ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ልታዘጋው ትችላለች ተብሎ የተሰጋው ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆነው ወሳኙ መተላለፊያ
ኢራን ወሳኙን የቀይ ባሕር የመርከብ መስመር እንደምትዘጋ መዛቷን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተጨማሪ መስተጓጎል ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች። ይህም ነዳጅ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ እንዳይወጣ አድርጓል። አሁን ደግሞ ዐይኗን በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባሕር መካከል በሚገኘው የባብ-ኤል መንደብ ወሽመጥ ላይ በመጣል የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ እየዛተች ነው።
ኢራን የአሜሪካ ወታደሮች በግዛቷ ላይ ከተሰማሩ ጦርነቱን ወደ "ሌሎች ግንባሮች ማስፋት" እንደምትችል ተናግራለች።
"የባብ ኤል-መንዳብ ወሽመጥ ከዓለም ስትራቴጂካዊ የባሕር ወሽመጦች አንዱ እንደሆነ ይቆጠራል። ኢራን በወሽመጡ ላይ ስጋት የመደቀን ፍላጎትም ሆነ ችሎታ አላት" ሲሉ ከእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ወታደራዊ መኮንን መናገራቸውን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
አሜሪካ ዋና የነዳጅ ተርሚናል የሆነውን የኻርግ ደሴትን ካጠቃች ኢራን የባሕር ወሽመጡን እንደምትዘጋ አስፈራርታለች። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ነዳጅ "መውሰድ" እንደሚፈልጉ እና ደሴቲቱን ለመያዝ እያሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ባብ ኤል-መንደብ ለምን አስፈላጊ ሆነ?
የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥን በቀይ ባሕር እና በአረቢያ ባሕር በየመን፤ በአፍሪካ ቀንድ በጂቡቲ እና በኤርትራ መካከል ይገኛል። ከሕንድ ውቅያኖስ እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚመጡ መርከቦች ወደ ሱዊዝ ቦይ ለመድረስ በወሽመጡ በኩል ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።
በ115 ኪ.ሜ ርዝመት እና 36 ኪ.ሜ ስፋት አለው። በአውሮፓውያኑ 1869 የሱዊዝ ቦይ መከፈቱ ወሽመጡን በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የማይተካ አገናኝ መተላለፊያ አድርጎታል። ይህም በአውሮፓ እና በእስያ መካከል አጭሩ የባሕር መንገድ እንዲሆን በር ከፍቷል።
የቀይ ባሕር ኮሪደር በጣም ሥራ ከሚበዛባቸው የመርከብ መስመሮች አንዱ ሲሆን፣ ከዓለም የባሕር ትራፊክ ውስጥ አንድ አራተኛውን ያህል ያስተናግዳል።
የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል በሚባልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ ከተዘጋ ተጨማሪ 12 በመቶ የዓለምን ነዳጅ አቅርቦት ይናጋል።
እንደ አሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር ገለጻ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ አገራት ወደ ምዕራብ የሚጓጓዝ አምስት ሚሊዮን በርሜል የሚገመት ነዳጅ በየቀኑ በወሽመጡ በኩል ያልፋል።
በተጨማሪም 8 በመቶ የሚሆነው የዓለም ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በዚሁ መስመር ስለሚተላለፍ ወሽመጡን ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ የደም ሥር ያደርገዋል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ ቀይ ባሕር በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ጠቀሜታው ከፍ ብሏል። ሳዑዲ አረቢያ ከያንቡ ወደብ ነዳጅ ለማጓጓዝ ባብ ኤል-መንደብን መጠቀም ጀምራለች። ሪያድ በየቀኑ ከምሥራቃዊ ነዳጅ ማውጫዎቿ በቧንቧ በሚሊዮን የሚቆጠር በርሜሎችን ታስተላልፋለች።
ከድፍድፍ ነዳጅ እና ከጋዝ በተጨማሪ፣ የባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ያለ ዋና የንግድ መስመር ሲሆን፣ በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ የጭነት መርከቦች በዚሁ መስመር በኩል ያልፋሉ።
መስመሩ ከተዘጋ በ2021 የፓናማ የጭነት መርከብ ኤቨር ጊቨን የስዊዝ ቦይን በመዝጋት የፈጠረችውን ዓይነት ተጽዕኖ በዓለም የነዳጅ እና የምርቶች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫናን ይፈጠራል።
በወቅቱ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ከባድ ማነቆዎች ተፈጥሮ ነበር። ይህም የነዳጅ አቅርቦትን እና የተለያዩ እቃዎችን ጉዞ ከማዘግየቱም በተጨማሪ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል።
