አሜሪካ የሩሲያ ነዳጅ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተነስቶ የሚቆይበት ጊዜን ማራዘሟን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አወገዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ የተጣለባት ማዕቀብ ተነስቶ ነዳጇን እንድትሸጥ አሜሪካ ያሳለፈችውን ውሳኔ ተቃወሙ።
አሜሪካ ይህንን እርምጃ በመውሰዷ አገራት እስከ ግንቦት 8/2018 ዓ.ም. ድረስ የሩሲያን የነዳጅ ምርቶች መግዛት ተፈቅዶላቸዋል።
ዋሽንግተን ማዕቀቡ እንዲነሳ የተደረገው አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የኃይል አቅርቦት መስተጓጎል ለማረጋጋት እንደሆነ ትከራከራለች።
ይሁን እንጂ የዩክሬን ፕሬዝዳንት እሁድ ዕለት "ለሩሲያ ነዳጅ የሚከፈል እያንዳንዷ ዶላር ለጦርነቱ የሚውል ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እ.አ.አ የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወረራ ሲከፍቱ ሩሲያ ላይ ሰፊ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የፈፀሙት አውዳሚ ጥቃት ተከትሎ ቴህራን እስራኤልን እና በገልፍ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ጣቢያዎችን አጥቅታለች። ከዚህም ባሻገር የአሜሪካ አጋር በሆኑ አረብ አገራት የኃይል ተቋማት እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች የአፀፋ ጥቃቶችን ፈፅማለች።
ጠባብ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን እና 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ እና ፈሳሽ ጋዝ መጓጓዣ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥም ዘግታለች።
ይህ የዓለም የነዳጅ ገበያን ትርምስ ውስጥ ያስገባ ሲሆን፤ ወሽመጡ በፍጥነት የማይከፈት ከሆነ የዓለም ምጣኔ ሐብት ውድቀት እንደሚገጥመው ተሰግቷል።
አሜሪካ ሩሲያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያላላችው መጋቢት ላይ ነበር። ይህ ውሳኔዋ ከዜሉንስኪ እና አውሮፓውያን አጋሮቻቸው ውግዘት ገጥሞታል።
ባለፈው አርብ አሜሪካ "ነዳጅ ለሚያስፈልጋቸው ተደራሽ መሆኑን ለማረጋገጥ" በሚል ላላ ያለው ማዕቀብ መፈፀሚያ ቀኑ እንደሚራዘም ገልፃለች።
የዩክሬኑ መሪ ሩሲያ ማዕቀቡን ለማምለጥ በሀሰተኛ ሰነድ በሚንቀሳቀስ 110 መርከቦች 12 ሚሊዮን ቶን ነዳጅ አላት ብለዋል።
ሽያጩ ለሞስኮ 10 ቢሊዮን ዶላር ያስገኛል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሩሲያ ገቢውን ዩክሬን ላይ አዲስ ጥቃቶች ለመፈፀም ታውለዋለች ሲሉም ከስሰዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ይህን አኃዛዊ መረጃ ከየት እንዳገኙት አልጠቀሱም።
ባለፈው ሳምንት ሩሲያ "ከ2,360 በላይ የድሮን፣ ከ1,320 በላይ የአየር ቦንቦች እና 60 የሚጠጉ ሚሳኤሎችን ተጠቅማ በተለያዩ ከተሞቻችን እና ማኅበረሰባችን ላይ" ድብደባ ፈፅማለች ብለዋል።
በሚያዚያ የመጀመሪያ ሳምንት ከወሩ ከተፈፀሙ ጥቃቶች እጅግ ከባድ የሆነው ጥቃት በ700 ድሮኖች እና ማሳኤሎች ሲፈፀም በጥቃቱ 18 ሠዎች ተገድለዋል።
ዩክሬንም ሩሲያ ላይ በዋናነት ደግሞ የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ያተኮረ ጥቃት ፈፅማለች።
ምንም እንኳ ጥቃቶች ቢቀጥሉም ጦርነቱ ያለበት ቦታ ላይ መቆሙ እየተነገረ ሲሆን፤ ሩሲያ 20 በመቶውን የዩክሬን ግዛት እንደተቆጣጠረች ናት።
ጦርቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የተጀመረው ጥረት በኢራን ጦርነት ምክንያት ተጓቷል።












