ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምድራችን ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እያመራች ነው? ወይስ የተጋነነ ስጋት ነው?
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ወደ ሁለተኛ ወር እየገሰገሰ ይመስላል። መካከለኛው ምሥራቅን ያዳረሰው ጦርነት ከቀጣናውም ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል።
ጦርነቱ የጎዳው ኢራንን ብቻ አይደለም። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራቅ፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኦማን፣ አዘርባጃን፣ በወረራ ሥር ያለው ዌስት ባንክ፣ ቆጵሮስ፣ ሶሪያ፣ ኳታር እና ሊባኖስ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
ጦርነቱ ከቀጣናው ተሻግሮ ዓለምን የሚያዳርስ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት የተስተጋባውም ለዚህ ነው።
የዓለም ጦርነት የሚባለው ምን ዓይነት ጦርነት ነው?
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ማርጋሬት ማክሚላን "ብዙዎች ጦርነት በአግባቡ ተወጥኖ የሚካሄድ እንደሆነ እና የጦርነቱ ተሳታፊዎችም አውቀው እንደሚገቡበት ያስባሉ" ይላሉ።
ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ጦርነቶች በመነሳት ግን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትን ሲገልጹ "በድንገት ተነስቶ፣ ተዋጊዎችም የተቀናቃኞቻቸውን አቅም ሳይገነዘቡ ገቡበት" ይላሉ።
"በትምህርት ቤት እንደሚካሄድ ድብድብ ልናየው እንችላለን" ሲሉ ያስረዳሉ።
የኦስትሮ-ሀንጋሪያዊው ንጉሥ ፍራንዝ ጆሴፍ ወንድም ልጅ መገደል በአውሮፓውያኑ 1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት እንዲነሳ አድርጓል።
በሳምንታት ውስጥ የአውሮፓ አጋር ኃይሎች ጦርነቱን ተቀላቀሉ። ኦስትሪያ እና ሀንጋሪ፤ ሰርቢያ ላይ ተነሱ። ጀርመን ኦስትሪያን ስትደግፍ ሩሲያ ሰርቢያን አገዘች።
ፈረንሳይ ሰርቢያን ለማገድ ሩሲያን ትትደግፍ ጀመር። ብሪታኒያ ለክብር እና ለዝናዋ ስትል ጦርነቱን ተቀላቀለች።
ጦርነቱ የመላው ዓለም የሆነው በዚህ መንገድ ነበር።
በኪንግስ ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ታሪክ ፕሮፌሰር ጆ ማይሎ እንደሚሉት የዓለም ጦርነት የሚባለው ኃያላን አገራትን ያሳተፈ ውጊያ ሲካሄድ ነው።
"በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የአውሮፓ ኃያላን አገራት ተዋግተዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ፣ ጃፓን እና ቻይና ገብተውበታል" ይላሉ።
ብዙዎች የኢራንን ጦርነት የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ብለው ነው የሚጠሩት።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሦስተኛው የዓለም ጦርነትን ጀምረዋል ብለዋል። ሞስኮ ላይ የምጣኔ ሃብት እና ወታደራዊ ጫና መደረግ አለበት ብለውም ያምናሉ።
"ፑቲን ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ጀምሮታል ብዬ አምናለሁ። ጥያቄው ምን ያህል ግዛት ይቆጣጠራል? ማንስ ያስቆመዋል? ነው" ብለዋል።
ሩሲያ አዲስ ዘይቤን ዓለም ላይ መጫን እንደምትፈልግ እና ይህም የሰዎችን ፈቃድ እንደሚጋፋ ገልጸዋል።
ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የመግባት ስጋት አለ?
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ማርጋሬት ማክሚላን እንደሚናገሩት ኢራን እና የየመን ሁቲ አማጺያን አጋሮቿ ጦርነቱን ሊያስፋፉ አይችሉም።
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን በመዝጋት ዓለም አቀፍ ጫና ማሳደር ትሻለች። በርካታ አገራት የኢነርጂ አቅርቦት መስተጓጎል እየፈተናቸው ይገኛል።
አሜሪካ በጦርነቱ መሳተፏ ቀውሱን ያባብሰዋል። ሌሎች አገራት በቀጥታ በጦርነቱ ባይሳተፉም በምጣኔ ሃብት እና በስትራቴጂ ተጎጂ ሆነዋል።
በአንድ ቀጣና የሚነሳ ግጭት በሌሎች አካባቢዎችም ግጭት እንደሚቀሰቅስ ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ።
ምዕራባውያን መዘናጋታቸውን በማየት ቻይና ታይዋንን ለመጠቅለል ትሞክር ይሆናል። ሩሲያም በዩክሬን የምትወስደውን እርምጃ ልታጠናክር ትችላለች።
ፕሮፌሰር ማርጋሬት "ግጭት ከቀጣናው ውጪ ሊስፋፋ ይችላል" ይላሉ።
በዚህ ግጭት ውስጥ ዕድሎች የሚታዩዋቸው አገራት በጦርነቱ ውስጥ መግባታቸው ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ነው።
ፕሮፌሰር ጆ በበኩላቸው ጦርነቱ ቀጣናዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ያምናሉ። ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ወደ ጦርነቱ ሊገባ ይችላል።
ቻይና እና ሩሲያ የጦርነቱ አካል ይሆናሉ ብለው ግን አይጠብቁም።
"ዓለም ላይ አንድ ነገር ሲከሰት ቻይና ታይዋንን ትጠቀልላች የሚለው ፍርሃት ትርጉም የለሽ ነው። ስለ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እያወራን ከሆነ ቻይና እና ሩሲያን በቀጥታ የሚያሳትፍ አይሆንም። የአውሮፓ የመካተት ዕድልም በጣም ጠባብ ነው" ይላሉ።
ቻይና ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የምትከተለውን ፖሊሲ ሲገልጹም "ተገዳዳሪ አገር የስትራቴጂ ስህተት ሲሠራ ማስቆም አያዋጣም" በማለት ነው።
የነዳጅ ዋጋ መጨመር ከፍተኛ ጫና ያሳደረባት ቻይና አሸማጋይ ከመሆን ተጠቃሚ አትሆንም?
