ሩሲያ ወዳጇን ኢራንን ለመርዳት እስካሁን ምን አድርጋለች?

ፕሬዚዳንት ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, ATTA KENARE/GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ ከኢራን ጋር "ስትራቴጂካዊ አጋርነት" ብትፈራረምም እስካሁን ያደረገችው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በአውሮፓውያኑ 2025 ጥር ወር ላይ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ወደ ሞስኮ አምርተው ነበር። በዚህ ብዙ በተወራለት ጉብኝት ሁለቱ አገራት ሁሉን አቀፍ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

ከዓመት በኋላ የአሜሪካ እና የእስራኤል ሚሳዔሎች ቴህራን ላይ መዝነብ ሲጀምሩ ሩሲያ በአጭር መግለጫ ያላትን አጋርነት ከመግለጽ ባለፈ ይህ ነው የሚባል እርዳታ ማድረግ አልቻለችም።

ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ እና ከጎረቤቶቿ የቀድሞው የሶቪየት ኅብረት አገራት ጋር እንዳላት ስምምነት ከኢራን ጋር የተፈራረመችው ሁሉን አቀፍ አጋርነት "የጋራ መከላከያ አንቀጾችን" አልያዘም።

ስለዚህ ቴህራንን በጦር ለማገዝ አትገደድም።

ለአራት ሳምንታት በዘለቀው የኢራን ጦርነት ሞስኮ ለቴህራን ቢያንስ በግልጽ የሚታወቅ የቁሳቁስ ድጋፍ አልሰጠችም።

ምናልባት በሁለቱ አገራት ግንኙነት ውስጥ ከመጋረጃ ጀርባ የሚከናወኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ እና የዩክሬን ምንጮች ሩሲያ ወሳኝ የሆኑ የደኅንነት መረጃዎችን ለኢራን ትሰጣለች ሲሉ ይከስሳሉ።

ከእነዚህም መካከል በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች የሚገኙባቸውን ቦታዎች ለቴህራን አሳልፎ መስጠት የተጠቀሰ ቢሆንም፤ ሞስኮ ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ሞስኮ ለወዳጅዋ ቴህራን የምትሰጠው ድጋፍ አለመኖሩ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምን ያህል አቅሟ የተገደበ መሆኑን ያሳያል።

ነገር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት በተራዘመ ቁጥር በነዳጅ ዋጋ መናር እና በምዕራባውያን ትኩረት መከፋፈል የተነሳ ተጠቃሚ መሆኗን ልታሰላ ትችላለች።

ሞስኮ ለቴህራን ምን ዓይነት ድጋፍ በይፋ ሰጥታለች?

የኢራን ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ክሬምሊን የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃቶችን በተደጋጋሚ ሲያወግዝ፣ የሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን ደግሞ የኢራንን እምቢተኛነትን አሞካሽቷል።

ሞጅታባ ኻሜኒ የኢራን አዲስ ጠቅላይ መሪ ሆነው በተሾሙበት ወቅት ፕሬዝዳንት ፑቲን የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ሞስኮ ለቴህራን ያላትን "የማያወላውል ድጋፍ" አረጋግጠዋል።

ሩሲያ "የእስላማዊው ሪፐብሊክ ታማኝ አጋር ነች፤ ሁልጊዜም ትሆናለች" ብለዋል።

ክሬምሊን ግን ያ ድጋፍ ምን ምን እንደሚያካትት ወይም ከንግግር በዘለለ የሚሄድ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 15 የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ቴህራን ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ መስክን ጨምሮ "የቅርብ ትብብር" እንዳላት ቢገልጹም፤ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ለመናገር ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቢቢሲ ሞኒተሪንግ በግጭቱ መጀመሪያ ሳምንታት ሞስኮ ለቴህራን በይፋ የሰብዓዊ እርዳታ መስጠቷን ዘግቧል።

በዕለቱ የሩሲያ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር ንብረት የሆነው ኢል-76 የጭነት አውሮፕላን ኢራን ከአዘርባጃን በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ላንካንራን ውስጥ አርፎ 13 ቶን የሕክምና ቁሳቁሶችን ለኢራን ቀይ ጨረቃ ማኅበር አስረክቧል።

በሞስኮ የኢራን አምባሳደር ካዜም ጃላሊ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ስለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበው ተጨማሪ የሩሲያ ሰብዓዊ እርዳታዎች በመንገድ ላይ መሆናቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

ሞስኮ ያላመነችው ድጋፍ የትኛው ነው?

