በቱርክ ኢስታንቡል የእስራኤል ቆንስላ አካባቢ "ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው" ተገደሉ
በቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
በተኩሱ ሁለት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
መገናኛ ብዙኃኑ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች “እርምጃ ተወስዶባቸዋል’ ያሉ ሲሆን ቢያንስ ሁለቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።
የቱርክ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በፖሊስ ጋር ተኩስ የከፈቱት ሦስት ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢስታንቡል አስተዳዳሪ ከአጥቂዎቹ ውስጥ አንዱ መገደሉን እና ሁለቱ ላይ ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ለሲኤንኤን ተርክ ተናግረዋል።
"በፖሊስ ኃይላችን ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ሁለቱ ፖሊሶቻችን ቆስለዋል። ከአሸባሪዎች ውስጥ አንዱ ተገድሏል። ሁለቱ ደግሞ በተወሰደባቸው እርምጃ ቆስለዋል" ያሉት ገዢው ጥቃቱ ትልቅ ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አነስተኛ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
በቱርክ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የእስራኤል ዲፕሎማት አለመኖሩን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።
የእስራኤል ኤምባሲ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኝ ሲሆን በኢስታንቡል ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ነው።
የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር በቆንስላው አካባቢ ስለተከፈተው ተኩስ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
በርካታ የፖሊስ አባላት በቆንስላው አካባቢ ታይተዋል። ቆንስላው የሚገኘው በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል ሰሜናዊ ክፍል ነው።
ጥቃቱ የተፈጸመው በቀጣናው እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ውጥረቶች በተባባሱበት ወቅት ነው።