ፕሮፌሰር ጆ እንደሚሉት፤ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ካሳደረው ጫና በበለጠ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ዋጋ አለው። አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ስትያዝ ቻይና የነዳጅ ሽያጭ ማካሄድ ትችላለች።
የመሪዎች ሚና
ታሪክ እንደሚያሳየው ጦርነት በመታበይ፣ በኩራት እና ተገዳዳሪ አገራትን በመፍራት ይጀመራል።
ፕሮፌሰር ማርጋሬት እንደሚሉት መሪዎችም የጦርነት ሁኔታን ይወስናሉ።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርጊስ ክሜንሲው "ጦርነትን ከመጨረስ ይልቅ መጀመር ይቀልላል" ያሉት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር።
ብዙ ውድመት እና እልቂት ከደረሰ በኋላ ጦርነትን የመቀጠል አዝማሚያ እንዳለ ተንታኞች ይናገራሉ።
የታሪክ ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት የመሪዎች መታበይ እና ኩራት ጦርነትን እንደሚያስቀጥል ማሳያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ናቸው።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ባወጣው አሀዝ ሩሲያ 1.25 ሚሊዮን ሰዎች አጥታለች። ይህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ ከሞቱባት ወታደሮች የበለጠ ነው።
ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት መሸነፋቸውን ማመን የማይፈልጉ መሪዎች ጦርነትን ያስቀጥላሉ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው አዶልፍ ሂትለር እና የሚያቀነቅነው ጽንሰ ሐሳብ እንደማያሸንፍ እየታወቀ ውጊያ መቀጠሉ ነው።
ጦርነትን ማርገብ
ጦርነትን ለማቆም ዲፕሎማሲ ቁልፍ ቦታ አለው።
የታሪክ ተመራማሪው እንደሚሉት ከሁልጊዜው በተቃራኒ ወገን ያለውን ፍላጎት መረዳት ያስፈልጋል። ከዚያም ወደ ንግግር ማምራት።
የታሪክ ፕሮፌሰር ማርጋሬት እንደሚሉት በቀዝቃዛው ጦርነት ማገባደጃ ላይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ማኅበር (ኔቶ) ጣልቃ መግባትን ተከትሎ በሁሉም ወገን ለመነጋገር ዝግጁ ሆኗል።
"ይሄ ነገር እብደት ነው ብለው ቀዝቀዝ የሚሉ ሰዎች ሁሌም አይታጡም። ከቁጥጥር ሊወጣ እንደሚችል በማሰብ ነገሮችን ያረግባሉ" ይላሉ።
ኃያላን አገራት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ስጋት መኖሩን ሳይጠቅሱ አያልፉም።
ፕሮፌሰር ጆ በበሉላቸው "ዋሽንግተን፣ ቴል አቪቭ እና ቴህራን ማሳካት የሚችሉት ጥግ ድረስ መሄዳቸውን ማመን አለባቸው" በማለት ጦርነቱ ለማክተም የሚያስፈልገውን የመጀመሪያ ደረጃ ያስቀምጣሉ።
ተጨማሪ ጦርነት ለየትኛውም ወግን "ተጨማሪ ውጤት" እንደማያመጣ ይናገራሉ።
"ማዕቀብ ማንሳት ያስፈልጋል። ደኅንነትን ለማስጠበቅ ስምምነት ለማድረግ ከውሳኔ መደረስም አለበት። ኢራን በዓለም ያላትን ቦታ መገንዘብም ያሻል" በማለት ተንታኙ ያብራራሉ።
በድርድር የተኩስ አቁም ላይ መድረስ እንደሚቻል ያምናሉ። ከዚያም ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ተስፋ ያደርጋሉ።