በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ውሃ እንዴት ከነዳጅ እኩል የግጭቱ አካል ሊሆን ይችላል?

ውሃ የሚጠጣ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, BBC and Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከነዳጅ ሃብት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የሚገመት ጉዳይ ነው። አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ ውሃም ሌላኛው የግጭቱ ማዕከል ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።

ከዓለም አቀፉ ታዳሽ የንፁህ ውሃ ውስጥ የባሕረ ሰላጤው አገራት ድርሻ 2 በመቶ ብቻ ነው። በተለይም ከ1950ዎቹ የነዳጅ ኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ በክልሉ በተፈጠረው ጫና ምክንያት ጨዋማ ውሃ እያጣሩ ይጠቀማሉ።

እንደ የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተቋም ገለጻ 90 በመቶ የሚሆነው የኩዌት ውሃ ከጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ይገኛል። የኦማን 86 በመቶ፣ የሳዑዲ አረቢያ 70 በመቶ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 42 በመቶ ነው።

"በ2021 ወደ ባሕረ ሰላጤው ከእነዚህ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች የሚገኘው አጠቃላይ ዕለታዊ የምርት መጠን ከ20 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ነበር። ይህም በቀኑ 8,000 የኦሎምፒክ የመዋኛ ገንዳዎችን መሙላት የሚያስችል ነው" ሲሉ በኦማን የአካባቢ፣ የዓሳ እና የውሃ ሳይንስ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ዊል ለኩዌስኔ ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

የባሕረ ሰላጤው የግብርና እና የምግብ ምርት በጨዋማ ውሃ ላይ የተመሠረተ ነው። ምክንያቱም በተለምዶ ለመስኖ የሚውለው የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ነው።

እናም ይህ ከፍተኛ ጥገኝነት የውሃ መሠረተ ልማትን ስትራቴጂካዊ ተጋላጭ ያደርገዋል። ለዚህም ነው አሜሪካም ሆነች ኢራን ለማጥቃት ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉት።

ተንታኞች የቴህራንን አካሄድ "ወደ ጎን ማስፋፋት" ሲሉ ይገልጹታል። ይህም ግጭቱ በቀጥታ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ከመቀጠል ወደ ሌሎች አገራት ጭምር የማስፋት አካሄድ ነው። እንደበቀል እርምጃ ቢቆጠርም የውሃ መሠረተ ልማትን ዒላማ ማድረግ የኢራን ስትራቴጂ አካል ይመስላል።

"የባሕረ ሰላጤው መንግሥታት የውሃ መሠረተ ልማታቸው ጥቃት እየደረሰበት ነው ብለው ካመኑ፤ ጦርነቱን ለማስቆም አሜሪካ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ" ሲሉ በኳታር የሚገኘው የሰሜን ምዕራብ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርክ ኦወን ጆንስ ተናግረዋል።

የኢራን ጥቃቶች "ድንጋጤን ለመፍጠር" ያለሙ ሲሆኑ ይህም ሲቪሎች "መቆየት ወይም መሸሽ አለመቻላቸው" ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ኢራን በዱባይ የፈጸመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Fadel Senna / AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የወሃ እጥረት በመኖሩ ለግጭት ምክንያት ሊሆን ይችላል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን በቀጥታ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካን መትታለች ስትል ባህሬን ከስሳለች። ኢራን በበኩሏ ቀደም ብላ የአሜሪካ ጥቃት በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ በሚገኘው ቄሽም ደሴት የሚገኝ የውሃ ተቋምን መጎዳቱ ገልጻለች።

በዱባይ የጄቤል አሊ ወደብ ላይ የተሰነዘሩ የኢራን ጥቃቶችም በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ማዕከላት በአንዱ አቅራቢያ እንደተሰነዘሩም ይታሰባል።

