ኢራን በ18 ቀናት ውስጥ የትኞቹ ከፍተኛ አመራሮቿ ተገደሉባት?

አሜሪካ እና እስራኤል ከ18 ቀናት በፊት ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ከተነሳበት ዕለት አንስቶ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በርካታ አመራሮቹን አጥቷል። የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቹ የተገደሉበት የኢራን መንግሥት፤ አሁንም ሳይፈረካከስ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠ ቀጥሏል።
እስራኤልም ከመጀመሪያዎቹ የጦርነቱ ቀናት በኋላ ረገብ አድጋ የነበረውን የኢራን ባለሥልጣናት ግድያ በድጋሚ ቀጥላ በአንድ ቀን ልዩነት ውስጥ ሦስት ከፍተኛ የደኅነት ባለሥልጣናትን መግደሏን አስታውቃለች።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምን ያህል የኢራን ባለሥልጣናት ተገደሉ? በቅደም ተከተል እንመልከታቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካቲት 21
በርካታ ኢራን አመራሮች የተገደሉት ጦርነቱ በተጀመረበት ቅዳሜ ዕለት በተፈጸሙ ጥቃቶች ነው። የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በተፈጸሙት ጥቃቶች ከተገደሉት አመራሮች መካከል እነዚህ ይገኙበታል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ - አያቶላህ አሊ ኻሜኒ
የመከላከያ ምክር ቤት ፀሐፊ እና የጠቅላይ መሪው የደኅንነት አማካሪ - አሊ ሻምኻኒ
የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ - ሞሐመድ ፓክፑር
የመከላከያ ሚኒስትር - አዚዝ ናስርዛዴህ
የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም - አብዶልራሂም ሙሳቪ
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ - ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ሺራዚ
የጦር ኃይሎች የስለላ ምክትል ኃላፊ - ብርጋዴር ጄነራል ሳለህ አሳዲ
የጦር ኃይሎች የሎጅስቲክስ እና ድጋፍ ምክትል ኃላፊ - ሜጀር ጄነራል ሞህሴን ዳሬህባጊ
የጠቅላይ አዛዥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ - ብርጋዴር ጄነራል አክባር ኢብራሂምዛዴህ
የጦር ኃይሎች የሎጅስቲክስ መምሪያ ኃላፊ - ብርጋዴር ጄኔራል ሐሰን አሊ ታጂክ

የካቲት 24
የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ያጠናቀረው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ እስራኤል በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የተገደሉትን የመከላከያ ሚኒስትር ተክተው የተሾሙት ሰይድ ማጂድ ኢብን ኢ-ረዛ ኃላፊነቱን በተረከቡ በሁለተኛው ቀን መግደሏን ገልጻለች።
በዚሁ ቀን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ልዩ ኃይል የሆነው ኩድስ ከፍተኛ አባል የሆኑት ረዛ ኻዛኢ በሊባኖስ ዋና ከተማ በቤይሩት ውስጥ በተሰነዘረ ጥቃት መገደላቸውንም እስራኤል አስታውቃለች።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የካቲት 29
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እሁድ የካቲት 29 ባወጣው መረጃ፤ በቤይሩት ሆቴል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ስብሰባ ላይ የነበሩ የአብዮታዊ ዘቡ አምስት አዛዦችን መግደሉን አስታውቋል።
እንደ እስራኤል ጦር ገለጻ፤ ከተገደሉት መካከል የሆኑት አሊሬዛ ቢ-አዛር እና አህመድ ራሱሊ ከፍተኛ የስለላ አመራሮች ናቸው።
"ሊባኖስ ውስጥ ለሚገኙ የኢራን መንግሥት ተቀጽላ ኃይሎች ገንዘብ የማስተላለፍ" ኃላፊነት ነበራቸው ያላቸውን ማጂድ ሀሳኒንም ከተገደሉት መካከል ጠቅሷል። የኩድስ ኃይል አባላት ናቸው የተባሉት ሁሴን አህመድሉ እና አቡ መሐመድ አሊም ተገድለዋል ተብሏል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢራን አምባሳደር በበኩላቸው በቤይሩቱ ራማዳ ሆቴል ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት አራት ዲፕሎማቶች መሆናቸውን በመግለጽ ለተመድ ዋና ፀሐፊ ደብዳቤ መላካቸውን የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
መጋቢት 3
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በዚህ ዕለት ባወጣው መግለጫ ቤይሩት በሚገኘው ሄዝቦህ ውስጥ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሚሳዔል ክፍል የኦፕሬሽን አዛዥ እንደሆኑ የገለጻቸውን አቡ ዳር መሐመዲን መግደሉን አስታውቋል።
ወታደራዊ አዛዡ እስራኤል በመስከረም 2017 ዓ.ም. በፈጸመችው ጥቃት ጉዳት የደረሰበትን "ሄዝቦላህን የሚሳዔል ፕሮግራም መልሶ በማደራጀት ረገድ ቁልፍ ሚና" እንደነበረው ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
መጋቢት 8
እስራኤል ከመጀመሪያው ዙር ጥቃት በኋላ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያለን የኢራን ከፍተኛ የደኅንነት አመራር የገደለችው ትናንት ማክሰኞ ነው። የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
ከዚህ ቀደም ለ12 ዓመታት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሆነው ጭምር ሆነው ያገለገሉት ላሪጃኒ የተገደሉት ከልጃቸው ጋር በተደበቁት አፓርትመንት ላይ በተፈጸመ ጥቃት እንደሆነ ተዘግቧል።
በተጨማሪም 'ባሲጅ' የተባለው የአብዮታዊ ዘቡ ታጣቂ ኃይል አዛዥ የሆኑትን ጎላምሬዛ ሶሌማኒ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል። ኢራን የደኅንነት እና ወታደራዊ አመራሮቹን ግድያ እንደምትበቀል ዝታለች።

የፎቶው ባለመብት, IRNA
መጋቢት 9
እስራኤል ትናንት ምሽት በፈጸመችው ጥቃት የኢራን የደኅንነት ሚኒስትር ኢስማኢል ኻቲብን መግደሏን የመከላከያ ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ በዛሬው ዕለት ተናግረዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ባወጡት መግለጫ "ማክሰኞ ምሽት የኢራን የደኅንነት ሚኒስትር ኻቲባ ተወግዷል" ብለዋል።
ኢራን የስለላ ኃላፊው ስለመገደላቸው እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠችም። የደኅንነት ሚኒስትሩ ኢስማኢል ኻቲብ መገደላቸው ከተረጋገጠ በ24 ሰዓታት ውስጥ በእስራኤል የተገደሉ ሦስተኛው ከፍተኛ የኢራን የደኅንነት ሹም ያደርጋቸዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት የኢራንን ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮችን ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ እየተናገሩ በመሆናቸው የሰለባዎቹ ቁጥር አሁን ባለበት ላይቆም ይችላል።















