አቅጣጫ በሳተች ጀልባ ላይ ለስድስት ቀናት ከቆዩ ስደተኞች መካከል 22ቱ ሞተው ተገኙ

የባሕር ጠረፍ ጥበቃ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የባሕር ጠረፍ ጥበቃ መርከብ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በትንሽዬ የፕላስቲክ ጀልባ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሲጓዙ የነበሩ 22 ስደተኞች ለስድስት ቀናት ባሕር ላይ ሲንከራተቱ ቆይተው ከግሪክ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ የጠረፍ ጥበቃ አስታወቀ።

አንድ ሕጻን እና ሴቶች የሚገኙባቸው ሌሎች ሃያ ስድስት ስደተኞች ደግሞ በአውሮፓ የድንበር ጠባቂ ኤጀንሲ ጀልባ በሕይወት ተርፈዋል። ከመካከላቸውም ሁለቱ በክሬት ደሴት ላይ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ስደተኞቹን ያሳፈረችው ጀልባ ከምሥራቃዊቷ የሊቢያ ወደብ ቶብሩክ የተነሳችው ባለፈው ቅዳሜ እንደነበረ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ዘግቧል።

በባሕሩ ላይ የነበረው መጥፎ የአየር ሁኔታ፣ የምግብ እና የውሃ ችግር ለስደተኞቹ ሞት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የጠረፍ ጥበቃ ኃይሉ አስታውቋል።

ግሪክ እና ጣልያን በአቅራቢያቸው ከሚገኙት ቱርክ እና ከሰሜን አፍሪካ የሜዲትራኒያን ባሕርን ተሻግረው የሚመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰነድ አልባ ስደተኞችን እየተቀበሉ ነው።

አብዛኞቹ ስደተኞች በሰሜን አፍሪካ አገራት በኩል የሜዲትራኒያን ባሕርን የሚያቋርጡት የአየሩ ሁኔታ ጥሩ ነው በሚባልበት ወቅት ነው።

የግሪክ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል እንዳለው "በጉዞው ላይ በትንሿ ጀልባ ላይ የነበሩት ስደተኞች አቅጣጫቸውን ስተው ካለ ውሃ እና ምግብ ለስድስት ቀናት ባሕር ኃይ ቆይተዋል።"

በመጨረሻም ጀልባዋ ከግሪኳ ክሬት ደሴት በስተደቡብ የባሕር ዳርቻ ላይ ስትቆም ነው በጠረፍ ጥበቃዎች ልትገኝ የቻለችው።

ከዚህች ጀልባ ጉዞ ጋር በተያያዘ ዕድሜያቸው 19 እና 22 የሆኑ ሁለት ደቡብ ሱዳናውያን ወንዶች ሰዎቹን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የግሪክ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

"ወደ አገሪቱ በሕገወጥ መንገድ በመግባት እና በግድየለሽነት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ በማድረግ" የተጠርጠሩ ሁለቱ ሰዎች ላይ በአሁኑ ጊዜ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።

የባሕር ጠረፍ ጥበቃው እንዳለው በሕይወት ከተረፉት መካከል 21 የባንግላዴሽ፣ አራት የደቡብ ሱዳን እና ሌሎቹ ደግሞ የቻድ ዜጎች ናቸው።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ ቢያንስ 41,696 ስደተኞች በባሕር በኩል ተሻግረው ወደ ግሪክ መድረሳቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ዩኤንኤችሲአር ገልጿል። በዚህ ዓመትም በሦስት ወራት ውስጥ ከ4,000 በላይ የሚሆኑ ደርሰዋል።

በቂ ምግብ እና ውሃ እንዲሁም የሕይወት አድን ጃኬት የሌላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ ጀልባዎቹ የተጨናነቁ ናቸው። ጉዞዎቹ የሚደረጉትም በተለይ መጥፎ የአየር ሁኔታ ባለበት ጊዜ መሆኑ የበለጠ አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አሃዝ እንደሚያመለክተው ባለፈው አውሮፓውያን ዓመት ቢያንስ 103 ሰዎች ሞተዋል ወይም የደረሱበት እንደማይታወቅ ይታሰባል።

ባለፈው ታኅሣሥ አንዲት ጀልባ ከክሬታን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ላይ በከፊል በውሃ ተውጣ በተገኘችበት ጊዜ 17 ስደተኞች ሞተው ተገኝተዋል።