የድሮን ስብርባሪዎች

የፎቶው ባለመብት, SCOTT PETERSON/GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ምዕራባውያን ምንጮች ሩሲያ ለኢራን የድሮን መለዋወጫዎች እና የደኅንነት መረጃዎች ትሰጣለች ሲሉ ይወነጅላሉ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ ለኢራን ያደረገችው ድጋፍ ላይ እርግጠኛ መሆን የማይቻለው ከወታደራዊ እና ደኅንነት ጋር የተያያዙትን ነው።

ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያሉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ "100 ፐርሰንት" እርግጠኛ ነኝ በማለት ሩሲያ ወደ ኢራን ሻሂድ የተባሉትን አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን ልካለች ብለዋል።

እነዚህ ድሮኖች ደግሞ ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ ለማድረግ ትጠቀምባቸዋለች።

ሻሂድ ድሮን በመጀመሪያ የተሠራው በቴህራን ቢሆንም በኋላ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ዲዛይኑን አሳልፋ ሰጥታታለች።

ሩሲያ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምርቱን በማሻሻል ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ውጊያ በስፋት ጥቅም ላይ አውላዋለች።

በምዕራቡ ዓለም እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የደኅንነት ምንጮችን የጠቀሱ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሩሲያ የደኅንነት መረጃዎችን እና የድሮን ባለሙያዎችን ከመገጣጠሚያዎች ጋር ወደ ቴህራን መላኳን ዘግበዋል።

ክሬምሊን የዚህን ውንጀላ ትክክለኛነት ባያረጋግጥም ማስተባበያም አልሰጠም።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሁለት ጊዜ ሩሲያ ለቴህራን ስለምታደርገው የቴክኒክ ድጋፍ ሲጠየቁ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

አክለውም በዚህ ጉዳይ የሚወጡ ዘገባዎች "ረብ የለሽ መረጃዎች ናቸው" ሲሉም አጣጥለዋል።

ክሬምሊን በተመሳሳይ መልኩ ሞጅታባ ኻሜኔን ያሉበትን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱትን ወሬዎችን አጣጥሏል።

'አል ጃሪዳ' የተሰኘው የኩዌት ጋዜጣ ለኻሜኔ ቅርብ የሆኑ ምንጭን ጠቅሶ በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ጉዳት ደርሶባቸው በሞስኮ ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ዘግቧል።

ፔስኮቭ በዚህ ባልተረጋገጠ ዘገባ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህም በበርካታ የክሬምሊን ደጋፊ በሆኑ የበይነ መረብ ሚዲያዎች የኢራን አመራር ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የተነደፈ "የመረጃ ዘመቻ" ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ሩሲያ ለቴህራን የምታደርገው ድጋፍን በሚመለከት በመንግሥት ቴሌቪዥን የሚቀርብ ዘገባም ምሥጢራዊነት የታየበት ነው።

የቴሌቪዥን አቅራቢዋ ኦልጋ ስካቤዬቫ በመንግሥት በሚተዳደረው ሮሲያ 1 ቻናል ባቀረበችው ዘገባ "የኢራን ጥቃቶች ውጤታማነት ከተመለከትን የሆነ አካል በእርግጠኝነት የሆነ ነገር አሳልፎ ሰጥቷል" ብላለች።

ሩሲያ ከዚህ የተሻለ ማድረግ ያልቻለችው ለምንድን ነው?

ሞስኮ ለቴህራን ጎልቶ የሚታይ ድጋፍ ማድረግ ያልቻለችው ከአቅም ውስንነት እንዲሁም ፈቃደኝነት ከማጣት እንደሆነ ማየት ይቻላል።

በዩክሬን ውስጥ ባለው ጦርነት ከመጠን በላይ የተወጠረው ክሬምሊን የትኛውንም ወታደራዊ መሣሪያ ወደ ቴህራን ለመላክ መቸገሩን መመልከት ይቻላል።

ኢራን በ2023 ከሩሲያ ሱ-35 ተዋጊ ጄቶች እና ኤምአይ 28 ሄሊኮፕተሮችን ለመግዛት ስምምነት የፈረመች ሲሆን፣ አገራቱ በየጊዜው ወታደራዊ ትብብራቸው እየጨመረ ሄዶ ነበር።

ነገር ግን መጋቢት 16 'ፎሬይን አፌርስ' መጽሔት ባወጣው ዘገባ መሠረት ቴህራን የጦር ጄቶቹንም ሆነ ሂሊኮፕተሮቹ ተረክባ ስለመሆኑ ግልጽ መረጃ የለም።

ኢራን ለሞስኮ ዘመናዊ ኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።

ነገር ግን መጽሔቱ እንደዘገበው ከሆነ "እነዚህ ሁሉ ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ ለምታካሄደው ጦርነት የምትፈልጋቸው ንብረቶች ናቸው። ሞስኮ እነዚህን ሥርዓቶች ለኢራን ለመስጠት ብትፈልግ እንኳን በፍጥነት ይህን ማድረግ አትችልም።"

በቴህራን ለመንግሥት ያለው የሕዝብ ድጋፍ ውስን መሆን ሩሲያ ከእስራኤል፣ ከባሕረ ሰላጤው አገራት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ዘላቂ ግንኙነትን ለማስጠበቅ ያግዛታል።

ይህም ሩሲያ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚያካሄደው የተራዘመ ድርድር ላይ የሚፈልገውን ውጤት ለማግኘት እንደሚያስችለው ተስፋ ያደርጋል።

ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄደው የተራዘመ ጦርነት የተወሰኑ ጥቅሞችን ለማግኘት ታስባለች።

ቢያንስ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መሄዱ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ለገጠማት ሞስኮ እንደ መልካም ዕድል ይታያል።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት በመርከቦች ላይ የተጫኑ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ እና የነዳጅ ውጤቶች እንዲሸጡ የ30 ቀናት የእፎይታ ጊዜ ፈቅዷል።

ቀደም ሲል ታግዶ የነበረው የሩሲያ ነዳጅ እስከ ሚያዝያ መጀመሪያ ድረስ ርክክብ እና ሽያጭ እንዲደርግበት የአሜሪካ መንግሥት ፈቃድ ሰጥቷል።

የሩሲያ የፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ኪሪል ዲሚትሪቭ ለዚህ ውሳኔ በማኅበራዊ ገጻቸው በሰጡት ምላሽ፤ የሩሲያ ኢነርጂ በዓለም ላይ የተከሰተውን አስከፊ የኃይል አቅርቦት ቀውስ ለማቃለል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት ካስከተለው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጠቃሚ ሆናለች

የፎቶው ባለመብት, BLOOMBERG/GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት ካስከተለው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጠቃሚ ሆናለች

ከዚህም ባሻገር የኢራን ጦርነት ወደ ኪየቭ ሊሄዱ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎች አቅርቦቶችን ይቀይራል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት "ለፑቲን በኢራን ውስጥ የሚካሄድ የተራዘመ ጦርነት ጥቅም ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከነዳጅ ዋጋ መጨመር በተጨማሪ የአሜሪካ ክምችት መሟጠጥ እና የአየር መከላከያ መሣሪያ አምራቾች ክምችት ማሽቆልቆል ማለት ነው። ስለዚህ እኛም [ዩክሬን] የመሣሪያ እጥረት ይገጥመናል።"

እንደ ዩክሬን ፕሬዝዳንት ገለጻ ከሆነ የኢራን ጦርነት በጀመረ ሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በተደረገው የአራት ዓመት ጦርነት ወደ ዩክሬን ከላከቻቸው የፓትሪዮት ሚሳዔሎች በላይ ተጠቅማለች።

ለአሁኑ ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚካሄደው ጦርነት የምትሰተው ምላሽ የተጠናና እና ቁጥብነት የተሞላበት ነው።

ይህም ለቴህራን በምትሰጠው ድጋፍ የአሜሪካን ቀይ መስመር ላለማለፍ ጥንቃቄ ማድረግን እና የአጭር ጊዜ ግቦችን መቃረም ያካትታል።

ሩሲያ እያደረገች ያለችው ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር አሜሪካ እና እስራኤል ለ12 ቀናት ከኢራን ጋር ባካሄዱት ጦርነት ወቅት ከሰጠችው ምላሽ ጋር የሚናበብ ነው።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ ኢራንን ለመርዳት ለምን የበለጠ እየሠራች እንዳልሆነ ተጠይቀው ነበር።

"የበለጠ ሲባል በምን መልኩ?" ሲሉ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ምላሽ ሰጥተዋል።

"ወታደራዊ ዘመቻዎችን እንጀምር? እኛ የቆምንለትን ሀሳብ ከሚቃወሙ ጋር እና በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ ስጋት በሚፈጥሩ ላይ ወታደራዊ ዘመቻዎችን እያደረግን ነው።"

"በመሠረታዊነት እነዚህ ኃይሎች በኢራን እና በሩሲያ ውስጥ ተመሳሳይ ናቸው። እነሱ በስውር፣ ከኋላችን ናቸው። ከጀርባችን ይገኛሉ። ሆኖም ግን ከፊት ለፊት ያሉት እነርሱ አይደሉም።"