ከሆርሙዝ በፊት ዓለም ላይ ምን ያህል የባሕር እንቅስቃሴ እገዳዎች ተጥለዋል? ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ?

አነስተኛ የኢራን ባሕር ኃይል ጀልባ ላይ መሳሪያ ደግነው ያዙ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ሆርሙዝ ወሽመጥን በተመለከተ ግራ መጋባት እጅጉን የታየበት የሳምንት መጨረሻ ነበር።

ጸንቶ ለመርጋት ያልቻለ የተኩስ አቁም ባለበት፣ አርብ ዕለት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወሽመጡ ለንግድ መርከቦች "በቀረው የተኩስ አቁሙ ቀን ሙሉ በሙሉ ክፍት ነው" ሲሉ ተናገሩ።

ነገር ግን ከአንድ ቀን በኋላ አሜሪካ ወደቦቿን መዝጋት በመቀጠሏ የተበሳጨችው ቴህራን፣ አቋሟን በመቀየር ወሽመጡን ዳግም ዘግታዋለች።

ከዚያ በኋላም በርካታ የጭነት መርከቦች በኢራን ጦር እንደተተኮሰባቸው አልያም ወደ መነሻቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ እገዳ መጣሏ ጥንታዊ የወታደራዊ ጫና መፍጠሪያ ስልትን መልሶ ያመጣ ነው።

ይህም የባሕር መስመሮችን በመዝጋት ምጣኔ ኃብታዊ ጫና መፍጠር፣ ንግድን ማስተጓጎል እና ተገዳዳሪው አካል አቋሙን እንዲቀይር ወይም እጅ እንዲሰጥ የማስገደጃ ስልት ነው።

ታሪክ የሚያሳየን እንዲህ ዓይነት ስልቶች ጫና በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ቢሆኑም ሰፊ ተጽዕኗቸው ግን ከሚታሰበው በላይ ውስብስብ መሆኑን ነው።

በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ውስጥ እንደታየው የባሕር ላይ እገዳ መጣል የተፋላሚ ወገንን አቅም በማዳከም ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ አለው።

በጋዛ እና የመን ደግሞ የባሕር ላይ እገዳ ሰብዓዊ ቀውስን ሲያባብስ እንጂ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያመጣ አልታየም።

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ብሪታኒያ ጀርመን ላይ የጣለችው እገዳ

የታሪክ ባለሙያዎች በአንደኛው የዓለም ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩ በረሃብ መሞታቸውን ይገምታሉ፤ የበርሊን ነዋሪዎች ከቆሻሻ ላይ የሚበሉትን ሲፈልጉ በምስሉ ላይ ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, Historica Graphica Collection / Heritage Images / Getty Images

በአንደኛው የዓለም ጦርነት (እአአ 1914-1919) ብሪታኒያ ጀርመን ላይ የጣለችው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እገዳ፣ ብዙውን ጊዜ "በርቀት እገዳ መጣል" በመባል ይጠቀሳል።

ብሪታንያ የጀርመንን ወደቦች በቀጥታ ከመዝጋት ይልቅ፣ የባህር እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በሰሜን ባህር ላይ ባላት የበላይነት ላይ ትተማመን ነበር።

የሮያል የባህር ኃይል መርከቦችን ይፈትሹ የነበረ ሲሆን ገለልተኛ በሆኑ አገሮች ላይ ደግሞ ጫና በማድረግ ጀርመንን ከዓለም አቀፍ ንግድ አግደዋል። ከጊዜ በኋላ ወደ ጀርመን እንዳይጓጓዙ የተከለከሉት ቁሳቁሶች ዝርዝር ከወታደራዊ መሣሪያዎች ባሻገር ምግብና ማዳበሪያን ጨምረዋል።

