የእስራኤል ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ የፍልስጤም መንደሮች ላይ በከፈቱት ጥቃት ነዋሪዎች ሲጎዱ፤ ንብረቶች ተቃጠሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
አክራሪ የአይሁድ ሰፋሪዎች በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ የፍልስጤማውያን መንደሮች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመው ቤቶችን፣ ተሽከርካሪዎችን እና እርሻዎችን አቃጠሉ።
ጥቃቱ የተጀመረው ቅዳሜ ዕለት ብስክሌት እየነዳ የነበረ ይሁዳ ሼርማን የተባለ የ18 ዓመት ወጣት በፍልስጤማዊ ግለሰብ በሚሽከረክረው መኪና ተገጭቶ ከተገደለ በኋላ ነው። ፖሊስ የ18 ዓመቱ ወጣት የተገጨው ሆነ ተብሎ ነው ወይስ በአጋጣሚ የሚለውን ለማረጋገጥ ምርመራ መጀመሩን ተናግሯል።
የወጣቱ ሞት ተከትሎ ሰፋሪዎቹ "የበቀል ዘመቻ" እንዲደረግ በዋትስአፕ ግሩፖቻቸው ጥሪ አቅርበዋል። የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የመከላከያ ባለሥልጣንን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤ በአንድ ምሽት ብቻ ከ20 በላይ ጥቃቶች ሪፖርት ተደርገዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን የጀመሩትን ጦርነት ተከትሎ በሰፋሪዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች መጨመራቸውን እንዲሁም በዚህ ወር ስድስት ፍልስጤማውያን በሰፋሪዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፤ ቅዳሜ ምሽት እስራኤላዊያን "የንብረት ቃጠሎ እንዲሁም በአካባቢው ሁከት መፍጠር ላይ መሳተፋቸውን" የሚገልጽ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ ወታደሮች እና የድንበር ፖሊስ አባላትን ወደ በርካታ የፍልስጤም መንደሮች ማሰማራቱን ገልጿል።
የጥቃት ዒላማ ከሆኑት መንደሮች መከካል ጃሉድ፣ ቃሩት፣ አል ፈንዱ ቅሚያ እና ሲላት አል-ዳህ ይገኙባቸዋል።
ቢቢሲ በተናጥል ማረጋገጥ ያልቻለው እና በይነ መረብ ላይ የተለቀቀ ቪዲዮ፤ አብዛኛው የፊት ጭምብል ያጠለቁ እና ጥቁር ልብስ የለበሱ ከ90 በላይ ሰዎች ወደ ጃሉድ መንደር ሲሮጡ ያሳያል።
ከመንደሩ የወጡ ናቸው የተባሉ ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ በርካታ ተሽከርካሪዎች በእሳት ተያይዘው፣ የሕንጻ መስኮቶች ተሰባብረው እና የአምቡላንስ ድምፅ ሲሰማ አሳይተዋል። አንድ ፎቶ ላይ "ለይሁዳ እንበቀል" የሚሉት ቃላት በአንድ ሕንጻ ላይ ተጽፈው ታይተዋል።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር እንደገለጸው፤ ጃሉድ ውስጥ አጥቂዎችን የተጋፈጡ ቢያንስ ሦስት ፍልስጤማውያን የጭንቅላት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። አንዳንዶቹም ቆስለዋል ተብሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ሰፋሪዎቹ በሚጠቀሙበት የዋትስአፕ ግሩፕ ውስጥ "አይሁዶች ስለፈሰሰው የአይሁድ ደም ዝም አይሉም" የሚል መልዕክት ተላልፎ እንደነበር ዘግበዋል። ሌላኛው ደግሞ "መበቀል እና ጠላትን ከአካባቢው ማባረርን እንፈልጋለን" ይላል።
የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ "ቤቶችን እና ንብረቶችን ማቃጠል፣ ሲቪሎችን ማሸበር እና መግደል፣ በኢድ አልፈጥር ወቅት ወሳኝ መንገዶች፣ መገናኛዎችን እና ዋና ዋና መንገዶችን ዒላማ ማድረግ" እንደተፈጸመ በመግለጽ ጥቃቱን አውግዟል።
የእስራኤል ፖሊስ እሑድ ዕለት በዴር አል-ሃታብ መንደር አቅራቢያ የድንበር ጠባቂዎች አምስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቋል።
በርካታ የእስራኤል ሲቪሎች በኢታማር አቅራቢያ የጸጥታ ኃይሎችን ካጠቁ በኋላ አንድ የፖሊስ መኮንን መቁሰሉን ገልጿል፣ "ለአክራሪ አመፀኛ ግለሰቦች ምንም አይነት ትዕግስት ሳይኖረን እየሠራ ነው" ሲል አክሏል።
የፍልስጤማውያንን መብት ለማስጠበቅ የሚሠራው የእስራኤል የሲቪል መብቶች ቡድን 'የሽ ዲን' ሁኔታዎች "የጭፍጨፋ ምሽት" ሲል ገልጾታል።
"ፖሊስ ሊፈጸሙ ስለታቀዱት ጥቃቶች አስቀድሞ ቢያውቅም መዘጋጀት አልቻለም" ሲል ወቅሷል። ቡድኑ፤ "ጥቃቶቹን ለማስቆም ምንም አይነት የመከላከል እርምጃዎች አልተወሰዱም" በማለትም ተችቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በፍልስጤማውያን ላይ አመፅ በማነሳሳት በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት ማዕቀብ የተጣለባቸው የእስራኤልሉ የቀኝ ዘመም የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በይሁዳ ሼርማን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የአይሁድ ሰፋሪዎች እሑድ ምሽት በወረራ በተያዘው የዌስት ባንክ አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል የኢራን ጦርነት መነሳትን ተከትሎ የተባባሰውን የሰፋወዎች ጥቃት እንድታስቆም የአውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ በዚህ ወር መጀመሪያ ጠይቀዋል።
ከጥር መጀመሪያ አንስቶ ሰባት ፍልስጤማውያን በእስራኤል ሰፋሪዎች፤ 18 ደግሞ በእስራኤል ኃይሎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ የተገደሉት የኢራን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል ኢያል ዛሚር በዌስት ባንክ ሰፋሪዎች የሚፈጽሙት ጥቃት "በሞራልም ሆነ በሥነ ምግባር ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።
እስራኤል በ1967 በተካሄደው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ዌስት ባንክን እና ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ለ700,000 አይሁዶ መኖሪያ የሆኑ 160 ገደማ መንደሮችን ገንብታለች። በአካባቢው 3.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የእስራኤል ሰፈራዎች ሕገ-ወጥ ናቸው።












