የመንግሥታቱ ድርጅት አፍሪካውያን ላይ የደረሰውን ባርነት 'በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል' በማለት ዕውቅና ሰጠ

የባሪያ ንግድን የሚያሳይ ንድፍ

የፎቶው ባለመብት, Universal Images Group via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በባሪያ ንግድ ወቅት ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን የሚገመቱ አፍሪካውያን ተይዘው ወደ አሜሪካ መጋዛቸው ይገመታል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ አትላንቲክን በሚያቋርጠው የባሪያ ንግድ ወቅት አፍሪካውያን ተይዘው መሸጣቸው "በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ እጅግ የከፋ ወንጀል ነው" ሲል ድምጽ ሰጠ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ይህ ውሳኔ ለፍትህ እና የተፈጠረውን ቁስል እንዲሽር መንገድ እንደሚጠርግ ተስፋ አድርጓል።

በጋና የቀረበው ይህ የውሳኔ ሃሳብ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ዕውቅና እንዲሰጥ እንዲሁም አባል አገራት ለፈጸሙት የባሪያ ንግድ ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ለካሳ ፈንድ መዋጮ እንዲያደርጉም ይጠይቃል።

ምክረ ሃሳቡ ለካሳ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ በግልጽ አላስቀመጠም።

የውሳኔ ሃሳቡ ላይ 123 አገራት ድጋፋቸውን ሲሰጡ ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስራኤል እና አርጀንቲና ደግሞ ተቃውመውታል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት አባላትን ጨምሮ 52 አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አገሮች የዛሬዎቹ ተቋማት ከዚህ ቀደም ለተፈጠሩ ስህተቶች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደማይችሉ በመግለጽ የሚቀርብን የካሳ ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች በተለየ መልኩ የጠቅላላ ጉባዔው የሚሰጡ ውሳኔዎች የሕግ ተፈጻሚነት የላቸውም።

ከዚያ ይልቅ ሚዛን የሚደፋ ዓለም አቀፍ አስተያየትን ያመለክታሉ።

"ለታሪክ ተመዝግቦ ይቀመጥ፤ በባሪያ ንግድ ክብራቸውን ለተነፈጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እና አሁንም የዘር መድልዎ እየደረሰባቸው ለሚገኙ ሰዎች ትክክለኛውን ነገር እንዳደረግን ይመዝገብ" ሲሉ የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ ከድምጽ የመስጠት ሂደቱ በፊት ለጉባኤው ንግግር አድርገዋል።

"ይህ የውሳኔ ሃሰብ መጽደቅ እንዳይረሳ ለመጠበቅ እና ለመከላከል ያገለግላል። እንዲሁም ባርነት ያደረሳቸውን ዘላቂ ጠባሳዎች ይገዳደራል" ብለዋል።

ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኦኩዴቶ አብላክዋ ለቢቢሲ የኒውስዴይ ፕሮግራም "ካሳ እየጠየቅን ነው፤ ግልጽ መሆን ያለበት የአፍሪካ መሪዎች ለራሳቸው ገንዘብ እየጠየቁ እንዳልሆነ ነው" ብለዋል።

"ለተጎጂዎች ፍትህ እና ድጋፍ የሚደረግበት ምክንያት እንፈልጋለን፣ የትምህርት እና የኢንዶውመንት፣ የክህሎት ስልጠና ፈንዶች"

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደረጉ የካሳ ጥያቄዎች ከፍተኛ ደጋፊ እያገኙ ነው።

"የካሳ ፍትህ" የአፍሪካ ኅብረት የ2025 ይፋዊ መሪ ቃል ነበር። የኮመንዌልዝ አገራት መሪዎችም እንዲሁ በጉዳዩ ላይ በጋራ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል ።

አብላክዋ በተጨማሪም በውሳኔው ጋና የደረሰባትን በደል ከማንም በላይ አድርጋ እንዳላቀረበች ይልቁንም ታሪካዊ እውነታን ብቻ እየመዘገበች እንደሆነ ተናግረዋል።

ከ1500 እስከ 1800 ባለው ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ከ12-15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተይዘው ወደ አሜሪካ በባርነት ተወስደዋል።

በጉዞው ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል።