አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በፈጸመችባቸው አገራት ምን ተከሰተ?

የፎቶው ባለመብት, Gilles BASSIGNAC/Gamma-Rapho via Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ጦርነት ተመልሳለች። ዋሽንግተን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በቀጣናው በተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተሳተፈች ሲሆን፣ ሁሉም ያመጡት ውጤት ላይ በአንድ ድምጽ ከስምምነት መድረስ አይቻልም።
አሁን አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በጥምረት በመሆን በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የተጀመረው ጦርነት የአገሪቱን ከፍተኛ መሪ አሊ ኻሜኒን ገድሏል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን መሪ በማስወገድ፣ የአገሪቱን የኒውክሌር ፕሮግራም ማስቆም እንዲሁም የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ፍላጎታቸው ነው።
ትራምፕ በቀጣናው ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ የአሜሪካ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት አይደሉም።
አባት እና ልጁ ጆርጅ ቡሽ እንዲሁም ባራክ ኦባማ ቀደም ሲል በኢራቅ ከሳዳም ሁሴን ጋር ወይም በሊቢያ ከሙአመር ጋዳፊ ጋር ጦርነት ገጥመው ነበር።
የእነዚህ መሪዎች ከሥልጣን መወገድ ለአገራቱ ዲሞክራሲንም ሆነ የናፈቁትን ነጻነት አላስገኘም። ከዚያ ይልቅ በአገራቱ ውስጥ እስካሁን የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት እና አለመረጋጋት ፈጥሯል።
በሶሪያ አሜሪካ እስላማዊ መንግሥት በማለት የምትጠራውን ቡድን ለማስወገድ ድጋፍ ያደረገች ቢሆንም በ2024 አል አሳድ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሌሎች እስላማዊ ቡድኖች ሥልጣን ተቆጣጥረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍጋኒስታን፣ የታሊባን አገዛዝ አሜሪካ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በአገሪቱ ውስጥ ጣልቃ ከገባች በኋላ በ2021 ወደ ሥልጣን ተመልሷል።
በኦባማ አስተዳደር ወቅት ዲፕሎማት እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት ፊሊፕ ጎርደን በአውሮፓውያኑ 2015 ባወጡት ጽሑፍ አገራቸው በቀጣናው ውስጥ ያደረገቻቸው ጣልቃ ገብነቶች ቀውስ ማስከተላቸውን አስፍረዋል።
"በኢራቅ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ ገብታ አገሪቱን ተቆጣጠረች፤ ውጤቱም እጅግ ውድ ዋጋ ያስከፈለ ነበር። በሊቢያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ ገብታ አገሪቱን አልተቆጣጠረችም፣ ውጤቱም እዚህም የከፋ ነበር። በሶሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ አልገባችም ወይም አገሪቱን አልተቆጣጠረችም ውጤቱ ደግሞ ከባድ ነበር።"
ባለሙያዎች እንደሚሉት የአሜሪካ በአገራት ውስጥ ጣልቃ መግባት ለራሷ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ቀጣናውን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ ነበር።
በካይሮ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ኢብራሂም አዋድ "በአካባቢው ያለው አለመረጋጋት በአብዛኛው የሚከሰተው ከውጭ በሚኖር ጣልቃ ገብነት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ሙንዶ ያስረዳሉ።
ምንም እንኳን ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ ወይም የመን ከባድ የአስተዳደር ችግሮች የሰፈነባቸው ወይም አምባገነን ሥርዓቶች ያሏቸው አገራት ቢሆኑም፣ እነዚህ ጉዳዮች በአዋድ አስተያየት "በውጭ ጣልቃ ገብነት ሊፈቱ የሚችሉ" አልነበሩም።
ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ በርካታ አገራት ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ፈጽማለች። አንዳንድ ጊዜ የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ደጋፊ ሚና በመያዝ ወይም የሰፊ ጥምረት አካል የሆነችበት ጊዜያት አሉ።
ለመሆኑ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አሜሪካ በየትኞቹ አገራት ውስጥ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ፈጽማ ምን ተከሰተ?