የሁቲዎች ሚና
በባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ ላይ የሚሰነዘረው ማንኛውም ጥቃት በኢራን በሚደገፈው እና መቀመጫውን በየመን ባደረገው በሁቲ በኩል ሊሆን ይችላል።
ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ የሁቲ መሪ ቡድኑ ቴህራንን በመደገፍ የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን ለማጥቃት "በወታደራዊ መንገድ ዝግጁ" መሆኑን ለሮይተርስ ተናግሯል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁቲዎች ከቀናት በፊት እስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። እስራኤል ከየመን የተሰነዘሩባትን ሁለት ሚሳዔሎችን እንደተኮሰች ተናግራለች።
ቡድኑ የየመንን የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የሚቆጣጠር ሲሆን፣ በጋዛ ጦርነት ወቅት የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን ዒላማ አድርጎ ነበር። ሁቲዎች ከ100 በላይ የንግድ መርከቦችን በሚሳዔል እና በድሮን አጥቅተው ሁለት መርከቦችን ያሰመጡ ሲሆን፣ አራት መርከበኞችን ገድለዋል።
ቡድኑ ኅዳር 2023 በቀይ ባሕር ላይ ሲንቀሳቀስ የነበር በጃፓን የተመዘገበ የዩናይትድ ኪንግደም የጭነት መርከብን ለመጥለፍ ሄሊኮፕተር ተጠቅሟል።
ሁቲዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ብቻ ዒላማ እንደሚያደርጉ ቢናገሩም፣ ጥቃቶቹ ያለልዩነት እንደሚደረጉ በሰፊው ተገልጿል። ይህም በርካታ የዓለማችን ትላልቅ የመርከብ እና የነዳጅ ኩባንያዎች አካባቢውን መጠቀም እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል።
ሁቲዎች እጅ እንደሰጡ አሜሪካ ስትገልጽ ሁቲዎች በበኩላቸው አሜሪካ ማፈግፈጓን በወቅቱ ገልጸው ነበር። ተንታኞች ጥቃቱን በድጋሚ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው።
"ጦርነቱ ከቀጠለ ሁቲዎች ይቀላቀላሉ ተብሎ ሁልጊዜም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው" ስትል የቢቢሲዋ ዘጋቢ ሊስ ዱሴት ገልጻለች።
አክላም "ሰሜን ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ቀይ ባሕርን ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ጋር የሚያገናኘውን የባብ አል-መንደብ ወሽመጥን የማስተጓጎል ትልቅ መሳሪያቸውን እስካሁን አልተጠቀሙም" ስትል አክላለች።
የአሜሪካ የትራንስፖርት መምሪያ የባሕር አስተዳደር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ "ምንም እንኳን የሁቲ አሸባሪ ቡድን በጥቅምት ወር በእስራኤል እና በጋዛ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ የንግድ መርከቦችን ባያጠቃም፤ በአካባቢው የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን ጨምሮ የአሜሪካ ንብረቶች አሁንም አደጋ ላይ መሆናቸው ይቀጥላል" ብሏል።
ጫና ውስጥ የወደቀው ዓለም አቀፍ ንግድ
ባብ አል-መንደብ በአረብኛ "የእምባ በር" ወይም "የሐዘን በር" እንደማለት ነው። በአካባቢው የሚከሰቱትን ከጠንካራ ወጀብ እና ሊተነብይ ከማይችል ነፋስ እስከ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እንዲሁም ግጭትን የመሳሰሉ አደጋዎችን ለተመለከተ ስሙ አካባቢውን ይገልጸዋል።
ከ2008 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ የባብ አል-መንደብ ወሽመጥ እና በዙሪያው ያለው ውሃ በርካታ የባሕር ወንበዴ ጥቃቶችን አስተናግዷል።
በዋናነት ጥቃቱ የሚፈጸመው በሶማሊያ ቡድኖች ሲሆን የመርከብ ሠራተኞችን አፍነው ገንዘብ ይጠይቃሉ። ክስተቶቹ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የመርከብ ኩባንያዎች በአካባቢው ያለውን ደኅንነት እንዲያጠናክሩ አስገድዷቸዋል።
የባሕር መስመሩ መዘጋት በሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የተዳከመውን የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦትን የበለጠ በማወሳሰብ የዋጋ ንረቱን ያባብሰዋል።
በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል የብሬንት ድፍድ ነዳጅ ዋጋ ከጦርነቱ በፊት ከነበረበት 70 ዶላር ወደ ከ115 ዶላር በላይ እንዲደርስ አድርጎታል።
ከሸማቾች ምርቶች እስከ ግብርና ሸቀጦች ድረስ ያለው ዓለም አቀፍ ንግድም ተጽዕኖው እየደረሰው ነው። በሌላ የባሕር መስመር ላይ አዲስ መስተጓጎል መፈጠሩ ዋጋዎችን የበለጠ ከፍ ሊያደርግ እና በኢራን ጦርነት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ውድቀት ሊያባብሰው ይችላል።