በጣም ጥሩ ገቢ ማግኛ የሆነውን ወንጀል በማስቆም በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚካሄደውን የገንዘብ ወንጀሎች ለመከላከል እንዲጨንቁ ይገደዳሉ።
ከደቡብ አፍሪካ የመጡት አቃቤ ሕግ ሶሊሴ ካኚሌ ይህንን ውጥረት በደንብ ገልጸውታል።
የሁለትዮሽ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። በማደግ ላይ ያሉ አገራት የማጭበርበር ኔትወርኮችን ለማጥፋት እንዲረዱ ከፈለጉ የበለጸጉ አገራት የቴክኒክ ዕውቀታቸውን እና ሃብቶቻቸውንም ማጋራት አለባቸው።
ከዩናይትድ ኪንግደም የፍራውድ ሚኒስትር ሎርድ ሃንሰን አገሮች ማጭበርበርን ለመከላከል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወይም ባለመተባበራቸው መቅጣት ከንቱ ውጤት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በምትኩ ትኩረቱ "ትብብር" ላይ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
"ማድረግ የምችለው ለወንጀለኞች ማጭበርበርን የበለጠ ከባድ ማድረግ፤ ወጪያቸውን የበለጠ ከፍተኛ ማድረግ፣ ወደ ተጠያቂነት ማምጣት እና ከማጭበርበር የሚያገኙትን ማንኛውንም ሃብት ለማገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለማግኘት ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር መሞከር ነው።"
ባለሥልጣናት እና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በቂ በሆነ መልኩ አብረው እየሰሩ ነው ወይ የሚለው ጥያቄም አለ።
"ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ግዙፍ ኩባንያዎች የበለጠ ተሳትፎ እና የበለጠ መሥራት አለባቸው የሚለው ለረዥም ጊዜ ሃሳቤ ሆኖ ቆይቷል" ሲሉ አሁን ጡረታ የወጡት የቀደምው የእንግሊዝ የመጀመሪያው ብሔራዊ የኢኮኖሚ ወንጀል አስተባባሪ ስቲቭ ሄድ ተናግረዋል።
እአአ በ2014 ከስፔን የሚንቀሳቀሱ ማጭበርበሮችን በማፍረስ የብሪታንያ ዜጎችን በሌሉ አክሲዮኖች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ አግዘዋል።
"እነዚህ የበለጠ ማጠናከር የሚያስፈልገን ከእነዚህ ከትላልቅ ተቋማት ጋር ያሉ ባለብዙ ገፅታ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ናቸው" ሲሉ አክለዋል።
አማዞን እና ሜታን ጨምሮ ዲጂታል ኩባንያዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው የጋራ ስምምነቱ ፈርመዋል። የማጭበርበር መከላከያዎቻቸውንም አጠናክረዋል። የፍቅር ጓደኝነት መድረኩ Match.com የሐሰት አካውንቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና አሁን በየደቂቃው 50 አካውንቶችን እንደሚያስወግድ ተናግረዋል።
ሄድ እንደሚሉት ከሆነ ለስኬታማ እርምጃ መሠረት ለመጣል ማንኛውም የአሠራር እንቅስቃሴ ከመከናወኑ በፊት ጊዜ ይወስዳል። "ይህ አሁንም የጋራ ጥቅምን መፍጠር እና ማሳየት ነው። በአጋሮች መካከል በጋራ መከባበር መተማመንን መገንባት ነው።"
ገንዘቡን አሳዩኝ
ሁሉም ነገር መጥፎና ጨለማ አይደለም። በቪዬና ጉባኤ ላይ የተሳካላቸው በርካታ ሥራዎች በአርአያነት ቀርበዋል።
የቀድሞ አጭበርባሪ እና የቢቢሲ የማጭበርበር ቡድን አባል የሆነው አሌክስ ዉድ፣ በጣም አነስተኛ ቢሆንም ለወደፊት መነሳሳትን ሊፈጥር የሚችል የተሳካ የትብብር ምሳሌ መኖሩን ሰምቷል።
"በአንደኛው ክፍለ ጊዜ በጀርመን አንድ ተጎጂ እንዴት እንደተጭበረበረ እና ገንዘቡ ወደ ሆንግ ኮንግ እንዳመራ የጀርመን ፖሊስ ሲያብራራ ነበር" ብለዋል።
"ፖሊስ በኢንተርፖል ውስጥ የአንድን ሰው የሞባይል ስልክ ቁጥር በአጋጣሚ ይዞ ስለነበር ለዚያ ሰው ስልክ ደወለ። በኢንተርፖል ውስጥ ያለው ሰው በሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚገኝ የሌላ ሰው የሞባይል ስልክ ቁጥር ይዞ ነበር። በዚህ መልኩ ክፍያውን አስቁመው ገንዘቡን መልሰው ለማግኘት ችለዋል።"
ከቪየና የተገኘው ሌላኛው ምሳሌ ደግሞ የጉግል ተወካይ 2.8 ሚሊዮን "አጠራጣሪ መተግበሪያዎች" እንዳይጫኑ ለመከላከል ከሲንጋፖር መንግሥት ጋር እንደሠራ መግለጹ ነው። ወንጀለኞች ሰዎች እንደ ሐሰተኛ የባንክ መተግበሪያዎች "እንዲጭኑ" እያሳመኑ ነበር።
ምንም እንኳን ብዙዎች ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ ችግሩን ለመዋጋት ተስፋ ቢኖራቸውም እንደ ክርስቲ ያሉ ተጎጂዎች ግን ካስተላለፈችው ገንዘብ በተጨማሪ በሰዎች ላይ ያላትን እምነት አጥታለች።
አጭበርባሪዎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር ድንበር ተሻጋሪ መከላከሎችም ፈጣን መሆን አለባቸው።