የፎቶው ባለመብት, Scott Nelson/Getty Images
ኢራቅ
ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅ ላይ በተደጋጋሚ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ፈጽማለች።
ኢራቅ በሳዳም ሁሴን አመራር ስር ሳለች በአውሮፓውያኑ 1990 የኩዌት የነዳጅ ዘይትን ለመቆጣጠር እና ቀጣናዊ የበላይነቷን ለማጠናከር ወረራ ፈጽመለች።
በዋሽንግተን የሚመራ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ ወታደራዊ ጥምረት "ኦፕሬሽን ዴዘርት ስቶርም" [ዘመቻ የበረሃው ማዕበል] የተባለ ዘመቻ አካሂዶ ኩዌትን ታድጋታለች።
ጥምረቱ በከፍተኛ የአየር ድብደባዎች እና ፈጣን በሆነ የእግረኛ ወታደሮች ስምሪት የታገዘ ነበር። ይህ ዘመቻ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኢራቅ ጦርን በማስወጣት ኩዌትን ነፃ ማውጣት ችሏል።
በወቅቱ ሳዳም ሁሴን ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን፣ በአገር ውስጥም አለመረጋጋት እንዲቀሰቀስ እና የጎሳ ውጥረትን እንዲባባስ አድርጎ ነበር።
ይህ ዘመቻ በብዙዎች ዘንድ ዓለም አቀፍ ሕግን ወደነበረበት የመለሰ ወታደራዊ ስኬት ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር።
ከበርሊን ግንብ መፍረስ እና ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የተካሄደው ይህ የባሕረ ሰላጤው ጦርነት የአሜሪካን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አዲስ ዘመን ተደርጎ ተቆጠረ።
ዋሽንግተን ያለ ተቀናቃኝ አዲስ የዓለም ሥርዓት መሠረተች።
በአውሮፓውያኑ 2003፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚመራ ሌላ ጥምረት፣ አገዛዙ የጅምላ እልቂት መሳሪያዎች መታጠቁን እና ከዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት እንዳለው በመግለጽ ኢራቅን ወረረ።
ኢራቅ አላት የተባሉት የጦር መሳሪያዎች ባይገኙም፤ ጥምረቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ባግዳድ ደርሶ ሳዳም ሁሴንን በቁጥጥር ስር በማዋል በስቅላት ቀጣ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን አገሪቱ በሱኒዎች፣ በሺዓዎች እና በኩርዶች መካከል በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት መታመስ የጀመረችው ወዲያው ነው።
ከዚህም ባሻገር በአውሮፓውያኑ 2014 አና 2015 የኢራቅን አንድ ሦስተኛ እንዲሁም ከፊል ሶሪያን የተቆጣጠረው ኢስላሚክ ስቴት እንዲመሠረት መንገድ ጠርጓል።
አሜሪካ ከወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በኋላ ስለሚፈጠረው ሁኔታ ጠንካራ ዕቅድ ያልነበራት ሲሆን፣ የኢራቅ ጦር እና የፀጥታ ኃይሎች መፍረስን የመሳሰሉ ስትራቴጂክ ስህተቶች መሥራቷ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሠራዊቱ አባላት ሥራ አጥ እንዲሆኑ አድርጓል።
በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ታጣቂዎችን እንዲቀላቀሉ መንገድ ሲጠርግ አገሪቱን አሁንም ድረስ ለሚያናውጣት አለመረጋጋትም አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከአውሮፓውያኑ 2003 ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ሲከታተል የቆየው የ'ኢራቅ ቦዲ ካውንት ፕሮጀክት' እንደሚለው፣ ሰላማዊ ዜጎችን እና ተዋጊዎችን ጨምሮ ቢያንስ 300 ሺህ ሰዎች በግጭቶች ምክንያት ሞተዋል። ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም በጣም ከፍ ያለ እንደሆነ ያምናሉ።
ኢብራሂም አዋድ የዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ ገብነት "ኢራቅን በማኅበረሰቦች መካከል እንድትከፋፈል አድርጓል። ዴሞክራሲን፣ ዘመናዊነትን እና ከሃይነኖት ነጻ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓትን በሚፈልጉ እና በሚቃወሙ መካከል የተፈጠረው ክፍፍል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ እና እንደ አይኤስ ያሉ ታጣቂዎች የሚሳተፉባቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ አድርጓል" ብለዋል።
አፍጋኒስታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ በ2001 ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች የኔቶ አባል አገራት ጋር በመሆን በአፍጋኒስታን ውስጥ በታሊባን አስተዳደር ላይ 'ኦፕሬሽን ኢንዱሪንግ ፍሪደም' የተሰኘ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታ ነበር።
ዋሽንግተን ወረራ ለማድረግ የወሰነችው በ1996 አገሪቱን የተቆጣጠረው አክራሪ የእስልምና ንቅናቄ በመስከረም 11/2001 በኒው ዮርክ በሚገኙት መንትያ ሕንጻዎች እና ፔንታጎን ላይ በተፈፀመው ጥቃት እጁ ያለበትን የአል ቃኢዳ ቡድን መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው።
ጣልቃ ገብነቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የታሊባንን አገዛዝ በማስወገድ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚደገፍ አዲስ መንግሥት መመስሥረት ችሏል፣ ነገር ግን ጦርነቱን አላስቆመም።
ግጭቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ ሲሆን፣ ታሊባን ከመጥፋት ይልቅ እንደገና እንዲጠናከር እና ከአሜሪካ እና ከኔቶ ወታደሮች ጋር እንዲፋለም አድርጓል።
በ2020 የአሜሪካ ጦር በርካታ ቦታዎችን በታሊባን ከተነጠቀ በኋላ አገሪቱን ለቅቆ ለመውጣት ድርድር አድርጓል። ይህም በ2021 ግንቦት ወር የጀመረ ሲሆን፣ ታሊባን በነሐሴ 2021 ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላም ተፋጥኗል።
በአውሮፓውያኑ 2003 በኢራቅ የተጀመረው ጦርነት የአሜሪካን ትኩረት እና ወታደራዊ ኃይል ከአፍጋኒስታን እንዲርቅ አድርጓል።
ከዚህም በላይ አል ቃኢዳን ለማጥፋት ተይዞ የነበረው ዋነኛ ዓላማ ወደ "አገር ግንባታ" ፕሮጀክት ተሸጋግሯል። ይህም በኢራቅ ላይ በነበረው ጣልቃ ገብነት እንደተስተዋለው ሁሉ ይህንን ለማሳካት የሚያስችል ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ወይም የጋራ መግባባት አላስቀመጠም።
ከታሊባን ከሥልጣን መወገድ በኋላ የተቋቋሙት የጦር ሠራዊትና የፖሊስ ኃይል በጣም ደካማ እና ከምዕራባውያን ኃይሎች በሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ነበሩ።
እነዚህ ኃይሎች የአሜሪካ ጦር ጠቅልሎ ሲወጣ የታሊባንን ግስጋሴ መቋቋም አቅቷቸው በፍጥነት ፈርሰዋል።
በአሜሪካ ብራውን ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው "ኮስትስ ኦፍ ዋር ፕሮጀክት" መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ የ20 ዓመት ጣልቃ ገብነት እና ከዚያ ጋር በተያያዘው ግጭት ምክንያት ሰላማዊ ዜጎችን፣ የታሊባን ተዋጊዎችን እና የምዕራባውያን ወታደሮቸን ጨምሮ ከ176 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ይህ መረጃ በአገሪቱ በበሽታ ወይም በረሃብ ምክንያት የሚሞቱትን የሚጨምር አይደለም።
ሊቢያ

የፎቶው ባለመብት, Mario Tama/Getty Images
የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ አሜሪካ በ2011 በተሳተፈችበት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የተወገዱ ሌላ አምባገነን መሪ ናቸው።
ከአውሮፓውያኑ 1969 ጀምሮ አገሪቱን በጠንካራ ክንዳቸው ሥር አድርገው የመሩት ጋዳፊ ተቃውሞ የተነሳባቸው በአረብ አገራት የተቀጣተለውን ሕዝባዊ አመጽን ተከትሎ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ይህንን ሕዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ጸጥ ለማሰኘት ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ ወስደዋል።
ከዚያም በአገዛዙ ኃይሎች እና በአማፂ ቡድኖች መካከል ግጭት ተፈጠረ፤ እነዚህም ግጭቶች በመላ አገሪቱ ተዛመቱ።
በምላሹም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አገሪቱን ከማንኛውም በረራ ነጻ የሆነ ቀጣና እገዳ ሲጥል፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ሕዝባዊ ተቃውሞውን በመደገፍ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ።
በአሜሪካ እና በሌሎች የኔቶ አባል አገራት የታገዘው የአማፂያኑ ግስጋሴ በጥቅምት 2011 ትሪፖሊን አንዲቆጣጠር አድርጎታል። ከዚያም በኋላ ጋዳፊን ከተደበቁበት በማውጣት ገድለዋቸዋል። በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ እንደተከሰተው ሁሉ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚያ አላበቃም።
የጋዳፊ ከሥልጣን መወገድ ጥምረቱ ያልተዘጋጀበትን የሥልጣን ክፍተት ፈጥሯል። እንዲሁም እንደ እስላማዊ መንግሥት ያሉ አክራሪ ቡድኖችን ጨምሮ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች እና ሚሊሻዎች እንዲነሱ አድርጓል።
አዲስ እና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል የረዥም ጊዜ ጣልቃ ገብነት የማይፈልጉት ዓለም አቀፍ ኃይሎች ከሙአመር ጋዳፊ መገደል በኋላ ዘመቻቸውን አቁመው፣ አልፎ አልፎም የአየር ጥቃት በመሰንዘር የምክር እና የሥልጠና ድጋፍ በመስጠት ብቻ ራሳቸውን ገድበዋል።
በካይሮ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት እና የስደተኞች ጥናት ማዕከልን የሚመሩት አዋድ፣ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች እና ስደተኞችን ተቀባይ በሆነችው ሊቢያ ውስጥ የተካሄደው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት "አገሪቱን ለማስተዳደር ምንም ዓይነት ዕቅድ ሳይኖር በመሆኑ በቀላሉ ውስጣዊ ግጭትን እና ከባድ የኢኮኖሚ ቀውሶችን አስከትሏል።"
አገሪቱ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ቡድኖች መዋቅሮች ተከፋፍላ እና አለመረጋጋት ውስጥ ተዘፍቃ ትገናለች። መቀመጫውን በትሪፖሊ ያደረገው እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የብሔራዊ አንድነት መንግሥት መላውን አገሪቱን አይቆጣጠርም።
ሶሪያ

የፎቶው ባለመብት, DELIL SOULEIMAN/AFP via Getty Images
በአውሮፓውኑ 2011በአረብ አገር የተቀሰቀሰው እና አምባገነናዊ ሥርዓቶችን ለመጣል የተካሄደ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከናጣቸው አገራት መካከል አንዷ ሶሪያ ነበረች።
የባሻር አል አሳድ አገዛዝ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በኃይል በማፈን በመላ አገሪቱ የተዛመተ እና ከ15 ዓመታት በላይ የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት አስነስቷል።
በመጨረሻም ጦርነቱ የውስጥም ሆነ የውጭ ተዋናዮችን በማሳተፍ ባለብዙ ገጽታ ግጭት ሆነ።
እንደ አል ቃኢዳ እና ኢስላሚክ ስቴት ያሉ አክራሪ ቡድኖችን ጨምሮ፣ የኩርድ ኃይሎችን እና ሶሪያን ለመቆጣጠር የሚፎካከሩ የተለያዩ ኃይሎች በእርስ በርስ ጦርነቱ ተሳትፈዋል።
በሶሪያ ውስጥ ጎራ ለይተው ከባሻር አል አሳድ መንግሥት ጋር የሚፋሉት ኃይሎች ብቻቸውን አልነበሩም።
ሩሲያ እና ኢራን ለአገዛዙ ኃይሎች ወታደራዊ ድጋፍ ሲሰጡ፣ ቱርክ ደግሞ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በሚያደርጉት ውጊያ የሱኒ አማፂ ቡድኖችን ታስታጥቅ፣ ታሠለጥን እና የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2014 ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ግጭቱ በመግባት የሶሪያን ከፊል እና የኢራቅን አንድ ሦስተኛ ግዛቶች የተቆጣጠረውን ኢስላሚክ ስቴት ተዋግተለች።
የአሜሪካ አየር ኃይል ድብደባዎች ጽንፈኛውን ቡድን ሲያዳክሙ ይዟቸው የነበሩ ስፍራዎችን እንዲለቅ አድርገዋል።
ዋሽንግተን በኩርዲስታን ለሚገኙት የአማፂ ቡድኖች በተለይም ለሶሪያ ዴሞክራቲክ ኃይሎች ድጋፍ አድርጋለች። በዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመንም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ የኬሚካል ጥቃቶችን ለመቀበል በባሻር አል አሳድ መንግሥት ላይ የሚሳዔል ጥቃቶቸን ፈጽማለች።
በዚህ ወቅት ከአሜሪካ ወገን የባሻር አል አሳድን መንግሥት ከሥልጣን ለማውረድ ፍላጎት ስለመኖሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
በ2013 በተቃዋሚዎች ይዞታ ሥር ባለችው እና ከደማስቆ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ምሥራቃዊቷ ከተማ ጉታ በደረሰ የኬሚካል ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።
ምዕራባውያን እና የአሳድ ተቃዋሚዎች ለጥቃቱ የአሳድን አስተዳደር ተጠያቂ አድርገዋል።
የአሳድ አስተዳደር ይህንን አስተባብሏል። በዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት የኬሚካል መሣሪያዎችን አስወግዷል።
ሆኖም ግን ይህ እርምጃ ጦርነቱን አላቆመውም። በሶሪያ ጦርነት የኬሚካል ጥቃት ቀጠለ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች በሰዎች ላይ ግድያዎችን፣ መድፈርን እና ማሰቃየትን ጨምሮ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸው ገልጿል።
በ2015 የአሳድ አስተዳደር የአገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች መቆጣጠር ባለመቻሉ ለመውደቅ ተቃርቦ ነበር። ሆኖም ሩሲያ ጣልቃ ገብታ ቁልፍ ግዛቶች በአሳድ ቁጥጥር ሥር መልሰው እንዲገቡ አስችላለች።
በኋላም በአሕመድ አል-ሻራ የሚመራው አማፂ ቡድን የአገሪቱን ሥልጣን ሲረከብ ባሻር አል አሳድ ወደ ሩሲያ ተሰድደዋል።
የመን

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ ከ9/11 ጥቃቶች ወዲህ በየመን ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ላይ በተፈፀመው የፀረ-ሽብር ዘመቻ በተደጋጋሚ ተሳትፋለች።
የመን በአውሮፓውያኑ 2014 ወደ የእርስ በርስ ግጭት የገባችው በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን ዋና ከተማዋን ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ።
በአውሮፓውኑ 2015 በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ የአረብ አገራት ጥምረት በአማፂያኑ ላይ ጣልቃ በገባበት ወቅት፣ ዋሽንግተን ምንም እንኳ እግረኛ ጦሯን ባትልክም፣ የጦር መሣሪያዎችን ሸጣለች እንዲሁም የሎጂስቲክስ እና የስለላ ድጋፍ ሰጥታለች።
የሁቲ አማፂ ቡድን በአሁኑ ጊዜ የየመንን ግዛት 30 በመቶ የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል በሚል ይከሰሳል።
እስራኤል በሐማስ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ማካሄድ ከጀመረችበት ጊዜ ጊዜ አንስቶ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽሟል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከሌሎች አጋሮቿ ጋር በመተባበር፣ የቀጣናውን የባሕር ትራንስፖርት ለመጠበቅ የሁቲ ወታደራዊ ስፍራዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ደብድባለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በጣም ድሃ የሆነችው የመን፤ ለዓመታት በዘለቀው አለመረጋጋት ምክንያት በተባባሰ ጥልቅ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
በ2023 በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ377 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ሲል ካምፔይን አጌንስት አርምስ ትሬድ የተሰኘው ድርጅት ገልጿል።
እነዚህ ሞቶች የተመዘገቡት በአብዛኛው እንደ ረሃብ፣ በሽታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን አለማግኘት ባሉ የግጭቱ ተዘዋዋሪ ጦስ ምክንያት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮውን በሰብአዊ እርዳታ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ቤት ውጪ ናቸው።