እንዲሁም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚገኘው ፉጃይራህ ኤፍ1 የግል የውሃ እና የኃይል ማመንጫ አቅራቢያ የእሳት አደጋ ሪፖርት መደረጉ ጥርጣሬን ፈጥሯል። ባለሥልጣናት ፋብሪካው ሥራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኩዌቱ ዶሃ ዌስት ማጣሪያም በአቅራቢያው በሚገኙ የወደብ ጥቃቶች ወይም በድሮን ጥቃቶች ምክንያት ጉዳት ደርሶበታል።

"[ለኢራን] ይህ የበለጠ ምልክት ሰጪ አካሄድ ነው" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የውሃ፣ የአካባቢ እና የጤና ዩኒቨርሲቲ ተቋም ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ካቬህ ማዳኒ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ተናግረዋል።

ኢራን የምትወስዳቸው ማንኛውም እርምጃዎቿ በራሷ ላይ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች "ተገቢ" ምላሽ አድርጋ ታቀርባዋለች። በተለይም የባህሬኑን ጥቃቶች በቄሽም ደሴት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የበቀል እርምጃ አድርጋዋለች።

በወሳኝ የውሃ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት የኢራንን አቅም እና ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ምላሽ ለመስጠት ምን ያህል እንደተዘጋጀች ያሳያል።

ማዳኒ አክለውም ኃይሏ በባሕረ ሰላጤው ውድ የውሃ አቅርቦት ላይ ዘላቂ እና ዒላማ የተደረጉ የጥቃት ስጋቶች ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፤ ኢራን ወደፊት በእርግጠኝነት ምን እንደምታደርግ አመላካች አይደለም። ውሃ [በታሪክ] ሁልጊዜ ለማስፈራሪያነት እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሏል" ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጥቃት እንደሚኖር የሚያሳይ የላከችው የስልክ መልዕክት

የፎቶው ባለመብት, Fadel Senna / AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጥቃት እንደሚኖር የሚያሳይ የላከችው የስልክ መልዕክት

ማዳኒ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በሚገኙ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ላይ ቀጥተኛ እና ግልጽ ጥቃቶችን የማትሰነዝረው እራሷ ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን እና በጄኔቫ ኮንቬንሽን አንቀጽ 45 ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

"ሕጉ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ማጥቃት እንደማይቻል ይገልጻል። ነገር ግን [ኢራን] አልጀመረችውም። አባስ አራግቺ [በማኅበራዊ ሚዲያ] ላይ ያቀረቡት ይህንን ነው" ሲሉ ማዳኒ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን አመለካከት በመግለጽ ተናግረዋል።

አራግቺ የቄሽም ደሴትን ጥቃት "ከባድ መዘዝ ያለው አደገኛ እርምጃ…ግልጽ እና ተስፋ አስቆራጭ ወንጀል" ሲሉ ለብዙ መንደሮች የውሃ አቀርቦትን ገድቧል ስላሉት ጥቃት ገልጸዋል።

እነዚህ ክስተቶች ቢቀጥሉም ባይቀጥሉም ከአሜሪካ ጎን የቆሙ አገራት በውሃ ደኅንነት ረገድ ያላቸውን ደካማነት ያጎላዋል። ኢራንም ተጋላጭ ነች።

ምንም እንኳን ማዳኒ የውሃ አቅርቦቷ ከባሕረ ሰላጤው ጎረቤቶቿ በተሻለ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኝ እና በጨዋማ ውሃ ማስወገጃ ላይ ብዙም ጥገኛ እንዳልሆነች ጠቁመዋል።

ሌሎች ታዛቢዎች በበኩላቸው ኢራን በባሕረ ሰላጤው ወሳኝ የውሃ መሠረተ ልማቶች ላይ የምትሰነዝራቸው ማናቸውም ጥቃቶች በራሷ ላይ የበቀል ጥቃቶችን ሊጋብዙ ይችላሉ።

