በአሜሪካ አንድ አባት ሰባት ልጆቹን ጨምሮ ስምንት ሕፃናትን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ሊዊዚያና ግዛት አንድ አባት ሰባት ልጆቹን እና አንድ የማይዛመደውን ሕፃን በጅምላ መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ልጆቹ ከአንድ ዓመት እስከ 14 ዓመት እድሜ ያላቸው መሆናቸውን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።
ፖሊስ ጥቃቱ የተፈፀመው ትናንት እሁድ መሆኑን ገልጿል። ተጠርጣሪው በሰረቀው ተሽከርካሪው ከማምለጡ በፊት 10 ሠዎች ላይ መተኮሱን የፖሊስ ቃል አቀባይ ክሪስ ቦርዲሎን ተናግረዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ለማምለጥ ሲሞክር ተከትሎ በወሰደው እርምጃ መግደሉንም ገልፀዋል።
የሕፃናቱን እናት ጨምሮ ሁለት ሴቶች ለሕይወት አስጊ በሆነ ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
ተጠርጣሪው ሻመር ኤልኪንስ ተብሎ ማንነቱ መለየቱን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው ስምንት ልጆችን ከገደለበት ቤት አቅራቢያ አንዲትን ሴት መንገድ ላይ እንደተኮሰባት ፖሊስ ጠቁሟል።
ከተጎጂዎች መካከል አንዱ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ቤት በማምለጥ ለፖሊስ ደውሏል። ከቤቱ ጣሪያ የወደቀ ዘጠነኛው ሕፃን ሆስፒታል እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።
የከተማው ከንቲባ "ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ነው፤ ምን አልባትም በሼርቭፖርት ካየናቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች ውስጥ ዘግናኙ ነው" ብለዋል።
"ይህ ሁሉንም ማኅበረሰብ ይነካል፤ እናም ከእነዚህ ቤተሰቦች ጋር አብረን እናዝናለን።"
ጥቃቱ እ.አ.አ ጥር 2024 ስምንት ሠዎች ከተገደሉበት ጥቃት በኋላ በአሜሪካ እጅግ በጣም ገዳይ የጅምላ ግድያ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
'ገን ቫዮለንስ አርካይቭ' የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የጅምላ ግድያን ከተጠርጣሪው ውጭ አራት እና ከዚያ በላይ ሰዎች በጥይት የተመቱበት ክስተት ሲል ትርጓሜ ይሰጠዋል።
የሼርቭፖርት የፖሊስ አዛዥ ዌይን ስሚዝ "እንደዚህ ዓይነት ሁነት እንዴት ሊከሰት እንደሚችል ማሰብ አልችልም" ብለዋል።
አዛዡ ከተለያዩ የፀጥታ ተቋማት ጋር በመጣመር ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
"ለተፈጠረው ነገር መልስ ለማግኘት ምንም ያህል ቢወስድ በትጋት እንሰራለን" ብለዋል።
ይህን ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ሲሆን፤ ክስተቱን "ልብ ሰባሪ" እያሉ እየገለፁት ነው።












