ብልጽግና ፓርቲ፤ የአብን እና የኢዜማ አመራሮች በሚወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች ዕጩ አላቀረበም

የፎቶው ባለመብት, MIT/EZEMA/ACTS/EBC
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበባቸው ከ80 በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ የተቃዋሚዎቹ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች የሚወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች እንደሚገኙ ቢቢሲ ተገንዝቧል።
ቢቢሲ የተመለከተው የዕጩዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው የአብን ሊቀ መንበር ዶ/ር በለጠ ሞላ እና የኢዜማ ሊቀመንበር ኢዮብ መሳፍንት ዕጩ ሆነው በቀረቡባቸው ምርጫ ክልሎች ብልጽግና ተወዳዳሪዎችን አላስመዘገበም።
አብን ስድስት የሥራ አስፈጻሚ አባላቱን ለምርጫ ያቀረበ ሲሆን፣ እነዚህ የፓርቲው አመራሮች ለፓርላማ አባልነት በሚወዳደሩባቸው ስፍራዎች ገዢው ፓርቲ አይቀናቀናቸውም።
ግንቦት 2018 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ 10,919 የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ተወዳዳሪዎች በዕጩነት ቀርበዋል።
ብልጽግና ፓርቲ 2,950 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በቀዳሚነት የተቀመጠ ሲሆን ተቃዋሚው ኢዜማ ደግሞ 1,256 ተወዳዳሪዎች በማቅረብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አብን፤ ለዘንድሮው ምርጫ ያቀረበው 70 ዕጩዎችን ነው። ከእነዚህ ውስጥ 16 ያህሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወዳደራሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ግንቦት ላይ ውድድር የሚደረግባቸው አጠቃላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮች ብዛት 3,463 ነው።
ቢቢሲ በተመለከተ የዕጩዎች ዝርዝር መሠረት ገዢው ብልጽግናን ጨምሮ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ለሁሉም አገሪቱ ምክር ቤት መቀመጫዎች መወዳደር የሚያስችል ዕጩ አላቀረበም።
ብልጽግና ፓርቲ፤ 547 መቀመጫዎች ላሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው 466 ዕጩዎችን ብቻ ነው። ይህም ገዢው ፓርቲው በዘንድሮው ምርጫ በ81 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ እንደማይወዳደር ያሳያል።
ፓርቲው በአማራ ክልል ከማይወዳደርባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ለሰባቱ ተቃዋሚው አብን አመራሮች እና አባላቱን ዕጩ አድርጎ ያቀረበባቸው ናቸው።
ከእነዚህ ምርጫ ክልሎች አንዱ፤ የአብን ሊቀመንበር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ውስጥ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር በለጠ ሞላ የሚወዳደሩበት "ራያ ቆቦ" ነው።
ብልጽግና በዚህ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ቢያቀርብም ለተወካዮች ምክር ቤት ግን ተወካዩን አላስመዘገበም።
የአብን ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት መልካሙ ፀጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወዳደሩበት "ላይ ጋይንት 1" ምርጫ ክልልም ብልጽግና ዕጩ አላቀረበም።
ብልጽግና የፓርላማ ዕጩ ያላቀረበበት ሌላኛው ምርጫ ክልል "ኩታበር" ነው። በዚህ ምርጫ ክልል፤ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአብን የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ የሱፍ ኢብራሂም ይወዳደራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopost/Fana/GPAA
የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖስታ የአቅርቦት እና ፋሲሊቲ ቺፍ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ጋሻው መርሻ የሚወዳደሩበት "እስቴ 1" ምርጫ ጣቢያም በተመሳሳይ ብልጽግና ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አላቀረበበትም።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳምጠው ተሰማ እና ማሩ ጃኔ በዕጩነት በተመዘገቡባቸው ቦታዎችም ገዢው ፓርቲ አይወዳደርም።
የቀድሞ የፓርቲው አመራር ጣሂር ኢብራሂምም አብንን ወክለው በቀረቡበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ከብልጽግና ጋር አይፎካከሩም።
ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ከማይወዳደርባቸው ሦስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ በሁለቱ ላይ በዕጩነት የቀረቡት የተቃዋሚው ፖለቲካ ፓርቲ ኢዜማ አመራሮች ናቸው።
ለሰባት ዓመታት ገደማ ፓርቲውን ሲመሩ ከነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የካቲት መጨረሻ ላይ ኃላፊነቱን የተረከቡት ኢዮብ መሳፍን ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት በአዲስ አበባ ከተማ "ምርጫ ክልል 18" ነው። ይህ ምርጫ ክልል ብልጽግና ዕጩ ካላቀረበባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች አንዱ ነው።
የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ንጋቱ ወልዴ የሚወዳደሩት ደግሞ በ"ምርጫ ክልል 23" ሲሆን በዚህም ስፍራ ብልጽግና ዕጩ አላስመዘገበም።
ገዢው ፓርቲ የማይወዳደርበት ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚገኘው በ"ምርጫ ክልል 11" ነው።
በዚህ ምርጫ ክልል ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መካከል "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት"ን ወክለው የቀረቡት የተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አበባው ደሳለው እና የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ አባል የሆኑት ዶ/ር ሰይፈገብርኤል ተሾመ ይገኙበታል።
ብልጽግና ፓርቲ የኢዜማ አመራሮች በሚወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች ዕጩዎችን አለማቅረቡ መጀመሪያ የተዘገበው በበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃኑ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው። ኢዜማ ይህንን ዘገባ በመቃወም ቅሬታ እንዳቀረበ መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።
"ገዢው ፓርቲ ባይኖርም ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውድድር እንደሚኖር" የገለጸው ፓርቲው፤ ዘገባው ብልጽግና የማይወዳደርባቸው ወንበሮች "ለኢዜማ ተብሎ የተለቀቀ ለማስመሰል" የተዘጋጀ ነው በሚል ተችቷል።















