በዓለም ላይ ጠንካራ መገበያያ ገንዘቦች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ ጠንካራ ሆኑ?

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ብር ከትይዩ የመገበያያ ገንዘቦች በተለይም ከዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን ክፍት ከደረገች በኋላ የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል።

በምጣኔ ሀብት እና በገንዘብ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ብሉምበርግ ከወራት በፊት ባወጣው ዘገባም በፈረንጆቹ 2025 የኢትዮጵያ ብር በመግዛት አቅማቸው ደካማ ከተባሉ ሦስት የአገራት ገንዘቦች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክቷል።

ለመሆኑ የአገራት የመገበያያ ገንዘብ ደካማ የሚሆነው በምን ምክንያት ነው? በዓለም ላይ ጠንካራ ከሚባሉት የአምስት አገራት ገንዘቦች መካከል ዶላር እንደሌለበት ያውቃሉ? ለመሆኑ ጠንካራ የመገበያያ ገንዘቦች የትኞቹ አገራት ናቸው? ለጥንካሬያቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?

ጠንካራ መገበያያ ገንዘብ የአንድን አገር ምጣኔ ሃብት ጤናማነት ያሳያል። የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጤናማ ብቻ ሳይሆን የተረጋጋ መሆኑንም ይጠቁማል።

ጠንካራ መገበያያ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ገበያ ያለን ተቀባይነት እና ተፈላጊነት ያሳያል።

የአንድን አገር ገንዘብ ጠንካራ የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚለውን ስንመለከት ከፍተኛ የወለድ መጠንን ማንሳት ይቻላል። ከፍተኛ የወለድ መጠን ያላቸው መገበያያ ገንዘቦች ኢንቨስትመንት ይስባሉ።

በተያያዥም አነስተኛ የዋጋ ንረት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የምጣኔ ሃብት ማንሰራራት፣ የብሔራዊ ባንክ ተዓማኒነት የመገበያያ ገንዘብን ጠንካራ ያደርጋሉ።

የዓለም ባንክ አንድን ገንዘብ ጠንካራ መገበያያ ለማለት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የተረጋጋ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ይጠቀሳል።

መልካም አስተዳደር መገበያያን ጠንካራ ከማድረጉም ባሻገር ቀውስ ውስጥ ላለመግባት ይረዳል።

መገበያያ ገንዘብን ጠንካራ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የምጣኔ ሃብት እድገት እና የምጣኔ ሃብት እድገቱ የተረጋጋ መሆን በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ጠንካራ ሲሆን ምጣኔ ሃብት የተረጋጋ እና እያደረገ የመሄድ ተስፋ ያለው መሆኑን ያሳያል።

ሌላው አነስተኛ መጠን ያለው የዋጋ ንረት ነው። ይህም አንድ መገበያያ ገንዘብ በገበያ ላይ ያለው ዋጋ እንዳያሽቆለቁል እና በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥል ያስችላል።

የአንድ አገር የገንዘብ ፖሊሲ በምጣኔ ሃብት እንዲሁም በመገበያያ ገንዘቡ ላይም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

የአንድ አገር የወለድ መጠን ከፍተኛ ሲሆን፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ አስተማማኝ አቋም ላይ ሲገኝ እና ፖሊሲ በአግባቡ ሲተገበር የመገበያያ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል።

በተጨማሪም አንድ አገር ወደሌሎች አገራት የምትልከው እና ከሌሎች አገራት የምታስገባው ተመጣጣኝ እንዲሆን ይፈለጋል።

የአንድ አገር ምርቶች በሌሎች አገራት ተፈላጊነታቸው ሲጨምር የአገሪቱ ገንዘብ በዓለም ገበያ ያለው ዋጋም ከፍ ይላል።

ሌላው የገንዘብን ጥንካሬ የሚወስነው የኢንቨስትመንት ፍላጎት እና ፍሰት መጨመር ነው።

ይህም ከፖለቲካዊ ሁኔታ እና ከተቋማት ብቃት ጋር ሊተሳሰር ይችላል።

መልካም አስተዳደር እና የፖለቲካ መረጋጋት ኢንቨስትመንት ከመሳባቸው ጎን ለጎን የአንድ አገር መገበያያ ጠንካራ እንዲሆን ይረዳሉ።

የፋይናንስ ተቋማት ጥንካሬ እና በሕግ መገዛታቸውም በተያያዥ ሊጠቀስ ይችላል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ሲከሰት ባለ ሃብቶች እንደ ዶላር ወዳሉ እና አስተማማኝ ወደሚባሉ መገበያያዎች ፊታቸውን ያዞራሉ።

ገንዘብ ጠንካራ ነው የሚባለው ሊገበያዩበት የሚፈልጉ ወይም ገንዘቡ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆንም ነው።

ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ባንክ ጠንካራ መገበያያ ገንዘብን እንዴት ይለያል?

የዓለም ባንክ መገበያያን ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር አስተሳስሮ ይመለከታል። የአንድ አገር የፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር እና ሌሎች አገራት የሚፈጠር ቀውስን የመቋቋም ብቃትንም ከግምት ውስጥ ያስገባል።

ዘላቂነት ያለው መረጋጋት ለኢንቨስተሮች መተማመኛ ይሰጣል።

እአአ በ2025 በወጣ አሐዝ መሠረት በዓለም ላይ ባለው ዋጋ የኩዌት ዲናር ጠንካራው ሲሆን የሊባኖስ ፓውንድ ደግሞ ደካማው ነው።

ጠንካራ መገበያያ ተብሎ የሚበየነው ገንዘቡ እንደ ዶላር ካሉ ጠንካራ ገንዘቦች ጋር ካለው የምንዛሬ ተመን ጋር ተወዳድሮ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ የሚሆኑት መገበያያዎች አነስተኛ የሆኑ እና ምጣኔ ሃብታቸው ነዳጅ ላይ የተመሠረት አገራት ገንዘቦች ናቸው።

ምጣኔ ሃብታቸው የተረጋጋ ሲሆን የፋይናንስ ፖሊሲያቸውም ጥብቅ እና አስተማማኝ ነው።

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠንካራ መገበያያዎች የትኞቹ ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ዶላር በዓለም ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ የንግድ ልውውጥ የሚደረግበት ገንዘብ ነው።

በፎርብስ ዝርዝር መሠረት በዓለም ጠንካራ መገበያያ የሚባለው የኩዌት ዲናር ነው።

አንድ የኩዌት ዲናር 3.25 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል። ኩዌት መገበያያዋ ጠንካራ የሆነው በርካታ የነዳጅ ክምችት ስላላት እና ሕዝቡም አነስተኛ በመሆኑ ነው።

አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው አገራት የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከፍተኛ ይሆናል።

የኩዌት ዲናርን ተከትለው ቀጣዮቹ መገበያያዎች በቅደም ተከተል በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፦

የባሕሬን ዲናር- አንድ የባሕሬን ዲናር 2.66 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። ባሕሬን የገልፍ አገራት የምጣኔ ሃብት መዲና እየሆነች ሲሆን፤ ዋነኛ ገቢዋ የነዳጅ ኤክስፖርት ነው።

የኦማን ሪያል- አንድ የኦማን ሪያል 2.60 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። ነዳጅ አምራቿ ኦማን ምጣኔ ሃብቷን የሚደግፉ የተለያዩ ዘርፎች አሏት።

የዮርዳኖስ ዲናር- አንድ የዮርዳኖስ ዲናር 1.41 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። የፖለቲካ መረጋጋት እና ጠንካራ የፋይናንስ ፖሊሲ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የእንግሊዝ ፓውንድ- በተከታታይ ዓመታት ጠንካራ መገበያያዎች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። በዓለም ገበያ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ አንዱ ነው። ከተለያየ የምጣኔ ሃብት ዘርፍ የሚገኘው ገቢ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው።

የጂብላርታር ፓውንድ- እአአ በ1920 ገበያ ላይ የዋለው የጂብላርታር ፓውንድ ከእንግሊዝ ፓውንድ ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ሆኗል። በስፔን ደቡባዊ ግዛት የምትገኘው ጂብላርታር የእንግሊዝ አካል ናት።

የስዊዝ ፍራንክ- ስዊዘርላንድ የተረጋጋች አገር ስለሆነች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ሲከሰት ባለ ሃብቶች ወደ ስዊዝ ፍራንክ ፊታቸውን ያዞራሉ።

የካይማን ደሴቶች ዶላር- በካሪቢያን የሚገኘው የእንግሊዝ ግዛት የሆነው የካይማን ደሴቶች ባለ ሃብቶች ከአገራቸው ውጭ ገንዘብ ለማስቀመጥ ይመርጡታል። እአአ በ1970 ይፋ የተደረገ መገበያያ ነው።

ዩሮ- የአውሮፓ ኅብረት መገበያያ ሲሆን ከ27 አባል አገራት 20ው ይገለገሉበታል።

የአሜሪካ ዶላር- እአአ በ1770 የዓለም ገበያን የተቀላቀለው ዶላር የዓለም ግዙፍ ምጣኔ ሃብት ያላት አገር መገበያያ ነው። በዓለም ከፍተኛ ክምችት ያለው ገንዘብ ሲሆን በብሔራዊ ባንኮች በብዛትም ይገኛል። እንደ ነዳጅ፣ ወርቅ እና መዳብ ሁሉ ተመራጭ መገበያያ ነው።

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መገበያያ ገንዘብ ደካማ የሚሆነው በምን ምክንያት ነው?

