የኢራን ሚሳዔሎች ወደ ታላላቆቹ የአውሮፓ ከተሞች ሊደርሱ ይችላሉ?

የኢራን ካርታ፣ ባንዲራ እና ሚሳዔሎችን ያዘ ባነር

የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / AFP via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኢራን በሕንድ ውቅያኖስ ዲያጎ ጋርሲያ ደሴት ላይ ወደሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና የአሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ሰፈር ላይ የረዥም ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል።

በእርግጥ ሚሳዔሎቹ ወደታቀደላቸው ዒላማ ሳይደርሱ ቀርተዋል። ነገር ግን የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እንዲህ ዓይነት የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግሯል።

ቴህራን እስካሁን ድረስ ሚሳዔሎቹን መተኮሷን በይፋ አላረጋገጠችም፤ የኢራን ሚዲያዎችም ቢሆኑ በዘገባዎቻቸው በአብዛኛው የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ብቻ ጠቅሰዋል።

ባለሙያዎች አሁን የከሸፈው ጥቃት እንዲሁም በርቀት ለሚገኙ ዒላማዎች ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጨምሮ የራሳቸውን ትንታኔ እየሰጡ ነው።

በርሊን፣ ፓሪስ እና ለንደንን ጨምሮ የአውሮፓ ዋና ዋና ከተሞች በቴህራን ሚሳዔሎች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ?

የዩኬ የካቢኔ ሚኒስትር የእስራኤሉ መከላከያ እንደሚለው ኢራን ለንደን መድረስ የሚችሉ የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች እንዳሏት "ለማረጋገጥ የሚያስችል ምንም ዓይነት ግምገማ የለም" ብለዋል።

ከኢራን የተተኮሰ ሚሳዔል ከጋዛ ሰርጥ የፍልስጤም ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሲታይ

የፎቶው ባለመብት, Photo by Eyad Baba / AFP via Getty Images

የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ባልደረባ ጎህኔህ ሃቢቢያዛድ "የኢራን የሚሳዔል ፕሮግራም ለረዥም ጊዜ የዓለም አቀፍ ትኩረት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል" ይላል።

"ቴህራን የሚሳዔል ግንባታዋ ሙሉ በሙሉ ለመከላከል እና በብሔራዊ የመከላከያ ስትራቴጂ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ብትናገርም፣ ተቺዎች ግን ረዥም ርቀት የመምዘግዘግ አቅም ያላቸው መሣሪያዎች የአካባቢውን የደኅንነት ሁኔታ ሊለውጥ እንደሚችል ይከራከራሉ።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል እና አሜሪካ በጋራ ኢራን ላይ ጥቃት ሲከፍቱ በቴህራን የኒውክሌር መረሃ ግብር ላይ ያሉ ስጋቶችን ለመፍታት ድርድር እየተደረገ ነበር።

የዲያጎ ጋርሲያ አካል የሆነባቸው የቻጎስ ደሴቶች ከኢራን በግምት 3,800 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛሉ።

ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሲኤንኤን ስማቸውን ያልጠቀሷቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናትን መሠረት አድርገው ሁለት የባለስቲክ ሚሳዔሎች ወደ ደሴቱ መተኮሳቸውን ዘግበዋል።

ነገር ግን ሁለቱም ሚሳዔሎች ዒላማቸው ላይ እንዳልደረሱ ተናግረዋል።

አንደኛው ሚሳኤል በአየር ላይ እየተምዘገዘገ ሳለ መውደቁ ሲገልጽ፣ ሌላኛው ደግሞ በአሜሪካ የጦር መርከብ መክሸፉ ተነግሯል። ቢቢሲ ዘገባዎቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ተረድቷል።

