የሚሳዔል ዒላማ የሆኑት ቅንጡ ከተሞች፡ የኢራን ጦርነት በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ምን ለውጥ ያስከትላል?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የባሕረ ሰላጤው አገራት ለረዥም ጊዜ የመረጋጋት እና የቅንጦት ስፍራዎች ተደርገው ነበር የሚታዩት።
ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ኦማን እና ባህሬን ባለሀብቶችን፣ ዋና ዋና ኮርፖሬሽኖችን እና ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞችን በመሳብ ረገድ ወደር አልነበራቸውም።
አውሮፕላን ማረፊያዎቻቸው ወደ ዓለም አቀፍ ማዕከላት፣ ከተሞቻቸው ደግሞ ወደ የፋይናንስ እና የቱሪዝም ማዕከላትነት ተለውጠዋል።
ነገር ግን አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት እና የኢራን አጸፋ ይህንን ምሥል አጠልሽቶታል።
ምክንያቱም በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላትን ዒላማ ያደረጉ የኢራን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች በሲቪል እና በኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
መንግሥታት መደበኛ ኑሮን በፍጥነት በአገራቱ ለመመለስ ሞክረዋል።
ለምሳሌ የኳታር መንግሥት ከቤት መሥራትን ወዲያውኑ አስቁሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቋረጠው ትምህርት ዳግም እንዲጀመር አድርጓል።
ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያዎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ይህንን አስከፊ ሁኔታን መቋቋም ቢችሉም፣ ጦርነቱ ግን አንዳንድ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን መለስ ብለው እንዲቃኙ አስገድዷል ብለው ይከራከራሉ።
"ከኢራን የሚሰነዘረውን ጥቃት ማስቆም አይቻልም፤ ምክንያቱም ከመልክዓ ምድር አንጻር ያለ ቅርበት ነው" ይላሉ በዋሽንግተን የሚገኘው የመካከለኛው ምሥራቅ ኢንስቲትዩት ባልደረባ አሌክስ ቫታንካ።
"እነዚህ አገራት አሁን ቅርቃር ውስጥ ገብተዋል፤ የእነርሱ ባልሆነ ጦርነት ከፊት የተሰለፉ መንግሥታት ሆነዋል፤ ለዚያም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ እየከፈሉ ነው።"
አክለውም "ገንዘባቸውን በሙሉ ለመከላከያ ቢያውሉም፣ ያየነው እነዚህ አገራት ለኢራን በጣም ቀላል ዒላማዎች መሆናቸው ነው፤ የቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንታቸው ጥቂት ሺህ ዶላር ዋጋ ባላቸው የኢራን ድሮኖች አደጋ ላይ ወድቋል" ብለዋል።
ይህ አለመመጣጠን የኢንሹራንስ ወጪን ያንራል፤ የሎጂስቲክስ ጉዳዮችን ያወሳስበዋል፤ እንዲሁም ኩባንያዎች ለባሕረ ሰላጤው ያላቸውን ተጋላጭነት እንደገና እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ቫታንካ ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነጻነትን መጠበቅ
የባሕረ ሰላጤው አገራት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል አስቸጋሪ የሆነ መስመር ሲጓዙ፣ አንዱ አሁናዊ አደጋ ከዋሽንግተን ጋር የደኅንነት ትብብራቸውን ማደስ ነው ሲሉ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኘው የኤምሬትስ ፖሊሲ ማዕከል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤብተሳም አል ኬትቢ ይከራከራሉ።
የባሕረ ሰላጤው አገራት "አሁን በተፈጠሩት የደኅንነት ስጋቶች ምክንያት ያለ ምንም ኮሽታ ወደ አሜሪካ እና ወደ እስራኤል እየተጠጉ ነው" ይላሉ።
ነገር ግን ይህ ትብብር ተግባራዊ እንጂ የርዕዮተ ዓለም እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተዋል። "ወደ ጦርነቱ ዘልቀው እንዳይገቡ፣ ዋና ዒላማዎች እንዳይሆኑ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ነፃነት እንዳያጡ ይጠነቀቃሉ።"
ቫታንካ በተለይም የአሜሪካን ባሕረ ሰላጤ ለመከላከል ፈቃደኛነት በተመለከተ የጠበቀ የደኅንነት ትስስር ገደብ እንዲኖረው ያስጠነቅቃሉ።