የዋጋ ንረት፣ ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እና የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ የአንድን አገር መገበያያ ደካማ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በዓለም አቀፍ ገበያ የአንድ አገር ገንዘብ የሚገዛው የዶላር መጠን ውስን ሲሆን የደካማ መገበያያዎች ዝርዝር ውስጥ ይገባል።

የአንድ አገር ገንዘብ ደካማ ወይም ደግሞ ጠንካራ ነው የሚለው የሚወሰነው በመግዛት አቅሙ ነው።

የመግዛት አቅሙ የሚወሰነው ደግሞ በዋጋ ንረት፣ በወለድ መጠን፣ በውጭ ንግድ፣ በብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ እና በፖለቲካዊ ሁኔታ ነው።

የዋጋ ንረት ሲባባስ የአንድ አገር መገበያያ የመግዛት አቅሙ ዝቅ ይላል። አነስተኛ የወለድ መጠንም የገንዘቡን አቅም ያዳክማል።

የወለድ መጠን ማነስ የኢንቨስተሮችን ገንዘብ የማፍሰስ ፍላጎት ይገድባል።

አንድ አገር ወደ ውጭ የምትልከው እና ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ምርት አለመመጣጠንም የገንዘብን አቅም ያዳክማል።

ደካማ ገንዘብ ያላቸው አገራት የትኞቹ ናቸው?

እአአ በ2025 በወጣው የፍርብስ አሐዝ መሠረት የሊባኖስ ፓውንድ ከዓለም ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ነው። አንድ የሊባኖስ ፓውንድ በ0.000011 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል።

የሊባኖስ ፓውንድን ተከትለው ቀጣዮቹ መገበያያዎች በቅደም ተከተል በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፦

የኢራን ሪያል- አንድ የኢራን ሪያል በ0.000024 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። እአአ በ1700 ገበያውን የተቀላቀለ መገበያያ ነው። ኢራን ነዳጅ እና ጋዝ ላኪ አገር ብትሆንም የምጣኔ ሃብት ማዕቀቦች አሽመድምደዋታል።

የቬትናም ዶንግ- አንድ የቬትናም ዶንግ በ0.000038 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። የቬትናም ዋነኛ ገቢ የአገልግሎት ዘርፍ ነው። አገሪቱ ወደ ውጭ አገራት ምርቶቿን እንዳትልክ የተጣሉ ገደቦች ምጣኔ ሃብቷን ጎድተዋል።

የላዎስ ኪፕ- እአአ በ1950 ገበያውን የተቀላቀለው የላዎስ መገበያያ ደካማ ከሆኑት አንዱ ነው። ቬትናም፣ ታይላንድ፣ ካምቦዲያ እና ቻይና የሚያዋስኗት ባሕር አልባ አገር መዳብ፣ ወርቅ እና ቲምበር በመሸጥ ትታወቃለች።

የኢንዶኔዥያ ሩፒያሕ- አንድ የኢንዶኔዥያ ሩፒያሕ በ0.00006 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። ከአገልግሎት ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ሰፊ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ገቢ እንዲኖራት አድርጓል።

የኡዝቤኪስታን ሶም- የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባሏ ኡዝቤኪስታን ጥጥ አምራች አገር ናት። የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎች ብታደርግም ከፍተኛ የዋጋ ንረት እና ሥራ አጥነት ይፈትናል።

የጋያና ፍራንክ- አንድ የጋያና ፍራንክ በ0.000115 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ቢሮራትም የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ከላይቤሪያ እና ሴራ ሊዮን የተፈናቀሉ ሰዎች የፈጠሩት ምጣኔ ሃብታዊ ጫና ተጽዕኖ አሳድሮባታል።

የብሩንዲ ፍራንክ- ከ14 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አሏት። ቡና እና ሻይ 90% የውጭ ንግዷን ይሸፍናል። ሆኖም ደካማ መገበያያ ካላቸው አገሮች ውስጥ ትመደባለች።

የማዳጋስካር ኤሪያሪ- አንድ የማዳጋስካር ኤሪያሪ በ0.00022 የአሜሪካ ዶላር ይመነዘራል። በማዕድን ቁፋሮ እና በዓሣ ማስገር በዋናነት ትታወቃለች። ቫኒላ፣ ብረት እና ቅሩንፉድ ወደ ውጭ አገራት ትልካለች።

የፓራጉዋይ ጉዋራኒ- እአአ በ1952 ገበያውን የተቀላቀለ መገበያያ ነው። ባሕር አልባዋ ፓራጉዋይ አኩሪ አተር፣ ሥጋ እና በቆሎ በዋናነት ታመርታለች።

የአሜሪካ ዶላር የያዙ እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማይዋዥቀው መገበያያ ገንዘብ

ስዊዘርላንድ እና ሊቨንስቲን የሚገበያዩበት ፍራንክ የማይዋዥቁ ከሚባሉ መገበያያዎች መካከል ይጠቀሳል።

የስዊዘርላንድ ፖለቲካ የተረጋጋ መሆኑ ምጣኔ ሃብቷ አስተማማኝ እንዲሆን አስችሏል።

ስዊዘርላንድ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባው ምርት ይልቅ ወደ ውጭ የምትልከው ይበልጣል። በዚህም ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች።

የአገሪቱ የሃብት ክምችትም ከፍተኛ እና አስተማማኝ ነው።

የአገሪቱ የወርቅ ክምችት 1,039.9 ሜትሪክ ቶን ነው። ይህም በወርቅ ሃብት ሰባተኛዋ አገር ያደርጋታል። ከስዊዘርላንድ የሚበልጡት አገራት ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ ናቸው።