ትራምፕ የኢራን ኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያዘገዩት ለዲፕሎማሲ ወይስ ውጥረት ለማርገብ?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የሚሰነዘረውን ማንኛውንም ጥቃት ለተጨማሪ 10 ቀናት ለማዘግየት የወሰኑት ውሳኔ ለአራት ሳምንታት ያህል በዘለቀው ግጭት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጊዜ ገደቦችን በማክበር ያላቸው ቁርጠኝነት ተለዋዋጭ ነው።
ይህንን ጥቃት ለሁለተኛ ጊዜ ያራዘሙ ቢሆንም እርምጃቸው የቴህራንን ትኩረት ለመስረቅ ወይንም ጊዜ ለመግዛት የተደረገ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ የኢነርጂ መሠረተ ልማቷን ሙሉ በሙሉ "እናወድማለን" ሲሉ ከዛቱ በኋላ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች ተቋማት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች።
ይህም ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና በዓለም አቀፍ ምጣኔ ኃብት ማንሰራራት ላይ ጥላውን ያጠላ ሆኗል።
ትራምፕ ዓለም አቀፍ ገበያዎችን እንደገና ለማረጋጋት ሊፈልጉ ይችላሉ። የአሁኑን የጊዜ ገደማ የማራዘም ውሳኔ ይፋ ያደረጉት የዎል ስትሪት ግብይት ከተዘጋ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ይፋ ስለሆነ ተጽዕኖውን መናገር አይቻልም።
ፕሬዝዳንቱ የፋይናንሱ ዓለም በዲፕሎማሲው መስክ ሊኖሩ ስለሚችሉ መፍትሔዎች ያላቸውን ተስፋ ከፍ ለማድረግ ፈልገው ይሆናል።
በእርግጥም ዋይት ሐውስ ከገባበት የስትራቴጂክ ቅርቃር ለማውጣት እና የፖለቲካ መፍትሔ ለማግኘት ሌላ 10 ቀናት ጊዜ ይሰጠዋል።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው። በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የመልዕክት ልውውጦች በተለይ በፓኪስታን በኩል እየተካሄዱ ነው።
ሁለቱም ወገኖች በአብዛኛው የማይታረቁ የጥያቄዎች ዝርዝር እያቀረቡ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሁንም በፓኪስታን ውይይት ሊደረግ እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ዲፕሎማቶች የሚጠበቀው ነገር ዝቅተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
"ብዙ የሚያሳስቱ እና የሚያወናብዱ ነገሮች አሉ" ሲል አንድ ግለሰብ ተናግሯል። "አንዳንድ ጉዳዮችን በበቂ ሊያስተናግድ የሚችል አስተማማኝ የግንኙነት መስመር ብቅ ይላል የሚል ጥርጣሬ አለ"።
ነገር ግን ለጊዜው ፕሬዚዳንቱ ውይይቶች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆናቸውን አጥብቀው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ በኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ ለመሰንዘር የያዘችውን ዕቅድ ማዘግየቷ ለመዘጋጀት አልያም ከዚያ በላይ ለማድረግ ጊዜ ይሰጣታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ 2,000 የሚጠጉ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ወታደሮችን ያቀፈ ኃይል ከጃፓን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየሄደ ነው። ከካሊፎርኒያ ወደ ቀጣናው የሚሄዱ በርካታ ሺህ የአሜሪካ አየር ወለዶችም አሉ።
ዎል ስትሪት ጆርናል ተጨማሪ 10,000 ወታደሮች ወደ ባሕረሰላጤው አገራት ሊላኩ እንደሚችሉ የዘገበ ሲሆን ፔንታጎን ግን አስተያየት አልሰጠም።
እነዚህ ሁሉ ወታደራዊ ኃይሎች ለመሰባሰብ እና ለመቀናጀት ጊዜ ይወስዳሉ። ትራምፕ የቀነ ገደቡን ማራዘማቸው ምናልባት ለዚህ ጊዜ እየገዙ ይሆናል።
ግን ለምን ዓላማ? ፕሬዝዳንቱ ለራሳቸው ወታደራዊ አማራጮችን እየሰጡ ነው? በእርግጥ ኢራን ውስጥ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እያሰቡ ነው? ወይስ ለኢራን መሪዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ካለበለዚያ የከፋ መዘዝ እንዲገጥማቸው ለመጠቆም እየሞከሩ ነው?
"ስምምነት ላይ ካልደረሱ የከፋው ቅዠታቸው እኛ እንሆናለን" ሲሉ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል። "እነሱን መደብደባንን እንቀጥላለን።"
ትራምፕ ምንም ያስቡ ምን የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን ለማጥቃት የወሰኑት ውሳኔ ማዘግየታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ያጠናክራል።
ይህ ማለት በወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች ይቀጥላሉ፤ የኢራን የአጸፋ እርምጃዎች ይቀጥላሉ ማለት ነው። የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ለአብዛኛዎቹ መርከቦች እንቅስቃሴ ዝግ ሆኖ ይቆያል የሚለውንም ያሳያል።
የዶናልድ ትራምፕ የጊዜ ገደብም የባሕር ወሽመጡን አለመክፈት መዘዝ እንደሚያስከትል ማሳየት ዋናው ነጥብ ነው።
የጊዜ ገደቡ ማራዘሚያ ኢራን በባህረ ሰላጤው ላይ የጣለችውን ገደብ ለተጨማሪ አስር ቀናት እንድትቀጥል ውጤታማ በሆነ መንገድ ያስችላታል።
የአገዛዝ ለውጥ እና ኢራንን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ስለማውጣት ተወርቶ የተጀመረው ጦርነት በአብዛኛው የዓለም ኢኮኖሚ የሚመካበትን ጠባብ የውሃ መስመር የሚቆጣጠረው ማን ነው የሚለው ጥያቄ ላይ የቆመ ይመስላል።