ጀርመን መጀመሪያ ላይ ከገለልተኛ መንግሥታት እና በአገር ውስጥ ምርት በመተካት በንግድ በኩል የደረሰባትን ተጽእኖ ለመቋቋም ሞክራለች። ነገር ግን ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል፤ እና የዋና ዋና ግብዓቶች እጥረት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርትን ቀንሷል።

ማህበራዊ ቀውሱ በጣም ከባድ ነበር። እአአ በ1916 የተከሰተው የምግብ እጥረት ወደ ቀውስ ተሸጋግሯል። "ተርኒፕ ዊንተር" በመባል የሚታወቀው የዘመኑ ረሃብ እና እርዛት ምልክት ሆነ፤ የታሪክ ምሁራን እንደሚያስረዱት ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በተዛማጅ በሽታዎች ሞተዋል።

እገዳው የጀርመን ሽንፈት ብቸኛ ምክንያት ባይሆንም፣ የታሪክ ምሁራን ግን አገሪቱ ጦርነቱን የመቀጠል አቅሟን በማዳከም ረገድ ዋና ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን ላይ የተጣለው እገዳ

በጃፓን ኦኪናዋ ደሴት እአአ ሚያዚያ 1945 የአሜሪካ ወራሪ ኃይል እና መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, Galerie Bilderwelt / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጃፓን ኦኪናዋ ደሴት እአአ ሚያዚያ 1945 የአሜሪካ ወራሪ ኃይል እና መርከቦች

ጃፓን በባህር በምታስገባቸው ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኗ በተለይ ለእገዳ ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል። በደሴት ላይ እንደተመሰረተች አገር ዘይት፣ ጥሬ ዕቃዎችና ምግብ ለማስገባት እንዲሁም በፓስፊክ ውቅያኖስ የሚገኝ ጦሯን ስንቅ ለማቀበል በመርከብ መጓጓዣዎቿ ላይ በእጅጉ ትተማመን ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1943 ጀምሮ የአሜሪካ የባህር ሰርጓጅ መርከቦች የጃፓንን የንግድ መርከቦችን ዒላማ ያደረጉ ሲሆን በኋላ ላይ ደግሞ በተለይ "ኦፕሬሽን ስታርቬሽን' በተባለው ዘመቻ ወቅት ከአየር ላይ ፈንጂዎችን በመጣል ቁልፍ የባህር መስመሮችን የበለጠ አውካለች።

በጦርነቱ የመጨረሻ ዓመታት የጃፓን የንግድ መርከቦች በአብዛኛው ወድመዋል። ከጦርነቱ በኋላ የተደረጉ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት ይህ ውድመት በጦርነቱ ወቅት ምጣኔ ኃብቷ እንዲላሽቅ ትልቅ ምክንያት ነበር።

ከጀርመን በተለየ መልኩ ጃፓን ጫናውን ለማቃለል ምንም የየብስ መስመር አልነበራትም።

ምንም እንኳን በጦርነቱ እጅ ለመስጠቷ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የአቶሚክ ቦምብ ድብደባዎችን እና የሶቪየት ህብረት ወደ ጦርነቱ መግባትን ጨምሮ፣ የባህር አቅርቦት መስመሮች ማገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

የ1962ቱ ኩባ ላይ የተጣለው 'የባሕር ላይ ከበባ'

የአሜሪካ ኔፕቱን የተባለች የቅኝት አውሮፕላን በኩባ 'የሚሳዔል ቀውስ' ወቅት የሶቪየት የጭነት መርከብ አናት ላይ ስትበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ኔፕቱን የተባለች የቅኝት አውሮፕላን በኩባ 'የሚሳዔል ቀውስ' ወቅት የሶቪየት የጭነት መርከብ አናት ላይ ስትበር

የኩባ የሚሳኤል ቀውስ የባህር ትራንስፖርት ጫናን በተለየ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል። ዩናይትድ ስቴትስ ሆን ብላ እርምጃዋን እንደ እገዳ ከመጥራት ተቆጥባ ነበር። ይልቁንም "ማቆያ" የሚለውን ቃል ከህግ አንድምታዎች ለመሸሽ ትጠቀም ነበር።

በፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የሥልጣን ዘመን፣ የሶቪየት የጦር መሣሪያዎች ወደ ኩባ እንዳይደርሱ ለመከላከል የአሜሪካ የባህር ኃይል ተሰማርቶ ነበር።

ዓላማው ውስን የነበር ሲሆን ተጨማሪ ሚሳኤል ወደ ኩባ እንዳይደርስ ማድረግ እና ከሞስኮ ጋር ለሚደረገው ድርድር ድጋፍ መፍጠር ነበር።

ዘመቻው የቆየው ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ሲሆን በዋናነት እንደ መከላከያ በመሆን አገልግሏል። አንዳንድ የሶቪየት መርከቦች ለጥቃት በመጋለጣቸው ወደ ኋላ ለመመለስ ወስነዋል።

ከጠንካራ ዲፕሎማሲ ጋር ተዳምሮ፣ ውጥረቱ የሶቪየት ሚሳኤሎችን ከኩባ እና በድብቅ ከቱርክ የአሜሪካ ሚሳኤሎችን በማውጣት አብቅቷል። ከተገለጸው ዓላማ አንጻር ሲታይ ከበባው ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ኢራቅ ላይ የጣለው የባሕር ጉዞ ማዕቀብ

የኢራቅ የባስራ ወደብ እአአ በ2003፡ ከ1991ዱ ጦርነት በኋላ የአገሪቱ ብቸኛው ወደብ እና ለዓመታት የተጣሉ መርከቦች የማከማቻ ቦታ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራቅ የባስራ ወደብ እአአ በ2003፡ ከ1991ዱ ጦርነት በኋላ የአገሪቱ ብቸኛው ወደብ እና ለዓመታት የተጣሉ መርከቦች የማከማቻ ቦታ ሆኗል

ኢራቅ እንደ አውሮፓውያኑ በ1990 ኩዌትን ከወረረች በኋላ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት በባህር ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እና ለመገደብ የሚያስችል እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ማዕቀቦችን ጥሏል።

እነዚህ የቁጥጥር መንገዶች እአአ በ1990ዎቹ እና እስከ 2000ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ተግባራዊ ሲሆኑ፣ ኢራቅን በምጣኔ ኃብት ለማግለል እና ለዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ተገዢ እንድትሆን ለማስገደድ ለሚደረጉ ጥረቶች ወሳኝ ነበሩ።

የኢራቅ የባህር መዳረሻ ውስን እንዲሆን በመደረጉ፣ የባህር እንቅስቃሴ እገዳው የነዳጅ ምርቷን ወደ ውጭ እንዳትልክ በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበረው። ሆኖም የየብስ መስመሮች አንዳንድ ማዕቀቦችን እንድታመልጥ መንገድ ከፍተውላታል፤ ይህም የባሕር እገዳው ተጽዕኖ እንዲቀንስ አድርጓል።

በተግባር፣ እነዚህ እርምጃዎች ሰፋ ያለ ማዕቀብ እና ወታደራዊ ጫና ሲኖራቸው በጣም ውጤታማ ነበሩ።

በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ላይ የተጣለው የባሕር ጉዞ ማዕቀብ

የኔቶ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ የባህር ኃይል መርከቦች እአአ በ1992 በጥምረት በሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የጣለውን የባሕር ላይ ማዕቀብ ለማስከበር ተሰማርተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔቶ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ የባህር ኃይል መርከቦች እአአ በ1992 በጥምረት በሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የጣለውን የባሕር ላይ ማዕቀብ ለማስከበር ተሰማርተዋል

በባልካን ጦርነቶች ወቅት፣ የተባበሩት መንግሥታት በዩጎዝላቪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች በባህር ላይ በኔቶ እና በአውሮፓ ኅብረት የጋራ ዘመቻዎች ተግባራዊ ሆነዋል።

