ትራምፕ ኢራን ከስምምነት ላይ ካልደረሰች "በአንድ ምሽት" እንደሚያጠፏት ዛቱ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የዓለማችን ወሳኝ የሆነው የነዳጅ መተላለፊያን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ባስቀመጡት ቀነ ገደብ የማትስማማ ከሆነ "በአንድ ሌሊት" እንደሚያጠፏት አስጠንነቀቁ።

ትራምፕ በባህረ ሰላጤው ውስጥ የኃይል ፍሰትን የሚያካትት "ተቀባይነት ያለው" ስምምነት በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር እስከ ማክሰኞ 20:00 (ረቡዕ ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ) አስቀምጠዋል።

ትራምፕ በዋይት ሐውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በኢራን ውስጥ "ምክንያታዊ" መሪዎች "በቀና ልቡና" እየተደራደሩ እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል፤ ነገር ግን ውጤቱ እስካሁን ድረስ ምን እንደሆነ አልታወቀም።

ኢራን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የቀረቡ ሀሳቦችን ውድቅ አድርጋ፤ በምትኩ ግጭቱ በቋሚነት እንዲቆም እና ማዕቀቦች እንዲነሳ ጥሪ አቅርባለች።

ትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ከአሜሪካ ጦር ኃይል የጋራ ዕዝ ሊቀ መንበር ጄኔራል ዳን ኬይን፣ እና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ጋር ነው።

ባለሥልጣናቱ መግለጫውን የሰጡት የአሜሪካ ጦር በደቡባዊ ኢራን የተከሰከሰው ኤፍ-15 ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ እና የመሣሪያ ስርዓት ባለሙያን በተሳካ ሁኔታ ማዳን ከቻለ ጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

የትራምፕ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የበረራ አባላቱን ለማዳን የተደረገውን "ጀግንነት" ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ማክሰኞ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደገና ካልተከፈተ አሜሪካ በኢራን የኃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።

"መላው አገሪቱ በአንድ ሌሊት ሊጠፋ ይችላል፤ ያ ምሽት ደግሞ ነገ ማታ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

የጊዜ ገደቡ ካለፈ በኋላ ኢራን ወደ "ድንጋይ ዘመን" ትመለሳለች ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።

"ድልድይ አይኖራቸውም" ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ምንም አይነት የኃይል ማመንጫ አይኖራቸውም" ሲሉም ዝተዋል።

ኢራን ቀደም ሲል የአሜሪካን ጥያቄዎች ውድቅ ብታደርግም፣ ትራምፕ በተከታታይ የኢራን መሪዎች በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃቶች ከተገደሉ በኋላ ቴህራን በቅን ልቦና እየተደራደረች እንደሆነ ያላቸውን ተስፋ መናገራቸውን ቀጥለዋል።

"የሚሆነውን እናያለን" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

እየተካሄ ስላለው ውይይት መረጃ ያላቸው አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን በማንኛውም ድርድር ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ያለተኩስ አቁም ስምምነት ሊከናወን የሚችልበት ዕድል አነስተኛ ነው ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሥልጣኑ የሚደረጉት ንግግሮች ውስብስብ የሆኑት የኮሙኒኬሽን መቋረጥ በመኖሩ ከኢራን ባለሥልጣናት መልዕክቶችን ለማድረስም ሆነ ለመቀበል አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ብለዋል።

"ለኢራን መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እና ምላሽ በሚፈለገው ጊዜ ማግኘት አይቻልም" ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል። "አማካይ ምላሽ የማግኛው ጊዜ አንድ ቀን ወይም ከዚያ በላይ ነው።"

ፓኪስታን፣ ቱርክ እና ግብፅ ሁሉም አሜሪካ እና ኢራንን ለማደራደር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሳትፈዋል።

ትራምፕ ስለ አስተዳደሩ የወደፊት ዕቅዶች ሌሎች ዝርዝር ነጥቦችን መናገር አልፈቀዱም። "ምርጥ ዕቅድ" እንዳላቸው ነገር ግን ለመገናኛ ብዙኃን እንደማያሳውቁ ተናግረዋል።

የሕግ ባለሙያዎች በኢራን መሠረተ ልማት ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

"ሁሉንም የኃይል ማመንጫዎች ማውደም፣ መንግሥትን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት በሚል በሲቪሎች ላይ የኃይል እርምጃዎችን ለመውሰድ ማስፈራራት፣ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ሕገወጥ ናቸው" ሲሉ በኦባማ የሥልጣን ዘመን የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሕግ አማካሪ የነበሩት ቴስ ብሪጅማን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ትራምፕ ይህ "እንደማያሳስባቸው" ተናግረው የኢራን ሕዝብ "ነፃነትን ለማግኘት መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በግጭቱ ወቅት ለአሜሪካ ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም ያሏቸውን ቁልፍ አጋሮቻቸውን ዩኬ፣ ኔቶ እና ደቡብ ኮሪያ ላይ ዳግም ትችት ሰንዝረዋል።

"ይህ በኔቶ ላይ ፈጽሞ የማይጠፋ ምልክት ነው" ሲሉ አሜሪካ ዩኬን "እንደማትፈልግ" ተናግረዋል።

አሜሪካ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በኢራን ከ13,000 በላይ ጥቃቶችን መፈጸሟን ሰኞ ዕለት ከአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ኮማንድ የወጣ መረጃ አመልክቷል።