ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአሜሪካ የተባረሩ ሰዎችን መቀበል ጀመረች

ንጂሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአሜሪካ የተባረሩ እና ከደቡብ አሜሪካ እንደሆኑ የተገመቱ 15 ሰዎች ዲሞክራቲክ ኮንጎ መድረሳቸው ተገለጸ።

ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን ለመቀበል የተስማማችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ አሁን የተረከበችው ምን ያህል ሰዎችን እንደሆነ አልታወቀም።

የኪንሻሳ መንግስት ሰዎቹ በአገሪቱ ውስጥ የሚቆዩት በጊዜያዊነት እንደሆነ እና ዋሽንግተን "ለአቀባበል፣ ድጋፍ እና እንክብካቤ" ወጪዎች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጿል።

ህገወጥ ስደተኞች ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር ያጠናከረችው አሜሪካ፤ ከዚህ ቀደም ጋና፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤስዋቲኒ ጨምሮ ወደ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች ስደተኞችን አባርራለች።

የኮንጎ መንግሥት ከአሜሪካ ተባርረው መነሻቸው ወዳልሆነ ሦስተኛ አገር የሚላኩ ስደተኞችን የተመለከተውን ስምምነት ይፋ ያደረገው በዚህ ወር መጀመሪያ ነበር።

ስደተኞቹን ለመቀበል የተላለፈው ውሳኔ ከሰብአዊ ክብር፣ ከስደተኞች መብቶች እና ዓለም አቀፍ ህግን ለመከተል ካለው ቁርጠኝነት ጋር የሚጣጣም መሆኑን በወቅቱ ገልጾ ነበር።

የኮንጎ ባለሥልጣናትም ዕቅዱ ስደተኞቹን "በዘላቂ የመቀበል" ውሳኔ ወይም "በፍልሰት ፖሊሲ ገንዘብ የማግኛ ዘዴ" እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት "ከሌሎች መንግሥታት ጋር በሚደረጉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ላይ አስተያየት እንደማይሰጥ" ገልጿል።

ይሁን እንጂ የትራምፕ አስተዳደር "ሕገወጥ እና የጅምላ ፍልሰትን ለማስቆም እና የአሜሪካን የድንበር ደኅንነት ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት" ይቀጥላል ብሏል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በስደተኞች ላይ በያዙት ጠንካራ አቋም አሜሪካ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ሦስተኛ አገራት አባርራለች።

"የሚመለከታቸው ግለሰቦች የውጭ ዜጎችን መግቢያ እና መኖሪያ በተመለከተ ባለው ብሔራዊ ሕግ መሰረት ወደ አገሪቱ ግዛት የሚገቡት ለአጭር ጊዜ በሚሰጡ ፈቃዶች ነው" ሲል የኮንጎ መንግሥት አርብ ዕለት ስለ ተባረሩት ሰዎች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ገልጿል።

ቡድኑ አርብ ማለዳ ላይ ባረፈበት የንጂሊ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የነበሩ ምንጭ በአብዛኛዎቹ ስደተኞች የኮሎምቢያ እና የፔሩ ዜጎች መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግሯረዋል።

ከአሜሪካ የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በወጣው ሪፖርት መሠረት፣ የትራምፕ አስተዳደር እስከ ጥር 2026 ድረስ ወደ ሦስተኛ አገር ለሚላኩ ሰዎች ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቢያወጣም አጠቃላይ ወጪው "አልታወቀም።"

አሜሪካ ለአምስት አገሮች ማለትም ለኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ለሩዋንዳ፣ ለኤል ሳልቫዶር፣ ለኤስዋቲኒ እና ለፓላው ከ32 ሚሊዮን ዶላር በላይ "በቀጥታ" ሰጥታለች።

አሜሪካ እንደ ኮባልት፣ ታንታለም፣ ሊቲየም እና መዳብ ያሉ ወሳኝ ማዕድናትን ለማግኘት ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ስምምነት ለማድረግ እየተደራደረች ነው።

ትራምፕ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ቢያመቻቹም አፈጻጸሙ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ እያለፈ ነው።