የባሕረ ሰላጤው መንግሥታት ከግጭቱ በፊት ዋሽንግተንን ስለ ጦርነቱ ያላቸውን ስጋት ከረጅም ጊዜ በፊት አስጠንቅቀው እንደነበር እና በዚህም ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
"ትራምፕ ለኔታንያሁ ሲሉ ወደ ጦርነት ሲገቡ የባሕረ ሰላጤውን አገራት ችላ ብለዋል" የሚሉት ባለሙያው "እንደ እስራኤል ሊታዩ እንደማይችሉ ያውቃሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
የአሜሪካ የውስጥ ፖለቲካ ዋሽንግተን የባሕረ ሰላጤ አገራትን ለመከላከል ምን ያህል ርቀት እንደምትሄድ እንደሚገድብም በመጥቀስ ይሞግታሉ።
"የአሜሪካ ሕዝብ በባሕረ ሰላጤው ቀጣና ውስጥ ባሉ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በቸልታ ማየት ይፈልጋል?...እንዴት ነው ይህ የሚታየው? ይህ አሜሪካን ታላቅ ከማድረግ እንቅስቃሴ በተቃራኒው የቆመ ነው። [ፕሬዚዳንት ትራምፕ] አሜሪካ በውጭ አገራት ጦርነት የምታደርገው ጣልቃ ገብነት አገሪቱን ያዳክማል የሚል ሃሳብ ነበር የሚያቀነቅኑት።"
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲፕሎማሲ እና መከላከያ
ኢራን በበኩሏ የባሕረ ሰላጤ አገራት በጦርነቱ ውስጥ ገለልተኛነት እንዲሆኑ ጫና እያሳደረች ነው ሲሉ ቫታንካ ይናገራሉ።
"የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል አንዳቸውም አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት አላወገዙም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል…ኢራን 'ከዚህ ውጊያ ራሳችሁን አስወጡ' እያለቻቸው ነው።"
የባሕረ ሰላጤው መንግሥታት "በኢራን ላይ በጣም ተቆጥተዋል" ቢሉም ዋና ዒላማ ከመሆን መቆጠብ እንደሚፈልጉም አልሸሸጉም።
ስልታቸው በአሜሪካ ወይም በእስራኤል እርምጃዎች ላይ በግልጽ ሳይሳተፉ ራሳቸውን መከላከል እንደሆነ ተናግረዋል።
"ኢራን ሰዎች በእነዚህ አገሮች ውስጥ መኖርን አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው እያደረገች ነው። ይህም ለትውልድ የሚቀጥል የኅልውና አደጋ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ተናግረው የኃይል ማመንጫዎች እና የውሃ ው ማጣሪያ ጣቢያዎች ቢመቱ ሊኖረው የሚችለውን አደጋ ጠቅሰዋል።
አሁን በኩዌት ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እና በዩናይትድ ኪንግደም የቻተም ሐውስ የባለሙያዎች ቡድን ባልደረባ የሆኑት የኩዌት የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣን ዶ/ር ባደር ሙሳ አል ሳይፍ የረዥም ጊዜ መፍትሔው በዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ መሆኑንይናገራሉ።
"ከጎረቤቶቻችን ጋር መግባባት አለብን" የሚሉት ምሁሩ "ከኢራን ጋር በቀጥታ መነጋገር አለብን። ቀጣናችንን እንዴት በጋራ መጠቀም እንዳለብን ግልጽ የሆነ ዕቅድ ማውጣት አለብን።"
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምጣኔ ሀብት ጥንካሬ የተፈተነበት
የባሕረ ሰላጤው አገራት ከነዳጅ መር ኢኮኖሚ ወደ ዓለም አቀፍ የአገልግሎት ማዕከልነት ያደረጉት ሽግግር ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት እጅግ አስደናቂ የምጣኔ ሀብት ታሪኮች አንዱ ነው።
ምንም እንኳን ጦርነቱ ይህንን አቅጣጫ ባይቀይርም፣ ተጋላጭነቶችን ግን አሳይቷል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አል ኬትቢ የባሕረ ሰላጤ አገራት "ዋና ዋና ማዕከላት ሆነው እንደሚቀጥሉ" በመግለጽ "ነገር ግን እየጨመሩ የሚሄዱ ወጪዎች ይኖራሉ" ብለዋል።
እነዚሀም የኢንሹራንስ እና የአደጋ ጊዜ ስጋት መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ሽግግሩ ከግል ኩባንያዎች ይልቅ በመንግሥታት ላይ የበለጠ ጥገኛ እንደሚሆን እና ንግዶችም የተለያዩ ስፍራ ከሚገኙ ብዙ ማዕከላት እንደመሥራት ያሉ የመጠባበቂያ ስልቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
