በኢራን የሚደገፉ መረጃ መንታፊዎች የኤፍቢአይ ዳይሬክተር የግል ኢሜሎችን መጥለፋቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል የግል የኢሜይል አካውንት ከኢራን ጋር ግንኙነት ባለው ቡድን ተጠልፎ መቆየቱን ኤጀንሲው አረጋገጠ።
'ሃንዳላ ሃክ ቲም' በመባል የሚታወቀው ቡድን አርብ ዕለት በድረገጹ ላይ "ይህ ገና የመጀመርያችን ነው" ከሚል መልዕክት ጋር የፓቴልን ሲቪ እና ፎቶዎች አጋርቷል።
ኤፍቢአይ የፓቴልን የኢሜል መረጃ ዒላማ ያደረጉ "በክፋት የተነሳሱ ቡድኖች" እንዳሉ እንደሚያውቅ ተናግሯል። "ተሰርቋል የተባለው ሰነድ በባሕሪው የቆየ ሲሆን የመንግሥትን መረጃ አያካትትም" ሲልም ጨምሮ ገልጿል።
ኤጀንሲው የሃንዳላ ቡድን አባላት ማን መሆናቸውን የሚገልጽ መረጃ ለሚሰጥ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸልም አስታውቋል።
እአአ በ2024 ፓቴል የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው ሳምንታት አስቀድሞም በኢራን የሚደገፉ የመረጃ መንታፊዎች የግል የኢሜል ልውውጦችቻቸውን ሰርቀው ነበር።
የሃንዳላ ቡድን አርብ ዕለት መንትፌዋለሁ ያለው መረጃ፤ በ2024 ከተሰረቀው የተለየ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።
ሃንዳላ ከፓቴል የኢሜይል አካውንት እንደወሰዳቸው የተገለጹ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቡድኑ አርማ ተደርጎባቸው እየተዘዋወሩ ነው።
ፎቶዎቹ ፓቴል የት እንደሆኑ በማይታወቁ በተለያዩ ስፍራዎች የተነሷቸው ናቸው።
ቢቢሲ ሾልከው የወጡትን እነዚህን ሰነዶች በራሱ አላረጋገጠም።
የሃልሲዮን ራንሰምዌር የምርምር ማዕከል ምክትል ፕሬዝዳንት ሲንቲያ ኬይሰር ለቢቢሲ እንደተናገሩት አርብ ዕለት የተለቀቁት ኢሜሎች እስካሁን ከታዩት ሁሉ የተለዩ ናቸው።
"ኢሜሎቹ በጣም የቆዩ ይመስላሉ፤ ይህም ምናልባት በሌሎች ቡድኖች ከዚህ በፊት የተሰረቁ እና አሁን እንደገና ጥቅም ላይ የዋለ ይመስለኛል" ሲሉ በኤፍቢአይ የወንጀል፣ የሳይበር፣ የምላሽ አሰጣጥ እና የአገልግሎት ቅርንጫፍ ውስጥ የሠሩት ካይዘር ተናግረዋል።
የሃንዳላ ቡድን ባወጣው መግለጫ "የኤፍቢአይ 'የማይደረስባቸው' የተባሉት ስርዓቶች በቡድናችን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተንፍረክርከዋል። የአሜሪካ መንግሥት የሚኩራራበት ደህንነት ይህ ነው?! ይህ ዛቻዎች እና ጉቦዎች የተቃውሞ ድምጾችን ሊያደናቅፉ ይችላሉ ብሎ የሚያስብ የሳይበር ግዙፍ አካል ነው?!"
ባለሙያዎች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነቱ የመረጃ ምንተፋ በአንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ላይ ለመፈጸም ብዙ ውስብስብ ነገሮችን የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል።
"የግል አካውንቶች ከመንግሥት ስርዓቶች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጥበቃ እና የማስጠንቀቂያ ደረጃ የላቸውም፤ ስለዚህ እነዚህ ብዙውን ጊዜ ለመረጃ መንታፊዎች ማራኪ ዒላማ ናቸው" ሲሉ በዊስኮንሲን-ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ የብሔራዊ ደህንነት ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ዴቭ ሽሮደር ተናግረዋል።
"ሃንዳላ ይህንን ዓይነት ዕድሎችን ለማግኘት ያለማቋረጥ ይሞክራል፤ ምክንያቱም የታዋቂ ሰዎችን እና ድርጅቶችን መረጃ መጥለፍ ፍላጎታቸውን ስለሚያሟላ ነው" ሲሉ ሽሮደር አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የመረጃ መንታፊዎች ድረገጾች በቁጥጥር ስር አውሏል።
የኢራን የስለላ እና የደህንነት ሚኒስቴር የሃንዳላ ድረ ገጾችን በመጠቀም "የሽብር ፕሮፓጋንዳ" ያሰራጫል፤ "የአገዛዙን ተቃዋሚዎች ዒላማ ለማድረግ የሥነ ልቦና ዘመቻዎችን ይከፍታል።"
ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞችን እና ተቃዋሚዎችን እንዲገደሉ ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር ቢሮው አስታውቋል።
የፓቴልን መረጃ ለመጥለፍ ያገለገለው ድረገጽ የተመዘገበው የፍትህ ቢሮ ከቡድኑ ጋር የተያያዙትን አራት ድረገጾች መያዙን ይፋ ባደረገበት ቀን መሆኑን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ሃንዳላ የፓቴልን የኢሜይል አካውንት የጠለፈው ኤፍቢአይ ድረ ገጾቹን በቁጥጥር ስር በማዋሉ እና ከእነርሱ ጋር የተያያዘ መረጃ ለሚሰጡ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በማቅረቡ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ነው።
በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የሃንዳላ ቡድን በአሜሪካ የሕክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ስትሪከር ላይ ለደረሰው የሳይበር ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።