እአአ በ1992 እና 1996 መካከል በአድሪያቲክ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ተፈትሸዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ደግሞ አቅጣጫቸውን ቀይረው እንዲሄዱ ወይም እንዲቆሙ ተደርገዋል። በአንጻራዊ ሁኔታ የተጣበበ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ላይ መገኘቱ እገዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የበለጠ ምቹ አድርጎታል።

እነዚህ ተግባራት ማዕቀቦቹን ለመጣስ አስቸጋሪ በማድረግ ውጤታማነቱን አጠናክረዋል። ነገር ግን ግጭቱን በራሳቸው አላቆሙም።

ስምምነት ላይ ለመድረስ ሰፊ የሆነ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና አስፈልጎ ነበር።

የጋዛ እገዳ

የፍልስጤም የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች የእስራኤል የባህር ኃይል እገዳን እአአ በ2018 ለመጣስ ሲሞክሩ

የፎቶው ባለመብት, Majdi Fathi / NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፍልስጤም የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች የእስራኤል የባህር ኃይል እገዳን እአአ በ2018 ለመጣስ ሲሞክሩ

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2007 ጀምሮ በጋዛ ላይ የተጣለ የእንቅስቃሴ፣ የንግድ እና የሀብት ተደራሽነት እገዳ ነው።

እአአ ከ2009 ጀምሮ ጥብቅ እንዲሆን የተደረገው የባሕር ላይ እንቅስቀሴ እገዳ በውቂያኖሱ በኩል የሚደረግ ተደራሽነትን በመገደብ ረገድ አስፈላጊ ነበር። እስራኤል የጦር መሣሪያ በድብቅ እንዳይገባ ለማድረግ ወሳኝ ነው ስትል እርምጃዋን ትከላከላለች። የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች ግን የጋዛን ምጣኔ ኃብት እንዲሁም የነዋሪዎች ሕይወት ክፉኛ ጎድቷል ሲሉ ይሞግታሉ።

የእገዳው ሕጋዊነት አሁንም አከራካሪ ነው። እአአ በ2024 ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስለሚታየዑ ቀጣይ ስጋቶችን አጉልቶ አቅርቧል።

ለዓመታት የተጣሉ ገደቦች ቢኖሩም እገዳው በቀጣናው ውስጥ በተደጋጋሚ የሚደረጉ ግጭቶችን ማስቀረት አልቻለም። ጫናውን ቢቀጥልም ዘላቂ የደህንነት ወይም የፖለቲካ መፍትሄ ግን አላስገኘም።

በሳዑዲ የተመራው የመን ላይ የተጣለው እገዳ

ወረቀት የያዙ ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ለመድረስ ሲንጠራሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው የመን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ አጋጥሟታል

ከ2015 ጀምሮ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በየመን ወደቦችና የአየር ክልል ላይ ለሁቲ አማፂያን የሚደርሱ የጦር መሳሪያዎችን ለማስቀረት በሚል ገደቦችን ጥሏል።

የመን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በብዛት ትጠቀማለች፤ ስለዚህ እነዚህ እርምጃዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የረሃብ አደጋዎችን፣ የነዳጅ እጥረትን እና በጤና አጠባበቅ ስርዓቶች ላይ ጫና እንደሚኖር ደጋግሞ አስጠንቅቋል።

የደህንነት ስጋቶችን ከሰብአዊ ፍላጎቶች ጋር ለማመጣጠን በሚል ፍተሻዎች ቢደረግም ያንን ተከትሎ የተፈጠሩ መዘግየቶች ብዙ ጊዜ አቅርቦትን አስተጓጉለዋል።

እገዳው በሁቲ አማፂያን ላይ ጫና ቢጨምርም፣ ወሳኝ ውጤት ግን አላስገኘም። ይልቁንም ለረዥም ጊዜ የዘለቀ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ትችት አስከትሏል።