አል ኬትቢ ከጊዜ በኋላእነዚህ አገራት ከማን ጋር ንግድ እንደሚያካሂዱ በመወሰን ረገድ ሰፋ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ያምናሉ። ምናልባትም በአሜሪካ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ ላለመሆን ከቻይና እና ከቀጣናዊ አጋሮች ጋር መሥራታቸውን እንደሚያጠናክሩ ያምናሉ።
አል ሳይፍ የቀጣናው የፋይናንስ ጥንካሬ ምንም እንኳን ያለምንም ወጪ ባይሆንም ችግሩን እንደሚያቃልል ይስማማሉ።
"ይህ በአገራዊ የለውጥ ዕቅዳችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል" ሲሉ በኳታር በሚገኘው የራስ ላፋን የጋዝ ማመንጫ ላይ በተፈፀመው የሚሳዔል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን "ጥቂት ዓመታትን" እንደሚፈጅ ይናገራሉ።
አክለውም ጥገና በሚደረግበትም ወቅት በዓመት እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ድረስ እንደሚያስወጣም ገልጸዋል
"ይህ አንድ ትንሽ ምሳሌ ነው… ግን ይህንን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለን ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ፕሮጀክቶቻችንን መቀነስ ሊያስፈልግ ይችላል… ኢንቨስትመንቶቻችንን እንደገና መከለስ ይኖርብናል።"
አል ሳይፍ በጦርነት መካከል ድንገት መገኘታችን "ታይቶ የማይታወቅ ነገር አይደለም" ሲሉ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ኢራቅ ኩዌት ላይ የፈጸመችውን ወረራን እና ተከትሎ የመጣውን የባሕረ ሰላጤው ጦርነትን አስታውሰዋል።
አክለውም "በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሽብርተኝነት ሰለባዎችም ነበርን... እናም ያንን ፈተናም ተቋቁመናል" ብለዋል
በተጨማሪም "በ2010፣ በ2011 መጀመሪያ ላይ የአረብ ተቃውሞዎችን የምታስታውሱ ከሆነ፣ በቀጣናው፣ በባሕረ ሰላጤው ውስጥም ተከስተዋል፣ እኛም ከዚህ ሁኔታ በሚገባ መውጣት ችለናል" ብለዋል።
ወደ የተቀናጀ መከላከያ
የግጭቱ ዘላቂ ውጤት ይበልጥ የተዋሃደ እና በቴክኖሎጂ የዳበረ የባሕረ ሰላጤ የመከላከያ አቋም መገንባት እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አል ኬትቢ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ኔትወርኮችን፣ ድሮኖችን እና የሳይበር አቅሞችን በመጠቀም የሚሳዔል መከላከያዎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
አል ሳይፍ ውህደት ከዚህ በላይ መሄድ እንዳለበት ይከራከራሉ።
"ግዢዎቻችንን ማስተባበር፣ በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ማዕከላዊ የግዥ ሥርዓት መዘርጋት አለብን… በተጨማሪም፣ ለአካባቢው የመከላከያ ምርት ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፤ ይህ ሂደት አቅማችንን የሚያሰፋ ነው" ብለዋል።
ሆኖም ግን የሚኖረው ፉክክር ይህንን ምኞት ሊያጨልመው ይችላል።
ቫታንካ "አንዳንድ የባሕረ ሰላጤው አገራት ከኢራን ጋር ያላቸውን ያህል እርስ በእርሳቸውም ተቀናቃኞች ናቸው" ሲሉ የመከላከያ ትብብር ማድረግ ፖለቲካዊ መሆኑን ይገልጻሉ።
የፎቶው ባለመብት, EPA
ጥንቃቄ ያልተለየው መጻዒ ጊዜ
ባለሙያዎች እንደሚያምኑት የባሕረ ሰላጤው የወደፊት ሁኔታ በኢራን ብቻ ሳይሆን በሰፊው የቀጣናው ተለዋዋጭነት ላይ ጭምር ይወሰናል።
ይህም በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያለውን ውጥረት ይጨምራል።
"ኢራን በቀጣናዊ ሥርዓት ላይ የምትገኝ ብቸኛ አካል ናት ብሎ ማሰብ ስህተት ነው" ሲሉ ቫታንካ ያስጠነቅቃሉ። "እነዚህ አገራት ከአንድነት ይልቅ የመከፋፈል ታሪክ አላቸው።"
ሆኖም ባለሙያዎች እንደሚሉት ባሕረ ሰላጤው በወታደራዊ ፍጥጫ እና ለአደጋ ተጋላጭ በሆነ አካባቢ ውስጥ ቢገኝም ዋና የዓለም አቀፍ ማዕከል ሆኖ ግን ይቀጥላል።
"ወደ ኋላ አይመለሱም፤ ግን እንደገና መልሰው ይጠነክራሉ" ይላሉ አል ኬትቢ። "ባሕረ ሰላጤው የበለጠ ጠንካራ ይሆናል፤ ግን ከጊዜ በኋላ የበለጠ ተጋላጭ እና ወታደራዊ ፍጥጫ የማያጣውም ሆኖ ይቀጥላል" ሲሉ ጨምረው ያስጠነቅቃሉ።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም