'ንጉሥ አንፈልግም' የሚሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕን የሚቃወሙ ሰልፎች በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች ተካሄዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትራምፕ አስተዳደር ላይ ቅሬታቸውን የሚገልጹ ትላልቅ የተቃውሞዎች ሰልፎች በተለያዩ በአሜሪካ ከተሞች ተካሄዱ።
ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው 'ንጉሥ አንፈልግም' (ኖ ኪንግስ) በሚል መሪ መፈክር ስር በተካሄዱ ሰልፎች ቀደም ሲል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ እያካሄዱ ያሉትን ጦርነት፣ የፌደራል መንግሥቱ የስደተኞች አያያዝ፣ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ የሚከተሏቸው የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመቃወም አደባባይ መውጣታቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።
"ትራምፕ እንደ አምባገነን ሊገዛን ይፈልጋል። ይህ አሜሪካ በመሆኑ ሥልጣኑ የሕዝቡ ነው። ሥልጣኑ የነገሥታት ወይም የቢሊየነሮች ጓደኞቻቸው አይደለም" ብለዋል አዘጋጆቹ።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሰልፎቹን "ከትራምፕ ጋር ችግር ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን የሚያክሙበት መድረክ" ሲሉ ከመጥራት ባለፈ ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጡት "ሰልፉን ለመዘገብ የሚከፈላቸው ጋዜጠኞች ናቸው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜው ዕለት ኒውዮርክን፣ ዋሽንግተን ዲሲን እና ሎስ አንጀለስን ጨምሮ በዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች ሠላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ከሰዓት በኋላ በመሐል ዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል። ተቃዋሚዎቹ በሊንከን መታሰቢያ እና በናሽናል ሞል ተሰባስበዋል።
እንደ ቀደሙት ሰልፎች ሁሉ ተቃዋሚዎች የትራምፕን፣ የምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን እና የሌሎች ባለሥልጣናትን ምሥሎች ይዘው ከሥልጣን እንዲወርዱ እና እንዲታሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜ ዕለት ከተካሄዱት የ'ንጉሥ አንፍለግም' ተቃውሞዎች አንዱ በሚኒሶታ የተካሄደው ሲሆን ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።
በጥር ወር ሬኔ ኒኮል ጉድ እና አሌክስ ፕሬቲ የተባሉ ሁለት የአሜሪካ ዜጎች በፌዴራል የስደተኞች ተቆጣጣሪዎች በከተማዋ ተገድለዋል። ግድያዎቹ በመላ አገሪቱ ቁጣን ከመቀስቀሳቸው በላይ የትራምፕ አስተዳደርን የስደተኞች አያያዝ የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደው ነበር።
ቅዳሜ ዕለት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የበርካታ ባለሥልጣናትን ፎቶግራፍ በመያዝ ሴንት ፖል በሚገኘው የስቴት ካፒቶል ሕንፃ ተሰባስበዋል።
አሜሪካው አቀንቃኝ ብሩስ ስፕሪንግስቲን በመድረኩ ላይ በመገኘት ስትሪትስ ኦፍ ሚኒያፖሊስ (የሚኒያፖሊስ ጎዳናዎች) የተሰኘውን የፀረ-ስደተኞች እንቅስቃሴን የሚቃወመውን ዘፈኑን አቅርቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኒውዮርክ ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማንሃተን አልፈው ታይምስ አደባባይን አጨናንቀውት ነበር። ፖሊስ ሰልፉ እንዲካሄድ በሚል በሰዎች ይጨናነቁ የነበሩ መንገዶችን ዘግቷል።
የኒውዮርክ ፖሊስ መምሪያው በጥቅምት ወር ከአምስቱም የከተማዋ አካባቢዎች ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ተሰብስበው እንደነበር አስታውቋል።
የተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ አንዳንድ ክስተቶችም አጋጥመዋል። በሎስ አንጀለስ ሁለት ሰዎች የፌዴራል ሕግ አስከባሪዎችን በመተናኮላቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአገር ውስጥ ደኅንነት መምሪያ (ዲኤችኤስ) ገልጿል።
መምሪያው በኤክስ ላይ ባወጣው መግለጫ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች በድንጋይ ተመትተው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል። ይህ የተከሰተው "አንድ ሺህ ሰልፈኞች" ብሎ የጠራቸው ሰዎች ፌዴራል ሕንፃን ከበው በወኪሎቹ ላይ ድንጋይ መወርወር ከጀመሩ በኋላ ነው።
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ በሌላው ከተማው ክፍል ተቃዋሚዎች ከፌዴራል እስር ቤት አቅራቢያ እንዲበተኑ የተተሰጣቸውን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው "በርካቶች መታሰራቸውን" ገልጿል።
ተቃዋሚዎች "በሩን እንዳይሰብሩ እና ዕቃዎችን አንዳይወረውሩ" ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ የፌዴራል ባለሥልጣናት በአካባቢው ያለውን ሕዝብ ከቦታው ለማስለቀቅ "ገዳይ ያልሆኑ እርምጃዎችን" እንደተጠቀሙ ፖሊስ አረጋግጧል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ ሠልፉን የሚቃወሙ ሰዎች መንገዶችን በመዝጋት እና 'ንጉሥ አንፈልግም' ሰልፍን ለማስተጓጎል በሚጥሩበት ወቅት "አነስተኛ ግጭቶች" ከተከሰቱ በኋላ በዳላስም እስራቶች ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የብሔራዊ ዘብ (ናሽናል ጋርድ) ቢሰማራም ሠልፎቹ ሰላማዊ እንደነበሩ አዘጋጆቹ ተናግረዋል።
ትራምፕ በ2025 ወደ ዋይት ሃውስ በድጋሚ ከተመለሱ በኋላ የተወሰኑ የፌዴራል መንግሥት ክፍሎችን ለማፍረስ እና ከተለያዩ ግዛቶች የተነሳባቸውን ተቃውሞ ወደ ጎን በማለት የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ወደ አሜሪካ ከተሞች በማሰማራት ፕሬዝዳንታዊ የሥልጣንን ወሰናቸው አስፍተዋል።
የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት የፖለቲካ ባልንጣዎቻቸው ላይ ክስ እንዲመሠርቱ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በችግር ውስጥ ያለችውን አገርን ለማንሳት የሚወስዳቸው እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ከመጥቀስ ባለፈ የአምባገነን ባህሪ እያሳዩ ነው የሚለውን ውድቅ አድርገዋል።
"እኔን እንደ ንጉሥ ነው የሚቆጥሩኝ። ንጉሥ አይደለሁም" ሲሉ በጥቅምት ወር ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ተቺዎች ግን አንዳንድ የአስተዳደሩ እርምጃዎች ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና ለአሜሪካ ዴሞክራሲ ስጋት እንደሆኑ በመግለጽ ያስጠነቅቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተቃዋሚዎች በትላልቅ እና በትናንሽ ከተሞች ተሰብስበው የንጉሥ አንፈልግም የተቃውሞ ሰልፎች በቦስተን፣ ማሳቹሴትስ፣ ናሽቪል፣ ቴነሲ እና ሂዩስተን ቴክሳስ ተካሂደዋል።
ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ባሏቸው እንደ ሼልቢቪል፣ ኬንታኪ እና ሃውል ሚቺጋን ባሉ ከተሞችም ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል።
ተቃዋሚዎቹ የኢራን ጦርነት እና የኢሚግሬሽን እና በጉምሩክ አስከባሪ አካላት (አይስ) ላይ ተቃውሞዋቸውን ገልጸዋል።
በውጭ አገር የሚገኙ አሜሪካውያን ስደተኞችም ለተቃውሞ እየተሳበሰቡ መሆኑ ታውቋል። በፓሪስ፣ ለንደን እና ሊዝበን ወደ አደባባይ በመውጣት ብዙዎቹ ፕሬዝዳንቱን "ፋሺስት" እና "የጦር ወንጀለኛ" ብለው የሚጠሩ ጽሑፎችን ይዘው ታይተዋል። ከሥልጣን እንዲወርዱም ጥሪ አቅርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












