በኒው ዮርክ የፍልስጤም ደጋፊ አክቲቪስት ቤትን ለማፈንዳት አቅዶ ነበር የተባለ ግሰለብ ተያዘ

አክቲቪስት ነርዲን ኪስዋኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በኒው ዮርክ ከተማ በምትኖር የፍልስጤም ደጋፊ አክቲቪስት ላይ "የኃይል ጥቃት" ሊያደርስ አቅዷል በሚል አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ።

የ26 ዓመቱ ወጣት በቁጥጥር ስር የዋለው፤ ነዋሪነቷ በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ከተማ በሆነችው የፍልስጤም ደጋፊ አክቲቪስት ላይ "የኃይል ጥቃት" ሊያደርስ አቅዷል በሚል እንደሆነ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

አክቲቪስት ነርዲን ኪስዋኒ በኤክስ ገጿ ላይ ባወጣችው መግለጫ፤ የፌደራል ባለሥልጣናት "በሕይወቷ ላይ የተሸረበ ሴራ" ሊፈጸም እንደነበረ ሐሙስ ዕለት እንደገለጹላት አስታውቃለች።

ባለሥልጣናቱ እንደሚናገሩት፤ አሌክሳንደር ሄፍለር የተባለው ይህ ግለሰብ ኒው ጀርዚ ውስጥ በቁጥጥር የዋለ ሲሆን ሕገ ወጥ አውዳሚ መሣሪያዎችን በመያዝ እና በመስራት ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

የጸጥታ አካላት ኒው ጀርዚ በሚገኘው የግለሰቡ ቤት ውስጥ ስምንት የሞልቶቭ ኮክቴል ቦንቦችን እንዳገኙ የፍርድ ቤት ሰነዶች አሳይተዋል። ሞልቶቭ ኮክቴል፤ ተቀጣጣይ ፈሳሽ በያዘ ጠርሙስ ውስጥ ጨርቅ በማስገባ እና በእሳት በማያያዝ ጥቅም ላይ የሚውል የአመጻ መሣሪያ ነው።

የክስ መዝገቡ ግለሰቡ ድርጊቱን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው አይገልጽም። ፖሊስ አሜሪካዊውን ሄፍለር የገለጸው "በኒውዮርክ ፖሊስ የወንጀል ታሪክ የሌለው አክራሪ" በሚል እንደሆነ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

ፖሊስ፤ ግለሰቡ የጥቃት እቅዱን ያዘጋጀው ብቻውን እንጂ ውጭ ካለው የሽብር ቡድን ወይም የውጭ መንግሥት ጋር ነው ብሎ እንደማያምን ገልጿል።

የኒውዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄሲካ ቲሽ በሰጡት መግለጫ፤ "ይህ የኒውዮርክ ፖሊስ ምርመራ አሌክሳንደር ሄፍለር በነርዲን ኪስዋኒ ላይ የኃይል ጥቃት ለመፈጸም ተወጥኖ የነበረውን እቅድ አጋልጧል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፖሊስ እንደሚናገረው ሊፈጸም የነበረው እቅድ መዘጋጀት የጀመረው ባለፈው ወር መጀመሪያ ነው። በወቅቱ ሄፍለር በሽፋን የሚሰራ የጸጥታ አካል በተሳተፈበት "የራስን የመከላከል" ቡድን ቪዲዮ ጥሪ ላይ ተገኝቶ ነበር።

በቪዲዮ ጥሪው ወቅት ሄፍለር "ሞልቶቭ" ቦንቦችን ሊጥል የሚችልበት ቦታዎችን የሚያውቅ ሰው በግሩፑ ውስጥ ይኖር እንደሆን ጠይቋል። ኋላ ላይም የአክቲቪስቷ ኪስዋኒን ቤት ለመዝረፍ ስለያዘው እቅድ እንደተወያየ የፍርድ ቤት ሰነዶች ያሳያሉ።

ሄፍለር በቪድዮ ጥሪው ላእ ከነበረው በሽፋን ስር የሚሰራው የጸጥታ አካል ጋር በአካል ተገናኝተዋል። ሲገናኙ የኪስዋኒን መኖሪያ አድራሻ ይዞ እንደነበነር እና ከጸጥታ አካሉ ጋር ወደ ቤቷ አካበቢ አምርተው ቅኝት እንዳደረጉ ተገልጿል።

በወቅቱ ሞልቶቭ ኮክቴሎችን ለመስራት ከባድ እንዳልሆነ ተናግሯል የተባለው ሄፍለር፤ ከአገር ለማምለጥ እቅድ እንዳዘጋጀም እንደገለጸ ተነግሯል።

በተያዘው እቅድ መሠረት ሐሙስ ዕለት ሄፍለር ከኪስዋኒ ቤት አቅራቢያ ከጸጥታ አካሉ ጋር ተገናኝተዋል። በትልቅ ጠርሙስ ውስጥ ያለ አልኮል እንዲሁም ሞልቶቭ ኮክቴል ለመስራት የሚሆኑ ሌሎች ቁሶችንም ይዞ እንደነበር ተገልጿል።

እነዚህን ቁሶች መኪናዎች እና ቀጥታ የኪስዋኒ መኖሪያ ላይ ለመወርወር አቅዶ እንደነበርም የክስ መዝገቡ ያሳያል።

ሄፍለር በስፍራው ከተገኘ በኋላ የጸጥታ አካላት የሄፍለር ቤት ላይ የብርበራ ትዕዛዝ እንዳወጡ እና በፍተሻውም ስምንት ሞልቶቭ ኮክቴሎችን እንዳፈኙ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

'ዊዝኢን አወር ላይፍታይም' የተሰኘው በኒው ዮርክ የሚገኝ የፍልስጤም ደጋፊ ድርጅት መስራች የሆነችው ኪስዋኒ፤ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ሕይወቷ ላይ ስለተቃጣው አደጋ እንደተገለጸላት የከተማዋ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ በበኩላቸው፤ ሄፍለር ኤፍቢአይ 'በአመጻ ድርጊት የሚታወቅ ጽንፈኛ' ብሎ የፈረጀው 'ጁዊሽ ዲፌንስ ሊግ' አባል ነው በማለት ተናግረዋል።

ከንቲባው "የነርዲን ኪስዋኒን ቤት በአስፈሪ የፖለቲካዊ ጥቃት እና ግልጽ የግድያ ሴራ ለማፈንዳት ተሞክሯል" ብለዋል።

አክቲቪስቷ ኪስዋኒ እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች ላይ የፈጸመችውን ወረራ በይፋ በመቃወም ትታወቃለች። የቀኝ አክራሪ ቡድኖች በእሷ እና ሌሎች አክቲቪስቶች ላይ "የክትትል፣ ጥቃት፣ ማስፈራራት እና የሲቪል መብት ጥሰት ዘመቻ" እንደከፈቱ ትናገራለች።