ኢራን ከጊዜ ወደ ጊዜ "ወደ ፍጹም የውሃ እጥረት" እየተቃረበች ነው። ዝቅተኛ የዝናብ መጠን፣ "በዋና ከተማዋ ለዓመታት ባገለገለ የውሃ መሠረተ ልማት ምክንያት በተፈጠረ የውሃ መፍሰስ" እና ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር የተደረገው የ12 ቀናት ጦርነት ለእጥረቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲሉ የኢነርጂ ሚኒስትር አባስ አሊያባዲ ተናግረዋል።

በመላ አገሪቱ የሚገኙ ግድቦች "በአሳሳቢ ሁኔታ" ውስጥ ናቸው ሲሉ የኢራን ብሔራዊ የአየር ንብረት እና የድርቅ አስተዳደር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አህመድ ቫዚፌህ ተናግረዋል።

ዋና ዋና የሚባሉት የውሃ ማጠራቀሚያዎች ከመጠን በላይ ተጎድተዋል፤ እንደ ዛያንዴህ ሩድ ያሉ ወንዞች እና የኡርሚያ ሐይቅም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ፍሬድ ፒርስ እንደሚሉት ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ የግድብ ግንባታ፣ የውሃ አጠቃቀምን የሚጨምር ግብርና እና የአስተዳደር ጉድለት ሁኔታውን አባብሶታል። በአንዳንድ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ማውጣት በመስፋፋቱ ከባድ የመሬት መሸርሸርን አስከትሏል።

ቴህራን አንድ ቀን ውሃ በወረፋ ማከፋፈል ወይም በከፊል ነዋሪዎችን ማስለቀቅ ሊኖርባት እንደሚችል ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።

በደረቀው የዛያንዴህ ወንዝ ድልድይ አቅራቢያ ቆሞ ስልኩን የሚጠቀም ኢራናዋኢ

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ደግሞ የኢራንን ውስጣዊ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ መቋቋምን የሚጎዳ የአካባቢ እና የአገር ደኅንነት ስጋት ነው። ጉዳዩን የሚያባብሰው ደግሞ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለሳምንታት የዘለቀው ከባድ ግጭት መጨመሩ ነው።

ከጦርነቱ በፊት የውሃ እጥረት በኢራን ውስጥ ለተከሰተው አለመረጋጋት አስተዋጽኦ አድርጓል። ከኑሮ ውድነት እና ከፖለቲካው ጋር ተዳምሮ በኩዜስታን፣ በኢስፋሃን እና በሌሎች ቦታዎች ተቃውሞዎች ተነስተው ነበር።

የኢራን የውሃ ተግዳሮቶች ከክልላዊ ውጥረት ጋርም ይያያዛሉ። በሄልማንድ ወንዝ ዙሪያ ከአፍጋኒስታን ጋር በጤግሮስ እና በኤፍራጥስ ግድቦች ዙሪያ ቱርክ እንዲሁም ከኢራቅ ጋር በውሃ መጋራት ዙሪያ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አለመግባባት አላት።

ጦርነቱ የመካከለኛው ምሥራቅ የውሃ አቀርቦት ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ ተንታኞች ይገልጻሉ።

የግጭቱን አቅጣጫ እና ቆይታ እንዴት ሊቀይሩ እንደሚችሉ ያሳያል። አካባቢያዊ ጫናዎች እንደ ነዳጅ እና ጋዝ ክምችት ካሉ ነገሮች ጋር በመሆን ግጭቱን እንዳያባብሱ ያሰጋሉ።

በክልሉ ውስጥ የወደፊት ሊኖሩ የሚችሉ ግጭቶች የሚወሰኑት በነዳጅ ቧንቧ እና በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ብቻ ሳይሆን በወንዞች፣ በውሃ ማጠራቀሚያዎች እና በጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ጭምር ይሆናል። በዚህ ግጭት እና ከዚህ በኋላም ውሃ ከነዳጅ የበለጠ ዋነኛ ጉዳይ ሊሆን ይችላል።