እስራኤል ገደልኳቸው ስላለቻቸው የኢራን ባሕር ኃይል አዛዥ ምን ይታወቃል?

የፎቶው ባለመብት, Tehran Times
እስራኤል በሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ ላይ ያለውን አጠቃላይ እገዳ የሚቆጣጠረውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል አዛዥ መግደሏን አስታወቀች።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ እንዳሉት፣ የኢራን የባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑት አሊሬዛ ታንግሲሪ "በቀጥታ የሽብር ተግባር የቦምብ ጥቃት በመፈጸም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በቀጥታ ተጠያቂ ነበር" ብለዋል። አሁን "ተወግዷል" ሲሉም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም በእስራኤል ጥቃት ሌሎች በርካታ "የባሕር ኃይል ዕዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናት" መገደላቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን የባሕር ኃይል አዛዡ መገደልን በተመለከተ እስካሁን ከኢራን በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ከየካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ቴል አቪቭ የኢራን ጠቅላይ መሪን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን እና የደኅንነት ኃላፊውን አሊ ላሪጃኒን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገድላለች።
በኢራን፣ በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በኦማን መካከል የሚገኘው እንዲሁም የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋት፤ የኢራን ወሳኝ የጦርነት ስትራቴጂ ሆኖ ቆይቷል።
ጦርነቱ በጀመረ በሦስተኛው ሳምንት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ግዙፍ መርከቦች እንቅስቃሴ በ95 በመቶ አሽቆልቁሏል።
በዚህም ምክንያት በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ከማሻቀብ አልፎ በበርካታ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ነዳጅ አቅርቦት እጥረት አጋጥሟል።
እስራኤል ለሆርሙዝ መዘጋት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸው እና በፈጸመችው ጥቃት መገደላቸውን ያሳወቀችው የኢራን ባሕር ኃይል አዛዥ ታንግሲሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ይህንን የሚያንጸባርቅ ሃሳብ በተደጋጋሚ አስፍረው ነበር።
"በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም መርከብ በሆርሙዝ በኩል የማለፍ መብት የለውም" በማለት ጽፈው ነበር። በአሜሪካ፣ በእስራኤል እና በወዳጆቻቸው መርኮቦች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸምም ሲያስጠነቅቁ ነበር ተብሏል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑት አሊሬዛ ታንግሲሪ የባሕር ኃይሎ አዛዥ ሆነው የተሾሙት ከስምንት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ለአስር ዓመታትም የባሕር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ነበሩ።
በአውሮፓውያኑ 2019 ኢራን ከሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የአሜሪካንን የቅኝት ድሮን መትታ ከጣለች በኋላ ከሌሎች የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ አብዮታዊ ዘብ አዛዦች ጋር በአንድ ላይ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የኢራን ባሕር ኃይል አዛዥ መገደላቸውን በማረጋገጥ "የብዙ ሰዎች ደም በእጁ ላይ ያለ ሰው ነበረ" በማለት ከስሰዋቸዋል።
በአዛዡ ላይ የተፈጸመው ግድያም አሜሪካ እና እስራኤል በሚካሄደው ጦርነት ዓላማቸውን ለማሳካት ያላቸውን ትበብር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው በማለት ጥቃቱ ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት መፈጸሙን አመልክተዋል።
ከኢራን ባሕር ኃይል አዛዥ በተጨማሪ የባሕር ኃይሉ የደኅንነት መረጃ ኃላፊ ቤህናም ሬዛኢ መገደላቸውንም የእስራኤል ጦር ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ኤክስ ላይ ባሰራጨው መልዕክት አስታውቋል።
