ኢራን ወደ ደሴቲቱ ሚሳዔሎችን ካስወነጨፈች በኋላ ብዙም ሳይቆይ የእስራኤል ጦር አባል በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ በርካታ ከተሞች አሁን ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን እና ባለፈው ዓመት ቴህራን እንዲህ ዓይነት አቅም ያላቸውን ሚሳዔሎች ለማምረት እንዳሰበች መሳወቃቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ዋና አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል ኢያል ዛሚር ወደ ቻጎስ ደሴቶች ሚሳዔል ከተተኮሰ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባስቀመጡት የቪዲዮ መልዕክት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

"ኢራን 4,000 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኝ ዒላማ ሁለት አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች። ሚሳዔሎቹ እስራኤልን ለመምታት የታሰቡ አልነበሩም" ብለዋል። "ሚሳዔሎቹ የሚሸፍኑት ርቀት እስከ የአውሮፓ ዋና ከተሞች ይደርሳል። በርሊን፣ ፓሪስ እና ሮም ሁሉም በቀጥታ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው።"

የቀድሞው የዩኬ ጥምር ጦር አዛዥ ጄኔራል ሰር ሪቻርድ ባሮንን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ባለሙያዎች፤ ይህ ሁሉ የኢራንን የሚሳዔል ክምችት እና ተደራሽነት እንደገና መገምገም እንዳስገደዳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ቀደም ሲል የኢራን ሚሳዔሎች 2,000 ኪ.ሜ ርቀት መወንጨፍ እንደሚችሉ እናስብ ነበር፤ ዲያጎ ጋርሲያ ደግሞ 3,800 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።"

በርካታ የዓለም ዋና ከተሞች ከኢራን በምን ያህል ርቀት እንደሚገኙ የሚያሳይ ካርታ
የምስሉ መግለጫ, በርካታ የዓለም ዋና ከተሞች ከኢራን በምን ያህል ርቀት እንደሚገኙ የሚያሳይ ካርታ

ኢራን እስካሁን ድረስ በባላስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሟ ላይ ራሷ ላይ ገደብ ማስቀመጧን በመግለጽ ወደ 2,000 ኪ.ሜ የሚወነጨፉ ብቻ እንዳላት ተናግራለች። ይህ ማለት እስራኤል በኢራን ሚሳዔሎች ርቀት ውስጥ ስትሆን የአውሮፓ አገራት ግን አይደሉም።

ሟቹ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በ2021 ምንም እንኳ ወታደራዊ መሪዎች እና አብዮታዊ ዘቡ ባይስማማም ይህ ውሳኔ የፖለቲካ ምርጫ እንጂ ሚሳዔሎችን በማምረት ረገድ የአቅም ገደቦች ኖረው አለመሆኑን ተናግረዋል።

በወቅቱ እስራኤልን ማስጠንቀቅ እና አውሮፓን ላለማስደንገጥ መፈለጋቸው መሆኑ ግልጽ ነው።

ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ አንድ የኢራን የፓርላማ አባል ለመንግሥት ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፤ አብዮታዊ ዘቡ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳዔል በተሳካ ሁኔታ መሞከሩን ጠቅሰው ሚሳዔሉ ስለሚሸፍነው ርቀት ግን ሳይገልጹ ቀርተዋል።

የሚሳዔል ርቀት አቅም

እንደ ለንደን ያሉ አውሮፓ ከተሞች በኢራን ሚሳዔሎች ሊደረስባቸው ይችላል የሚለው ላይ ባለሙያዎች የተለያየ አቋም ነው ያላቸው

የፎቶው ባለመብት, Shomos Uddin via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንደ ለንደን ያሉ አውሮፓ ከተሞች በኢራን ሚሳዔሎች ሊደረስባቸው ይችላል የሚለው ላይ ባለሙያዎች የተለያየ አቋም ነው ያላቸው

በተጨማሪም የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኢራን የጠፈር ፕሮግራም አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳዔሎችን እንድትገነባ የሚያስችሏትን ቴክኖሎጂዎችን እንዳዘጋጀ ለረጅም ጊዜ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ይህም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ቴክኖሎጂውን መጠቀም እንደምትችል ያሳያል።

አንዳንድ ተንታኞች በዚህ ይስማማሉ።

በለንደን የሚገኘው የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ካሪን ቮን ሂፔል ለቢቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት "ሚሳኤሎቹ ዲያጎ ጋርሲያ እንደደረሱ በማሰብ...ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ በተግባር ላይ ባይውሉም ኢራናውያን እስከ 10,000 ኪ.ሜ የሚጓዙ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳዔሎችን እያመረቱ ነው" ብለዋል።

ይህ ማለት ከኢራን የሚተኮሱ ሚሳዔሎች አህጉር አቋርጠው አሜሪካ ሊደርሱ ይችላሉ ማለት ነው።

ታዛቢዎች እንደሚሉት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የታሰበው ጥቃት የርቀት ገደቡ መነሳቱን ያሳያል።

የኢራን ሚሳዔል ላይ የሚሳለቁ ምስሎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኢራን ረዥም ርቀት የሚመዘገዘጉ ሚሳዔሎችን ላለማምረት በራሷ ላይ እገዳ አስቀምጣ ነበር። አንዳንዶች ይህ አሁን ተቀይሯል ሲሉ ይሞግታሉ

ነገር ግን አንዳንዶች ሚሳዔሎቹ መጀመሪያ ላይ ባይከሽፉም እንኳ ወደታሰበላቸው ዒላማ መድረስ ይችሉ እንደሆነ አጠራጣሪ ነው ይላሉ።

የዩኬ ሚኒስትር ስቲቭ ሪድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ኢራናውያን ዩኬን ዒላማ እያደረጉ ነው ወይም ይፈልጋሉ ለሚለው ግልጽ የሆነ ግምገማ የለም" ብለዋል።

ዋናው አከራካሪ ጉዳይ ኢራን እንዲህ ያሉ የረዥም ርቀት ጥቃቶችን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ ታጥቃለች ወይ የሚለው ነው።

ይህም ሚሳዔሎችን በእንደዚህ ዓይነት ረዥም ርቀት የመቆጣጠር እና የመምራት ችሎታን ይጨምራል።

እናም በዚህ ውስጥ ግልጽ የሆነ የሥነ ልቦና ገጽታ አለ።

አንዳንዶች ኢራን ዒላማዎቹን ለመምታት አስባ እንዳልሆነ ያምናሉ፤ ይልቁንም ቴህራን ግልጽ የሆነ የማስጠንቀቂያ መልዕክት እያስተላለፈች ነው ብለው ያምናሉ።

በቴል አቪቭ በሚገኘው የብሔራዊ ደኅንነት ጥናት ተቋም ውስጥ የሚሠራው የቀድሞ የእስራኤል ወታደራዊ የስለላ መኮንን ዳኒ ሲትሪኖዊች "ነገ ለንደን ወይም ፓሪስን እንደሚያጠቁ ያስባሉ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ለእነሱ መከላከያውን ለመገንባት የሚያስችላቸው ሌላ አካል ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ለለንደን ጋዜጣ ተናግሯል።

እስራኤል በዚህ ሳምንት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ለተተኮሰው ሚሳዔል የሰጠችው ምላሽ ከጎናችሁ ነኝ፤ አድምጡኝ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።

"እርግጥ ነው እስራኤል ይህንን የምትለው ጦርነቱን በማስፋት ከእራሷ እና ከአሜሪካ ጎን ሌሎች አገራትን ለማሰለፍ ስለምትፈልግ ነው" ሲሉ የአውሮፓ የቀድሞ የኔቶ ምክትል አዛዥ ጄኔራል ሰር ሪቻርድ ሺረፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ይህንን መቃወም አለብን። ይህ የትራምፕ ጦርነት ነው፣ ግልጽ የሆነ መጨረሻ እና ስትራቴጂ የሌለው፣ የበለጠ እየተጠላለፈ የመጣ ነው። የኢራን ኒውክሌር አቅሞቿ እንደወደሙ ከስድስት ወራት በፊት ተነግሮናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከዋሽንግተን የሚመጣ ምንም ነገር ማመን አንችልም።"